1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ ታላቁ ግድብ፤ ያላባራዉ ዉዝግብ

እሑድ፣ ታኅሣሥ 1 2010

የሁለቱ ሐገራት ሚንስትሮች እና ባለሥልጣናት የሱዳንን ጨምረዉ በተደጋጋሚ ቢነጋገሩም የካይሮ እና የአዲስ አበባ የቃላት ቴኒስ ግጥሚያ አልበረደም። የግብፅ የግድብ እና የዉኃ ሐብት ሚንስትር መሐመድ አብደል አቲ ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ግብፅ ከአባይ ወንዝ ከምታገኘዉ ዉኃ አንዲት ኩባያ እንኳ እንዲቀነስባት እንደማትፈቅድ አስጠንቅቀዋል

https://p.dw.com/p/2p2cg
ወዳጅ ናቸዉ ጠላት??
ምስል Reuters

ዉይይት፤ ታላቁ ግድብ፤ ያላባራዉ ዉዝግብ

 

የኢትዮጵያ እና የግብፅ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ በምታስገነባዉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ምክንያት ሰሞኑን አዲስ ዓይነት እንኪያ ሰላንቲያ የገጠሙ መስለዋል።እርግጥ ነዉ ኢትዮጵያ ግድብ መገንባት ከጀመረችበት ከ2003 ጀምሮ ግብፆች ተቃዉሞና ቅሬታቸዉን ማሰማታቸዉ አልቀረም ነበር።

ይሁንና ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ሲሲ በሕዝብ የተመረጡትን የግብፅ ፕሬዝደንት መሐመድ ሙርሲን በኃይል  አስወግደዉ ሥልጣን ከያዙበት ከ2005 ወዲሕ የካይሮዎች ቅሬታ፤ተቃዉሞ እና ዛቻ ጋብ ያለ መስሎ ነበር።አል ሲሲ የካይሮ መንበራቸዉን በቅጡ ካደላደሉ በኋላ አሁን የአባይን ዉኃ ማንም ሊነካዉ አይችልም ማለታቸዉ ተዘግቧል።ፕሬዝደንቱ ዉኃ ለግብፅ የብሔራዊ ደሕንነት ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዉ መንግስታቸዉ ብሔራዊ ደሕንነቱን የማስጠበቅ አቅም እንዳለዉ አስታዉቀዋል።

የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይም ተመሳሳዩን አፀፋ ስጥተዋል።ቃል አቀባይ መለስ ዓለም በቅርቡ ለጋዜጠኞች እንደነገሩት የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረዉን የግድብ ግንባታ ማንም አያስቆመዉም።

የሁለቱ ሐገራት ሚንስትሮች እና ባለሥልጣናት የሱዳንን ጨምረዉ በተደጋጋሚ ቢነጋገሩም የካይሮ እና የአዲስ አበባ የቃላት ቴኒስ ግጥሚያ አልበረደም።አል መስር አልዮም የተባለዉ የግብፅ ጋዜጣ እንደዘገበዉ፤ የግብፅ የግድብ እና የዉኃ ሐብት ሚንስትር መሐመድ አብደል አቲ ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ግብፅ ከአባይ ወንዝ ከምታገኘዉ ዉኃ አንዲት ኩባያ እንኳ እንዲቀነስባት እንደማትፈቅድ አስጠንቅቀዋል።የግብፅ የምክር ቤት እንደራሴዎች በበኩላቸዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር በቅርቡ ለምክር ቤቱ ያደርጉታል የተባለዉን ንግግር እንዳያደርጉ ለማሳገድ ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻ ጀምረዋል።

Eco@Africa - Damm
ምስል Eco@Africa

የአባይ ግድብ ወደ ሱዳን እና ግብፅ በሚፈሰዉ የዉኃ መጠን ላይ የሚያደርሰዉን ተፅዕኖ እንዲያጠና የተሰየመዉ ተቋም የደረሰበት የጥናት ዉጤም ግብፅና ኢትዮጵያን አላግባባም ነዉ የተባለዉ።

ኢትዮጵያ ግድቡን፤ ግብፅ ዉኃዉን የሕዝብ ብሔራዊ ሥሜት መቀስቀሻ ማድረጋቸው በግልፅ እየታየ ነዉ።በየጋዜጦቹ፤ በተለይም በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተካረሩ አስተያዮቶችን እያነበብን ነዉ።ያሁኑ እንኪያ ሰላንቲ ትክክለኛ ምክንያቱ፤ መዘዙ እና የመጨረሻ ዉጤቱ የዛሬ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ልደት አበበ