1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፍ ስፖርት

ሰኞ፣ ጥቅምት 12 2005

በእግር ኳሱ ዓለም በዚህ በአውሮፓ ሣምንቱ የሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያዎች የሚካሄዱበት ሲሆን ሰንበቱም በቀደምቱ ሊጋዎች ብሄራዊ ውድድሮች ላይ ድምቀት የታየበት ሆኖ ነው ያለፈው።

https://p.dw.com/p/16Ucw
ምስል Getty Images

በእግር ኳሱ ዓለም በዚህ በአውሮፓ ሣምንቱ የሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያዎች የሚካሄዱበት ሲሆን ሰንበቱም በቀደምቱ ሊጋዎች ብሄራዊ ውድድሮች ላይ ድምቀት የታየበት ሆኖ ነው ያለፈው። በዚህ በጀርመን ባየርን ሙንሺን ስምንተኛ ግጥሚያውንም በተከታታይ በድል በመወጣት አዲስ የቡንደስሊጋ ክብረ-ወሰን ሲያስመዘግብ በስፓኝ ላ-ሊጋም ዕድሜ ለሊዮኔል ሜሢ ባርሣ ግንባር-ቀደም እንደሆነ ቀጥሏል።

ዘገባችንን በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እንጀምርና ኤፍ-ሲ ቼልሢይ በስምንት ግጥሚያዎቹ አንዴ እኩል ለእኩል ከመውጣቱ በስተቀር አንዴም ሳይሸነፍ አመራሩን ይዞ እንደቀጠለ ነው። ቼልሢይ ባለፈው ቅዳሜ ቶተንሃም ሆትስፐርን 4-2 ሲያሸንፍ በጠቅላላው 22 ነጥቦች አሉት። ማንቼስተር ዩናይትድም ስቶክ ሢቲይን በተመሳሳይ ውጤት ሲረታ አራት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሁለተኛ ነው።  18 ነጥቦች አሉት።                                                                      

ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ማንቼስተር ሢቲይም በአልቢዮን 1-0 ከተመራ በኋላ በ 2-1 ሲያሸንፍ ከከተማ ተፎካካሪው ከማኒዩ ጋር በነጥብ እኩል እንደሆነ ቀጥሏል። ለማንቼስተር ሢቲይ የዘገዩትን ሁለት ጎሎች ያስቆጠረው ተቀይሮ ሜዳ የገባው የቦስና ብሄራዊ ተጫዋች ኤዲን ጄኮ ነበር። ከኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስ አቻ ለአቻ 1-1 የተለያየው ኤቨርተን በ 15 ነጥቦች አራተኛ ሲሆን አርሰናል በአንጻሩ በኖርቮች ሢቲይ 1-0 በመረታት ወደ 9ኛው ቦታ አቆልቁሏል። ሊቨርፑል ደግሞ 12ኛ ነው። 

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ባርሤሎና በስምንት ግጥሚያዎች 22 ነጥቦችን በማግኘት ሊጋውን በጎል ብልጫ ይመራል። ቡድኑ ከዴፖርቲቮ ላ ኮሩኛ ጋር ያደረገው ግጥሚያ የጎል ፌስታ የታየበት ነበር። ጨዋታው 5-4 በሆነ ውጤት ሲፈጸም በመጀመሪያ መርቶ የነበረው ባርሣ ተሸንፎ ከሜዳ ባለመውጣቱ ለብቻው ሶሥት ጎሎች ያስቆጠረውን ድንቅ ኮከቡን ሊዮኔል ሜሢን እጅጉን ሊያመሰግን ይገባዋል። ሊዮኔል ሜሢ በዚህ ሰንበት 11ኛ የሊጋ ጎሉን ሲያቆጥር በጎል አግቢነትም በወቅቱ በፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ውስጥ ቀደምቱ ነው።                                                                                          

የዓመቱ የዓለም ድንቅ ተጫዋችሜሢ በዚህ ዓመት ለክለቡና ለአገሩ ያስቆጠረው ጎል 71 ሲደርስ ታላቁ የብራዚል ኮከብ ፔሌ በ 1959 አስመዝግቦት ከነበረው ክብረ-ወሰን ላይ ለመድረስ የሚቀሩት አራት ግቦች ብቻ ናቸው።  ወደ ስፓኙ ፕሬሜራ ዲቪዚዮን ወቅታዊ ውድድር እንመለስና ሬያል ሶሲየዳድን 1-0 ያሸነፈው አትሌቲኮ ማድሪድም ከባርሣ ጋር እኩል ነጥቦች ሲኖሩት ሆኖም በጎል በመበለጥ ሁለተኛ ነው። ማላጋ ደግሞ በ17 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድም ሤልታ ቪጎን 2-0 በመሸኘት በአራተኝነቱ መጽናቱ ተሳክቶለታል። 

