1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣቶችና ሽብር በማሊ

Eshete Bekeleሐሙስ፣ ኅዳር 16 2008

ፓሪስ በሽብር ከተናወጠች ጥቂት ቀናት በኋላ የማሊ ዋና ከተማ ባማኮም ተመሳሳይ እጣ ገጥሟታል። በባማኮ በሚገኝ ቅንጡ ሆቴል ላይ በተፈጸመው ጥቃት በትንሹ 19 ሰዎች ተገድለዋል። ለጥቃቱ አል-ሙራቢቱን የተሰኘ ጽንፈኛ የታጣቂዎች ቡድን ኋላፊነቱን ወስዷል።

https://p.dw.com/p/1HD9v
Mali Geiselnahme Hotel in Bamako
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Traore

[No title]

ዓለም አንዳች የሽብር ጥቃት ሳትሰማ ውላ ማደር የተሳናት ይመስላል። የሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች፤ጋዜጣና መጽሔቶች አሰቃቂ የሽብር ጥቃቶችን ይዘግባሉ። ከጥቂት ሳምንታት በፊት በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ማሊ ዋና ከተማ በሚገኝ ሆቴል ላይ የተፈጸመው የሽብር ጥቃትም አንድ ሰሞን መገናኛ ብዙሃንን ጉድ ያሰኘ ወሬ ሆኖ አልፏል። ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደው አል-ሙራቢቱን መሰል ታጣቂዎች በምዕራባውያን ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት ወጣት ወንዶችና ሴቶች እንዲቀላቀሉ ልባቸውን ለማሸፈት ጥረት ከጀመሩ ሰነባብቷል።ብራም ፖስቱመስ በምዕራብ አፍሪቃ የዶይቼ ቬለ ወኪል ነው።

«ማሊ ሐብታም አገር አይደለችም። ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግርም አለ። ኑሮም እጅግ አስቸጋሪ ነው። ጽንፈኛ የሆነው የእስልምና አተረጓጎም በርካታ ሰዎችን ወደ መስጊድ በተለይም የዕለተ-አርብ ጸሎት እንዲሄዱ እያደረጋቸው ነው። ከእነዚህ መካከል ጥቂት ሰዎች በዚህ ጽንፈኛ በሆነው አዲስ አተረጓጎም እየተማረኩ ነው። በነገራችን ላይ ይህ አዲስ አተረጓጎም በመላው ምዕራብ አፍሪቃ እስልምና ዘንድ ተቀባይነት የለውም።»

Mali Geiselnahme Hotel in Bamako
ምስል Imago

ብራም ፖስቱመስ ሥራ አጥነትና ተስፋ ማጣት የገፋቸው የማሊ ወጣቶች ወደ አውሮጳ መሻገር አሊያም ኮት ዲቯርን ወደ መሳሰሉ ