1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውጥረት በቡሩንዲ የምርጫ ዋዜማ

ማንተጋፍቶት ስለሺረቡዕ፣ ሰኔ 17 2007

በቡሩንዲ በአዲስ መልክ ግጭት ቢቀሰቀስም የምክር ቤት ምርጫ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚካሄድ የቡሩንዲ መንግስት አስታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ በመንግሥት እና በተቃዋሚዎችን በኩል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። የቡሩንዲ መንግሥት ግን ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደረገው ንግግር መቋረጡን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/1Fmvi
Burundi Verhandlungen zwischen Regierung und Opposition
ምስል UN

[No title]

የቡሩንዲው ፕሬዚዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን በፕሬዚዳንትነት እወዳደራለሁ ማለታቸውን ተከትሎ የተከሰተውን ቀውስ ለማርገብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጀመረው ጥረት የተሳካ አይመስልም።

ቀደም ሲል ከሁለት ሣምንታት በፊት የከሸፈውን ንግግር ለማስጀመር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቡሩንዲ ልዩ ልዑክ ሴኔጋላዊው ፖለቲከኛ አብዱላዬ ባቲሊ የተለያዩ ፖለቲከኞችን እና ተቋማትን ጋብዘው ነበር። ንግግሩን ዳግም ለማስጀመር ልዑኩ የሃይማኖት አባቶችን እና የማኅበረሰቡ ተወካዮችን ቢጋብዙም የቡሩንዲ መንግሥት ግን ራሱን ከንግግሩ እንዳገለለ ትናንት አስታውቋል። በቡሩንዲ CNDD-FDD የተሰኘው ገዢው ፓርቲ ሊቀ መንበር ፓስካል ንያቤንዳ መንግሥታቸው በንግግሩ የማይሳተፍበትን ምክንያት አስታውቀዋል።

«ፓርቲያችን በንግግሩ እንደማይሳተፍ ተወያይቶበታል። ምክንያቱም እንደሚታየው ከሆነ የዚህ ንግግር ዓላማ ምርጫውን ማወክ ነው።»

ቡሩንዲያውያን «ጊዜያቸውን ከማባከን» በምርጫው ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉ የመንግሥት ተወካዩ ተናግረዋል። ከሦስት ሣምንታት በፊት በቡሩንዲ ሊካሄድ ታቀዶ የነበረው የምክር ቤት ምርጫ ከአምስት ቀናት በኋላ የፊታችን ሰኞ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

ከፊታችን ሰኞ ሁለት ሣምንታት በኋላ ደግሞ እጅግ ሲያወዛግብ የከረመው የፕሬዚዳንት ምርጫ እንደሚኪያሄድ ተጠቅሷል። ፕሬዚዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን ለመወዳደር ማቀዳቸው የውዝግቡ ሰበብ ሆኖ ከርሟል።

የመንግስት ተቃዋሚዎች የፕሬዚዳንቱ ድርጊት ሕገ-መንግሥቱን የጣሰ ነው በሚል ምርጫው እንዳይከናወን ጥረት ሲያደርጉ መክረማቸው ይታወቃል።

የቡሩንዲ ምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ ክላቨር ንዳዪካሪ ግን ለምርጫው የሚያስፈልጉ ነገሮች ተሟልተዋል፣ ምርጫውም በታቀደለት የጊዜ ገደብ ይከናወናል ብለዋል።

«ሰኔ 22 የሚካሄደውን የምክር ቤት ምርጫን በተመለከተ ሁሉም ነገር ተጠናቋል። እንደውም ከሳምንታት በፊት ነው የተጠናቀቀው። ምርጫው ነገ ቢሆን እንኳን ዝግጁ ነን። ሁሉም ነገር ተሟልቷል። ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ጨምሮ በሀገሪቱ ሁሉም ነገሮች ዝግጁ ናቸው»

በቡሩንዲ 17 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቀደም ሲል በምርጫው እንደማይሳተፉ መግለጣቸው ይታወሳል። የምርጫ ኮሚሽኑ በይፋ በምርጫ ላለመሳተፍ ያመለከተ ፓርቲ የለም ሲል ተናግሯል። ተቃዋሚዎች የምርጫ ኮሚሽኑ እና የፍርድ ስርዓቱ ለገዢው ፓርቲ የቆሙ ናቸው ሲሉ ይወቅሳሉ።

አንድ ወር ከመንፈቅ ባስቆጠረው የቡሩንዲ ቀውስ እስካሁን 70 ሰዎች ተገድለዋል። 500 ያህል ቆስለዋል። ከ500 በላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እስር ቤት ይገኛሉ።

ማን እንደጣለው ያልታወቀ ቦንብ ባለፈው እሁድ ሰሜን ቡሩንዲ ንጎዚ ከተማ አንድ ቡና ቤት ውስጥ ፈንድቶ አራት ሰዎች ሲገደሉ፤ ቢያንስ 27 ሰዎች ቆስለዋል። የቦንብ ጉዳቱን ያደረሰው በመባባል መንግሥት እና ተቃዋሚዎች ጣት ተቃስረዋል።

የአውሮጳ ኅብረት ለግጭት ሰበብ የሚሆኑ ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ሊጥል እንደሚችል ሰኞ ዕለት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ቡሩንዲ የአመት በጀቷን አጋማሽ የምታገኘው ከአውሮጳ ኅብረት መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም እንደ ቤልጂግ እና ኔዘርላንድን የመሳሰሉት ሃገራት ለቡሩንዲ የሚሰጡትን የልማት ርዳታ ቀንሰዋል። ጀርመንም ለቡሩንዲ ትሰጥ የነበረውን የገንዘብ ርዳታ እንደያዘች ተጠቅሷል።

ያም ሆነ ይኽ የቡሩንዲ መንግሥት ምርጫው በታቀደለት መሰረት ሰኞ ከመካሄድ የሚያግደው አንዳችም ነገር የለም ሲል በተደጋጋሚ አስታውቋል።

Burundi Proteste gegen Präsident Nkurunziza Demonstration
ምስል Getty Images/AFP/J. Huxta
Bujumbura Burundi Protest Gewalt
ምስል picture-alliance/D. Kurokawa
Senegal Abdoulaye Bathily
ምስል picture-alliance/dpa/Panapress/A. Mbaye

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