Fußball Bundesliga Fortuna Düsseldorf FC Bayern München
ምስል picture-alliance/dpa

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ባየርን ሙንሺን ስምንት ግጥሚያዎቹን በሙሉ በተከታታይ በማሸነፍ አዲስ የሊጋ ክብረ-ወሰን ማስመዝገቡ ሰምሮለታል። የጀርመኑ ሬኮርድ ሻምፒዮን ባየርን ከሁለተኛው ዲቪዚዮን የወጣውን ዱስልዶርፍን 5-0 ሲቀጣ በዚህ ሣምንትም እንዳለፉት ሁሉ ፍጹም ልዕልና ነው ያሳየው። ጎሎቹን ማሪዮ ማንጁኪች፣ ሉዊስ ጉስታቮ፣ ቶማስ ሙለርና ራፊኛ ሲያስቆጥሩ ሁለቱን ጎሎች ያስገባው ቶማስ ሙለር እንደሚለው ለስኬቱ ዋናው ምክንያት በተለይም የቡድኑ ጥንካሬ ነው። ራሱን ማወደሱን አልመረጠም።

«ሁሉም ነገር ጥሩ እየተራመደ ነው። ቡድኑ ጥሩ ነው የሚጫወተው። ዋናው ነገር ደግሞ ይሄው ይመስለኛል። የተሟላ ቡድን ከሌለ በግል ደምቆ ለመታየት አይቻልም። እኔም ቢሆን የቡድን ተጫዋች እንጂ የግል ጠቢብ አይደለሁም። በጥቅሉ ቡድኑ በወቅቱ እጅግ ግሩም ነው። እና እኔም በዚህ በጣም ነው የምደሰተው»

ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ዶርትሚንድ በበኩሉ የተመልካቾች ሁኸት በታየበት ግጥሚያ በሻልከ በሜዳው 2-1 ሲሸነፍ ከሶሥተኛው ቦታ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አምሥት ከፍ ብሏል። የሻልከ ድል አሠልጣኙ ሁብ ስቴቨንስ እንዳለው በትግል እንጂ በአጋጣሚ የተገኘ አልነበረም።

«ዕውነተኛ የአካባቢ ፉክክር የሰፈነበት ግጥሚያ ነበር። ተጫዋቾቼ ለድል ለመብቃት በጣሙን ነው የታገሉት። እናም ዘጠናውን ደቂቃ በሙሉ ከተመለከትን በሚገባ አሸንፈናል ለማለት እችላለሁ»

በተቀሩት የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች ሌቨርኩዝን ከማይንስ 2-2 እና ሆፈንሃይም ከፉርት 3-3 ሲለያዩ ቮልፍስቡርግ ለዚያውም በገዛ ሜዳው በፍራይቡርግ ሁለት ለባዶ በመረታት ባለፉት ሣምንታት አቆልቋይ ሂደቱ ቀጥሏል። አሁን መጨረሻ ነው። በሌላ በኩል አይንትራኽት ፍራንክፉርት ሃኖቨርን 3-1 በማሸነፍ በሁለተኝነቱ ሲቀጥል ብሬመን ደግሞ በድንቅ ጨዋታ ግላድባህን 4-0 በመሸኘት ወደ ዘጠነኛው ቦታ ክፍ ሊል በቅቷል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ የቅርብ ተፎካካሪውን ናፖሊን በዘገዩ ጎሎች 2-0 ሲያሸንፍ አሁን በሶሥት ነጥቦች ብልጫ እየመራ ነው። ናፖሊ ቢሸነፍም በ 19 ነጥቦች ሁለተኛ እንደሆነ ቀጥሏል። የሣምንቱ ውጤት ተጠቃሚዎች ናፖሊን እስከ አንዲት ነጥብ ልዩነት የተቃረቡት ላሢዮና ኢንተር ሚላን ነበሩ። ሁለቱም ክለቦች የየበኩላቸውን ግጥሚያ ማሸነፉ ሲሆንላቸው አሁን ሶሥተኛና አራተኛ ናቸው። ሮማና ፊዮሬንቲና ደግሞ ፈንጠር ብለው ይከተላሉ። በተረፈ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ፓሪስ-ሣንት-ዠርማንና በኔዘርላንድ ሻምፒዮናም ትዌንቴ ኤንሼዴ የየበኩላቸውን ሊጋዎች መምራት ቀጥለዋል።

