1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፉ የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦትና አፍሪቃ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 3 1998
https://p.dw.com/p/E0eH

በዘገባው መሠረት የመዋዕለ-ነዋዩ እንቅስቃሴ እንደቀድሞው በአንድ ብቻ ሣይሆን በሁለት አቅጣጫ መራመድ መያዙም ሌላው መጠናከር የያዘ አዲስ አዝማሚያ ነው። ግን ይህም ሆኖ የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ድርሻ በተለያዩ ምክንያቶች ሲበዛ ጥቂት ነበር። ባለፈው 2004 ዓ.ም. ወደ ታዳጊ አገሮች እንዲፈስ የተደረገው ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ወይም ካፒታል 650 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚጠጋ ነበር። ይህም ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር ሁለት በመቶ ከፍ ያለ መሆኑ ነው። ከጥቂት ቀናት በፊት ለተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ፤ በአሕጽሮት UNCTAD ቀርቦ የነበረው የተቋሙ ዘገባ በመዋዕለ-ነዋይ እንቅስቃሴ አኳያ የዓለም ገጽታ መቀየር መያዙን አመልክቷል። ለዚሁም መንስዔው ራሳቸው ከባሕር ማዶ ካፒታልን በሥራ ላይ የሚያውሉት በተሣካ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኙ በመልማትና ወደ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ በሽግግር ላይ ያሉ አገሮች እየተበራከቱ መሄዳቸው ነው።

በጥናቱ መሠረት በ 2004 ከመላው የውጭ ቀጥተኛ ካፒታል 36 በመቶው የሄደው በመልማት ላይ ወደሚገኙት አገሮች ነው። ይህ ደግሞ ከሰባት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛው ሲሆን እርግጥ በሌላ በኩል በአሥር ታዳጊ አገሮች ከፍተኛ ማቆልቆል ታይቷል። ምንም እንኳ ለታዳጊው ዓለም የቀረበው የውጭ መዋዕለ-ነዋይ በአጠቃላይ ከፍ ብሎ ቢታይም ከዚሁ ሂደት ተጠቃሚ ሊሆኑ ያልቻሉት ብዙዎች ናቸው። ለምሳሌ በደቡባዊው አፍሪቃ አቅርቦቱ 18 በመቶ ወይም በአንድ ቢሊዮን ዶላር አቆልቁሎ ተገኝቷል።

ለዚሁም ምክንያት አልታጣም። በዓለም ላይ በልማት እጅግ ወደኋላ የቀሩ ተብለው የሚመደቡት ሃምሣ አገሮች የውስጥ ገበያቸው ትንሽ ነው። የሠለጠነ ሙያተኛ እጥረትና የአቅርቦት ብቃት ችግርም አለባቸው። ይህም ዓለምአቀፍ መዋዕለ-ነዋይ ለውጭ በሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በሥራ እንዲውል የሚያበረታታ አልሆነም፤ የ UNCTAD ዘገባ እንደሚያመለክተው። አፍሪቃን በአጠቃላይ ከተመለከትን የውጩ መዋዕለ-ነዋይ ቀደም ሲል በነበረበት 18 ቢሊዮን ዶላር ተወስኖ ነው የቀረው።

አብዛኛው ገንዘብ የፈሰሰውም በነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር የተነሣ ይሄው የተፈጥሮ ሃብት ባለቸው ናይጄሪያን፣ አንጎላን፤ ኤኩዋቶሪያል ጊኒንና ሱዳንን ወደመሳሰሉት አገሮች ነው። በ 2004 አፍሪቃ ከገባው የውጭ ካፒታል አብዛኛው በሥራ ላይ የዋለውም ግብጽን ጨምሮ በነዚሁ በተጠቀሱት ጥቂት አገሮች ነበር። በነዳጅ ዘይትና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ባሏቸው አገሮች በሥራ የዋለው ገንዘብ ሲቀነስ ታዲያ በርከት ላሉት ለተቀሩት ብዙም ገንዘብ አይተርፍም።
ለ UNCTAD ዘገባውን ያቀረበው Global Compact የተሰኘ የተባበሩት መንግሥታት አካል አስተዳዳሪ ጌኦርግ ኬል እንደሚሉት በአፍሪቃ የግል ኤኮኖሚውን ዘርፍ ተግባራት ለማጠናከር ገና ብዙ ነው የሚቀረው። ወደ ታዳጊ አገሮች የፈሰሰውን ካፒታል ቀረብ ብለን ካስተዋልን ዋነኛው ዕድገት የታየው በእሢያና በፓሢፊክ አካባቢዎች ነው። 46 በመቶ ድርሻ አለው። እነዚህ አካባቢዎች ባለፈው ዓመት 148ቢሊዮን ዶላር ሲቀበሉ፤ ይህም ከ 2003 ሲነጻጸር በ 46 ቢሊዮን ከፍ ያለ ነበር። በዚሁ የዓለም ክፍል ቻይናና ሆንግኮንግ ብቻቸውን ሁለት-ሶሥተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

