1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፉ የቱሪዝም ንግድ

ረቡዕ፣ የካቲት 30 2003

የቱሪዝም የንግድ መስክ በዓለም ዙሪያ አንድ መቶ ሚሊዮን ሠራተኞችን ያቀፈ አንዱ የኤኮኖሚ ዕድገት ጠቃሚ ዘርፍ ነው።

https://p.dw.com/p/R7gk
ምስል dapd

በዚሁ ዘርፍ ላይ ያተኮረው ታላቁና ዓመታዊው የቱሪዝም ትዕይንት ደግሞ ዛሬ በርሊን ላይ ተከፍቷል። በትዕይንቱ ላይ ከአያሌ ሃገራት የመጡ የዘርፉ ተወካዮች የሚሳተፉ ሲሆን ከነዚሁ መካከል የኢትዮጵያ የቱሪዝም ተጠሪዎችም ይገኙበታል።

በዓለምአቀፉ የጉዞ ኢንዱስትሪ ትዕይንት ላይ ከ 188 ሃገራት የመጡ ከ 11 ሺህ የሚበልጡ የቱሪዝም ተወካዮች በየአዳራሹ ተሰማርተው ራሳቸውን እያስተዋወቁ ነው። የስፍራው በብዙ አቅራቢዎች መጨናነቅ ንግዱ ከዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ወዲህ መልሶ እያበበ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ነው የጀርመን የቱሪዝም ዘርፍ ፌደራል ማሕበር ፕሬዚደንት ክላውስ ሌፕለ ያመለከቱት።

“2011 በቱሪዝም ረገድ ጠንካራው ዓመት እንደሚሆን እርግጠኛ ነገር ነው። እስካሁን ለቱሪዝሙ ንግድ ግሩም የነበረውን የ 2008 ዓ.ም.ን መጠን አልፈን ለመሄድና በሁሉም መስክ አቻ ያልታየለት አዲስ ውጤት ለማስመዝገብ እንችላለን”

ለምሳሌ በዚህ በጀርመን ባለፈው ዓመት የጉዞ ወኪሎቹ ገቢ በጥሩ የኤኮኖሚ ሁኔታ የተነሣ ወደ 21,3 ሚሊያርድ ኤውሮ ከፍ ብሎ ነበር። ይህም ቀደም ካለው 2009 ዓ.ም. ሲነጻጸር በ 2,5 ከመቶ የላቀ መሆኑ ነው። ጀርመናውያን በተጓዥነት በዓለም ላይ በሰፊው የታወቁ ሲሆኑ ለቱሪዝም በያመቱ የሚያወጡት ገንዘብ 60 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ይጠጋል። የአገሪቱ ጎብኚዎች በአውሮፓ በብዛት የሚጎርፉትም ወደ ስፓኝ ሲሆን ሌሎች የሜዴትራኒያን አካባቢ አገሮችም በጣም ተወዳጆች ናቸው።

ITB Eröffnungsrundgang
ሲከፈትምስል picture alliance/dpa

እርግጥ ጀርመናውያን ወደ ውጭ በመጓዝ ብቻ ሣይሆን እረፍትን በአገር ውስጥ በማሳለፍም ረገድ ቁጥራቸው እየጨመረ ሲሄድ ነው የሚታየው። ከጀርመን ተጓዦች አርባ በመቶ የሚሆኑት ባለፈው ዓመት እረፍታቸውን በራሳቸው አገር ማሳለፋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። አገሪቱን የሚጎበኘው የውጭ ቱሪስትም በአሥር ከመቶ ነው የጨመረው።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የቱሪዝም ወኪሎችም ዘንድሮም በበርሊኑ ትዕይንት ላይ በሰፊው በንቃት እየተሳተፉ ሲሆን ስለ አገሪቱ ቱሪዝም ዕድገትና የወደፊት ተግባር የተቋሙን የማርኬቲንግ ክፍል ባልደረባ አቶ ተሥፋዬ ደሣለኝን ዛሬ አነጋግረን ነበር፤ ያድምጡ!

አምሥት ቀናት በሚፈጀው በበርሊኑ ዓለምአቀፉ የቱሪዝም ትዕይንት ላይ መጠናቸው ስድሥት ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ የሚደርስ የቱሪዝም ንግድ ውሎች እንደሚፈረሙ ነው የሚገመተው። ትዕይንቱን በጠቅላላው 170 ሺህ ሰዎች እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን የልማት ድርጅትና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ቱሪዝም በታዳጊ አገሮች ለማሕበራዊ ዕድገት ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ የፖለቲካና የኤኮኖሚው ዘርፎች ታላቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ትዕይንቱን ምክንያት በማድረግ ባቀረቡት የጥናት ውጤት አስገንዝበዋል። በግብጽና በቱኒዚያ እንደታየው የቱሪዝሙ ዘርፍ ተጠቃሚዎች ይበልጡን አምገባገነን ገዢዎችና ጥቂት አበሮቻቸው መሆናቸው ማሳዘኑ አልቀረም።
በእሢያና በላቲን አሜሪካም በቱሪዝም ገንዘብ ለመካበት ሰብዓዊ ክብር የሚረገጥ ሲሆን ዘርፉ በጥቅሉ ጥቂቶች ተጠቃሚ፤ ብዙሃኑ ደግሞ ተበዝባዦች ሆነው የሚገኙበት ነው። ለምሳሌ እንደ ካምቦጃ ቱሩዝምን ለማስፋፋት ድሆች ዜጎች አካባቢዎቻቸውን ለቀው እንዲሄዱ ይገደዳሉ የዓለምአቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት የአምነስቲይ ኢንተርናሺናል ባለሙያ ካታሪና ሽፒስ እንደሚሉት።

ITB Berlin 2011 Tunesien
ቱኒዚያ በጉባኤዉምስል dapd

“በኤኮኖሚው ዕድገት ድሃው ሕዝብ አብዛኛውን ተጠቃሚ ያልሆነባት ካምቦጃ ለዚህ አንድ ጥሩ ምሳሌ ናት። የቱሪስት ይዞታዎችን ለማስፋፋት ቦታ ለማግኘት ሲባል ሰዎች ቤታቸውን ለቀው እንዲባረሩ ይደረጋሉ”

ካታሪና ሽፒስ የፖለቲካ ባለሥልጣናት ስለ ቱሪዝም በሚያስቡበት ጊዜ ሰብዓዊ መብትን እንዳይዘነጉ ነው አጥብቀው ያሳሰቡት።

መሥፍን መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