Berlin Marathon Männer
ምስል AP

በመሃሉ በአትሌቲክስ ላይ እናተኩርና በትናንትናው ዕለት በኔዘርላንድ ተካሂዶ በነበረው የአምስተርዳም ማራቶን ሩጫ የኢትዮጵያ አትሌቶች በጥቅሉ ግሩም ውጤት አስመዝግበዋል። በወንዶች ምንም እንኳ ኬንያዊው ዊልሰን ቼቤት ቢያሸንፍም ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡት ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ስንታየሁ አሰፋ ሁለተኛ፤ አብርሃ ገ/ጻዲቅ ሶሥተኛ! ቼቤት ሩጫውን የፈጸመው በጥሩ የሁለት ሰዓት ከአምሥት ደቂቃ 41 ሤኮንድ ጊዜ ነው።                                                                                                               

በሴቶች መሠረት ሃይሉ አሸናፊ ስትሆን ኬንያዊቱ ኦይኒስ ኪርዋ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ገነት ጌታነህ ሶሥተኛ ወጥታለች። መሠረት ሃይሉ የአምስተርዳሙን ቀደም ያለ ክብረ-ወሰን ከስድሥት ደቂቃዎች በበለጠ ጊዜ ስታሻሽል በቅርቡ በቡልጋሪያ ግማሽ ማራቶን ሩጫ ባሳየችው ጥንካሬዋ እንደቀጠለች መሆኗ ጎልቶ ታይቷል።

ከሌላ የአትሌቲክስ ዜና ለመረዳት እንደቻልነው በሴቶች ያለፈው የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊ ፍሬሕይወት ዳዶ በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው ውድድር ድሏን ለመድገም አትካፈልም። ለዚሁም ምክንያቱ የአትሌቷ የአካል ጉዳት መሆኑን ዛሬ አዘጋጆቹ አመልክተዋል። በሌላ በኩል በዘንድሮው የኒውዮርክ ማራቶን ውድድር ከሚጠበቁት ዕውቅ አትሌቶች መካከል ኬንያዊቱ የዓለም ሻምፒዮን ኤድና ኪፕላጋት፣ ኢትዮጵያዊቱ የለንደን ማራቶን አሸናፊ ቲኪ ገላናና በዚያው በኦሎምፒያ የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ የነበረችው ሩሢያዊት ታቲያና አርካፖቫ ቀደምቱ ናቸው።

በአውሮፓ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ሊጋ በዚህ ሣምንት የመጀመሪያ አጋማሽ ውስጥ ሶሥተኛ ዙር የምድብ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ከነዚሁ መካከል ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል በነገው ምሽት ቼልሢይ ከኡክራኒያው ዶኔትስክ፤ ባየርን ሙንሺን ከፈረንሣዩ ሊልና ባርሤሎና ከሤልቲክ ግላስጎው የሚገናኙ ሲሆን በማግሥቱ ረቡዕ ደግሞ ፖርቶ ከዲናሞ ኪየቭ፤ አርሰናል ከሻልከ፤ አያክስ አምስተርዳም ከማንቼስተር ሢቲይና ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ከሬያል ማድሪድ በታላቅ ጉጉት የሚጠበቁት ናቸው።

Bildergalerie Africa Cup Of Nations Südafrika
ምስል gettyimages

ለ 2013 ዓመተ-ምሕረት የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የሚደረገው የመጀመሪያ ዙር ውድድር ዕጣ በፊታችን ረቡዕ በአዘጋጇ በደቡብ አፍሪቃ የሕንድ ውቂያኖስ ወደብ በደርባን ይወጣል። ኢትዮጵያም ቀደም ባለው ማጣሪያ ሱዳንን አልፋ በዕጣው የምትሳተፍ ሲሆን ጥሩ ምድብ እንደሚገጥማት ተሥፋ እናደርጋለን። የ 2010 የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ አዘጋጅ ደቡብ አፍሪቃም ግሩም መስተንግዶ ማድረጉ እንደሚሳካላት በሰፊው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።                                                    