ሕዝባዊት ቻይና አሁንም ቢሆን በታዳጊ አገርነት ነው የምትቆጠረው። ብዙዎች የአገሪቱ አካባቢዎች ገና የለሙ አይደሉም፤ ከታላቅ ከተሞች ውጭ ዛሬ በድሕነት የሚኖረው ሕዝብ ከ 500 ሚሊዮን ይበልጣል ነው የሚባለው። በላቲን አሜሪካ የውጩ አቅርቦት ከአራት ዓመታት አቆልቋይ ሂደት በኋላ 44 በመቶ በማደግ ወደ 68 ቢሊዮን ከፍ ሊል በቅቷል። ግን እዚህም ቢሆን አብዛኛው የፈሰሰው ወደ ሁለት አገሮች፤ ማለት ወደ ብራዚልና ወደ ሜክሢኮ ነበር። በዚህ አካባቢ መልሶ ለተፈጠረው ዕርምጃ ዓለምአቀፍና የአካባቢ ሁኔታዎች ተጣምረው አስተዋጽኦ አላቸው። ዋናው ነገር ግን ከረጅም ጊዜ መቆርቆዝ በኋላ የተጠናከረ የኤኮኖሚ ዕድገት መስፈኑ ነው።

በተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ጉባዔ ላይ የቀረበው ዘገባ በኩባንያዎች የምርምርና ልማት ተግባርም የመጀመሪያ ጥናት ውጤቱን ያጠቃልላል። ዘገባው እንደሚለው ይሄው የምርምርና የልማት ሂደት ዓለምአቀፍ ባሕርይ ማግኘት ለመዋዕለ-ነዋይና ለሥራ መስኮች አዲስ ዕድል የሚከፍት ነው። በዘገባው መሠረት ዓለምአቀፉ ኩባንያዎች በምርምርና ልማቱ ጉዳይ ዋነኞቹ ሃይላት ሲሆኑ ታላላቆቹ ኩባንያዎች በመስኩ የሚያወጡት ገንዘብ ከብዙዎች አገሮች ድርሻ ይበልጣል። ለምሳሌ በ 2003 ዓ.ም. ፎርድ፣ ዳይይለር-ክራይስለር፣ ዚመንስ፣ ቶዮታና ጀነራል ሞተርስ ለምርምርና ልማት ያወጡት ገንዘብ በተናጠል ከአምሥት ቢሊዮን ዶላር ይበልጥ ነበር።

አብዛኛውን ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ በማቅረብ አሁንም ቀደምቱን ቦታ ይዘው የሚገኙት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ አገሮች ናቸው። ግማሽ ገደማ የሚጠጋው ካፒታል የመነጨው አሜሪካን፣ ብሪታኒያንና ሉክሰምቡርግን ከመሳሰሉ ሶሥት አገሮች ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ በተለይ የእሢያ አገሮችም ጠቃሚ የውጭ ኢንቨስትመንት ምንጭ ሊሆኑ መብቃታቸው ሌላው ሃቅ ነው። ከነዚሁ አንዷ ቻይና ስትሆን አገሪቱ ገንዘብ በውጭ በሥራ ላይ እንድታውል ገፋፊ ምክንያት የሆነው ለተፈጥሮ ጥሬ ሃብት ያላት ፍላጎት እያደገ መሄድ ነው። ይህንንም ትኩረቷ በላቲን አሜሪካና በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለማት ላይ ማመዘኑ ያረጋግጣል።

የንግድና ልማቱ ተቋም ጠበብት አንዳንድ ቅድመ-ግዴታዎች ከተሟሉ ቀጥተኛው የውጭ መዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት እያደገ እንደሚሄድ ያምናሉ። የኤኮኖሚው ዕድገት ከተረጋጋና ይበልጥ ከተስፋፋ፣ መዋቅራዊ ጥገና መደረጉ ከቀጠለ፣ ትርፍ የሚገኝ ከሆነና አዲስ ገበያ መክፈቱ ካልተቋረጠ ማለት ነው። ዋናው ተግባር በታዳጊዎቹ አገሮች በራሳቸው መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ይሆናል። ከዚህ ግብ ለመድረስ ደግሞ በተሃድሶ፣ በትምሕርትና በኢንቨስትመንት ፖሊሲ ላይ ያተኮረ ቀልጣፋ፤ ሆኖም የማይጋፋ የማይጋፋ የመንግሥት ተሳትፎ በተለይ የሚጠቅም ነው።

ለመሆኑ የአፍሪቃ ሁኔታ በዚህ መስፈርት ምን ይመስላል? ሰሞኑን የተባበሩት መንግሥታት ተቋም “የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት ሚና ሲገመገም” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ በአፍሪቃ የተለየው መልክዓ-ምድራዊ፣ ታሪካዊና መዋቅራዊ ገጽታ ካፒታልን በልምድ በውጭ ንግድ ላይ ባተኮሩ፤ ከተቀረው ኤኮኖሚ ጋር ግንኙነት በሌላቸው ምርቶች ላይ ስቦ ነው የኖረው። ይህ በአንድ ወገን ላይ ያጋደለ ፖሊሲ ቀርቶ በክፍለ-ዓለሚቱ ማሕበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ ሃቅና ከልማት ችግሮች ጋር የተጣጣመ ሁኔታ ካልተፈጠረ ለውጥ ማስፈኑ የማይቻል ነገር ነው።

