1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፍ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ትዕይንት በሃኖቨር

ረቡዕ፣ የካቲት 30 1997
https://p.dw.com/p/E0ev
የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን የምትቀበለው ሞባይል
የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን የምትቀበለው ሞባይልምስል AP

እስከፊታችን አርብ ሣምንት በሚቆየው ትዕይንት ከስድሥት ሺህ የሚበልጡ አምራቾች በመረጃና መገናኛው ቴክኖሎጂ ዙሪያ ያደረጉትን የተሃድሦ ውጤት ለጎብኚዎች ያስተዋውቃሉ። የኤሌክትሮኒኩ መገናኛ ዘርፍ ከ 2000 እስከ 2003 በተከታታይ ገጥሞት የነበረው የገበያ ቀውስ ቀላል አልነበረም። ቢሆንም ካለፈው ዓመት ወዲህ ምርቶቻቸውን ለዓለምአቀፉ ትዕይንት የሚያቀርቡት ኩባንያዎች ቁጥር በመጠኑም ቢሆን ዕድገት ማሣየቱ የአቅጣጫ ለውጥን የሚያመለክት ሆኖ ተገኝቷል። ሴ.ቢት እንደቀድሞው ማበብ እየጀመረ ነው። የሃኖቨር አዘጋጆችም በዓለም ላይ ታላቁ የሆነው የኤሌክትሮኒኩ ዘርፍ ትዕይንት ነቅሎ ወደ ሌላ አገር እንዳይሄድ ለመግታት በቅተዋል።

ለነገሩ ቀደም ያሉትን አርኪ የዝግጅት ውጤቶች ለተመለከተ ሃኖቨር የትዕይንቱ ማዕከል ሆና መቆየቷ እምብዛም አያስደንቅም። መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል በዓለም ላይ የመጀመሪያው ተንቀሳቃሽ ኮምፒዩተር ሌፕቶፕም ሆነ የመጀመሪያው ሄንዲይ ወይም ሞባይል በዚያው ነበር ለትርዒት ቀርቦ የተዋወቀው። ዛሬ በዓለም ላይ ለግልጋሎት የሚውሉት ሌፕቶፖች ከሁለት ሚሊያርድ ይበልጣሉ። 3.5 ሚሊያርድ ሞባይሎች ከተጠቃሚው ዕጅ መድረሳቸውም ነው የሚገመተው። የሴ.ቢት ታሪክ እንግዲህ የትዕይንቱ አዘጋጆች አፈ-ቀላጤ ሚሻኤል ጋይደ እንደሚሉት የወደፊቱን ተሥፋ የሚያዳብር ነው።

በዕውነትም አዲስ የተሃድሶ ስሜት መሰረጹ ሰሞኑን በትዕይንቱ መክፈቻ ዋዜማ ከመቼውም ይበልጥ ጎልቶ ታይቷል። የመገናኛ ቴክኖሎጂው ኩባንያዎች መዋዕለ-ነዋይን በሥራ ላይ ማዋሉን በተመለከተ ባለፉት ጊዜያት ያሣዩት ቁጥብነት በዚህ ትዕይንት ሂደት መልኩን እንደሚለውጥ የብዙዎች የዘርፉ አዋቂዎች ዕምነት ነው።

እርግጥ በአስተናጋጇ አገር በጀርመን የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦቱም ሆነ የተጠቃሚው ብዛት ከሌሎች በቴክኖሎጂው ዕውቀት ከዳበሩ አገሮች ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው። ይሁንና የሃኖቨሩ ትዕይንት ሴ.ቢት በአጠቃላይ በዓለም ላይ እንደገና በሚታየው የኤኮኖሚ ዕድገት በመጠቀም ይህንኑ ቀዳዳ መሽፈኑ የሚያዳግተው አይመስልም።

በትዕይንቱ የሚሳተፉት የውጭ ኩባንያዎች እጅግ ብዙዎች ናቸው። የምርት አቅራቢዎቹ ቁጥር ዘንድሮ ከፍ በማለት 6.300 ገደማ ደርሷል። በተለይ ደግሞ በእሢያው ገበያ ላይ ዕድገቱ ከፍተኛ ነው። በወቅቱ በሃኖቨሩ ትዕይንት ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁት የእሢያ ኩባንያዎች ቁጥር ከ 1.600 ይበልጣል።

ሴ.ቢት ታላቁ የኮምፒዩተር ትዕይንት ብቻ ሣይሆን እነዚሁ የእሢያ አምራቾች የሚገናኙበትና የውስጥ ልውውጣቸውን የሚያከናውኑበትም ዋናው መድረክ ነው። ከነዚሁ ዋና ዋናዎቹ ታይዋን ከ 770 በሚበልጡ፣ ሕዝባዊት ቻይና በ 310፤ ይህም ካለፈው ጊዜ ሲነጻጸር እጥፍ መሆኑ ነው፤ እና ደቡብ ኮሪያ ከ 200 በሚበልጡ አምራቾች በትዕይንቱ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የዘንድሮውን የሃኖቨር የኤሌክትሮኒክ ጥበብ ትዕይንት 500 ሺህ ጎብኚዎች እንደሚመለከቱት የሚገመት ሲሆን በኢንተርኔት አማካይነት ስልክ መደወል የሚያስችለው (Voice over IT ወይም የድምጽ ስርጭት በኢንተርኔት ፕሮቶኮል) የተሰኘው ግኝት ይበልጥ የብዙዎችን ትኩረት እንደሚስብ የአዘጋጆቹ ዕምነት ነው። ተመልካቹ በርከት ያሉ አዳዲስና ዘመናዊ ምርቶች ተደርድረው ይጠብቁታል። አዳዲሶቹ ኮምፒዩተሮች-ሌፕቶፖችና ሞባይሎች ብዙ ማከናወን የሚችሉ ከዚህ ቀደም የበለጠ አገልግሎት የሚሰጡ ሆነው ነው የቀረቡት።

ለምሳሌ የራዲዮ ስርጭቶችን ከመቀበል ባሻገር ሙዚቃን በረቀቀ መንገድ የሚያጫውቱና በቅርቡም ዲጂታል የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ማሣየት የሚችሉ ሞባይሎች ሰሞኑን ሕዝብ ከሚደነቅባቸው ምርቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ከአቅራቢዎቹ መካከል አንዱና ታላቁ የጀርመኑ ኩባንያ ዚመንስ የዶቼ ቬለን ጨምሮ አምሥት የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የሚስብ ሞባይሉን ያሣያል። የኮምፒዩተር ጽሕፈት መምቻዎችን በላዘር፤ ማለት በጨረርታ አማካይነት ተሃድሶ የሚሰጠው የቴክኖሎጂ ግኝትም ሌላው አስደናቂ ነገር ነው።