በነገራችን ላይ ደቡብ አፍሪቃ ፍጻሜውን ስታዘጋጅ መጨው ሁለተኛው ሲሆን አገሪቱ አሁንም ለዝግጅቱ ቀደምቷ ምርጫ አልነበችም። ደቡብ አፍሪቃ በ 1996 ዝግጅቱን የገንዘብ ችግር ከገጠማት ከኬንያ ስትረከብ መጪውንም የምታስተናግደው የፖለቲካ ቀውስ ገጥሟት በነበረው በሊቢያ ምትክ ነው። በዚያው በአፍሪቃ ትናንትና ከትናንት በስቲያ የአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር። የግብጹ አል-አህሊ ካይሮ ላይ የናይጄሪያ ተጋጣሚውን 1-0 ሲረታ የቱኒዚያው ኤስፔራንስም የዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ ተፎካካሪውን ማዜምቤን በተመሳሳይ ውጤት አሸንፏል። በአጠቃላይ ውጤት ለፍጻሜው ማለፉ የተሳካላቸው አል አህሊና ኤስፔራንስ ናቸው።

ለሁለት ዓመታት ያህል በአካል ጉዳት መሰናክል ሲገጥማት የቆየችው አሜሪካዊት የቴኒስ ኮከብ ቬኑስ ዊሊያምስ ትናንት በሉክሰምቡርግ-ኦፕን ፍጻሜ በማሸነፍ ለረጅም ጊዜ ለጠበቀችው ድል በቅታለች። ቬኑስ ዊሊያምስ የሩሜኒያ ተጋጣሚዋን ሞኒካ ኒኩሌስኩን 6-2,6-3 በሆነ በለየለት ውጤት ስታሸንፍ ይህም በአጠቃላይ 44ኛ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ድሏ መሆኑ ነው።  በስቶክሆልም-ኦፕን ፍጻሜም የቼኩ ቶማስ በርዲች የፈረንሣይ ተጋጣሚውን ጆ-ዊልፍሪድ-ሶንጋን 2-1 በሆነ ውጤት በመርታት ለዓመቱ ማጠቃለያ የዓለም ቴኒስ ፍጻሜ ዙር ለመድረስ ዕድሉን ከፍ አድርጓል።                                       

በቪየና-ኦፕን ደግሞ አርጄንቲናዊው ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖትሮ የስሎቬኒያ ተጋጣሚውን ግሬጋ ዜምልያን በሁለት ምድብ ጨዋታ አሸንፏል። ከዚሁ ሌላ በቫሌንሢያ-ኦፕን ፍጻሜ የክሮኤሺያው ማሪን ቺሊች የሰሎቫኪያውን ማርቲን ክሊዛንን ሲያሸንፍ በሞስኮ የክሬምሊን ዋንጫ ደግሞ በሴቶች የደንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ አውስትራሊያዊቱን ሣማንታ ስቶሱርን፤ በወንዶችም የኢጣሊያው አንድሬያስ ሤፒ የብራዚሉን ቶማሽ ቤሉቺን መርታቱ ተሳክቶላቸዋል።

Olympia 2012 Tischtennis Timo Boll
ምስል dapd

በጠረጴዛ ቴኒስ ጀርመናዊው ኮከብ ተጫዋች ቲሞ ቦል በዚሁ የስፖርት ዓይነት በአውሮፓ አቻ የሌለው መሆኑን እንደገና ለማስመስከር በቅቷል። ቲሞ ቦል ትናንት በዴንማርክ ሄኒንግ ላይ በተጠቃለለው የአውሮፓ ሻምፒዮና የክሮኤሺያ ተጋጣሚውን ታን ሩዊቩን 4-1 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ድሉ በተከታታይ ስድሥተኛው መሆኑ ነው። በሴቶች ደግሞ የቤላሩሷ ቪክቶሪያ ፓብሎቪች ለሁለተኛ ጊዜ ለፍጻሜ ድል በቅታለች።

በተረፈ የትናንቱ ሰንበት ለሌላ ጀርመናዊ ስፖርተኛም የሰመረ ነበር። ማሌይዚያ ውስጥ በተካሄደ የሞተር ቢስክሌት የዓለም ሻምፒዮና ሣንድሮ ኮርቴስ በአዲሱ ሞቶ 3 ደረጃ  አሸናፊ ሆኗል። ኮርቴስ በዚሁ ውጤቱ በመጪው ዓመት ወደ ሞቶ 2 ደረጃ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል።

መሥፍን መኮንን