አፍሪቃ የበለጠ መዋዕለ-ነዋይን ለመሳብ ከፈለገች ብዙ የተሃድሶ ጥረት እንድታደርግ በተባባሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ጉባዔ ተጠይቃለች። የድርጅቱ ባልደረባ አነ ሚሮ እንደዘረዘሩት ከሆነ የሚፈለገው ብዙ ነው። የገበያው እጦት፣ መዋቅራዊው ችግር ከብዙዎቹ መሰናክሎች ጥቂቶቹ ናቸው። በ 2005 የዓለም ኢንቨስትመብት ዘገባ መሠረት ባለፈው ዓመት ከውጭው መዋዕለ-ነዋይ ወደ አፍሪቃ የዘለቀው ከሶሥት በመቶ ያለፈ አልነበረም። ከግማሽ የሚበልጠውም ከፈረንሣይ፣ ኔዘርላንድ፣ ብሪታኒያ፣ አሜሪካና ከፕሬቶሪያ የመነጨ ነበር። በግል ንብረት መስፋፋትና ለዘብተኛ ፖሊሲ የተነሣ መዋዕለ-ነዋዩ 53 ከሚሆኑት አገሮች በአርባው ማደጉን ነው ዘገባው ያመለከተው። በተቀሩት 13 አገሮች ደግሞ ማቆልቆሉ አልቀረለትም።

ችግሩ እርግጥ ይህ ብቻ አይደለም። አብዛኛው ዓለምአቀፍ ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ የሚፈስባትን ቻይናን ብንመለከት ኩባንያዎች ወደዚያ የሚዘልቁት ዕውቀትንም በማስገባት የአገሪቱን ዕድገት ለማራመድ በሚበጅ ሁኔታ በተግባር የሚሰማሩ ከሆነ ነው። በአፍሪቃ ከነዳጅ ዘይትና ሌሎች የተወሰኑ የተፈጥሮ ሃብቶች ለመጠቀም ካልሆነ በስተቀር ለሁለንተናዊው የልማት ዕድገት በሚጠቅም መንገድ ስምሪት የተደረገበት ቦታ አይገኝም። የተገኘ ጥቅም አለ ለማለትም እምብዛም አያስደፍርም።
ለግንዛቤ ያህል ባለፈው ዓመት ወደ አፍሪቃ ከተሻገረው 18 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ካፒታል በነዳጅ ዘይት ሃብት ከታደሉት አገሮች በስተቀር ወደተቀሩት አካባቢዎች የደረሰው መቶ ሚሊዮን ዶላር እንኳ አይሞላም። ይህ በጥናት የተደረሰበት ጉዳይ ነው።

እርግጥ የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር በወቅቱ ናይጄሪያንና ሱዳንን የመሳሰሉትን አገሮች ይበልጥ ማተኮሪያ ቢያደርግም ይህ አንድ-ወጥ የኤኮኖሚ ዘይቤ ለነዚህ ታዳጊ አገሮች ማሕበራዊ ልማት በረጅም ጊዜ አስተማማኝ መሆኑ ሲበዛ ያጠያይቃል። ሁል-ገብ የሆነ ኤኮኖሚን ለማስፈን መጣሩ ነው የተሻለ የሚሆነው። በመዳብ ሃብት የታደለችው ዛምቢያ ተሃድሶን ችላ በማለቷ የዚሁ ምርት ዋጋ በዓለም ገበያ እንደወደቀ ካፒታል አቅራቢዎች ገሸሽ ከማለታቸው የተነሣ የደረሰባት ውድቀት ትምሕርት ሊሆን ይገባል።

በመሠረቱ የውጭ መዋዕለ-ነዋይን በመሳብ ብሄራዊ ኤኮኖሚን ለማሳደግ መጣሩ ባልከፋም ነበር። ሆኖም ይህ ከፖለቲካ ችግሮች ተነጥሎ ሊታይ የሚችል ጉዳይ አይደለም። አገር ያፈራውን የተፈጥሮ ሃብት ለሕብረተሰብ ዕድገትና ልማት በሚበጅ መልክ ለመጠቀም ለመብቃት ፍትሃዊ የአስተዳደር ዘይቤና የሙስና ልክፍት መወገድ ይኖርበታል። አለበለዚያ የአገር ሃብትና የተፈጥሮ ጸጋ ሕዝቡን ሣይሆን ጥቂት ባለሥልጣናትና ትርፍ ፈላጊ ኩባንያዎችን በማካበት ሊቀጥል ነው። በአፍሪቃ ይህ ደግሞ-ደጋግሞ የታየና መታየት የቀጠለም ሃቅ ነው።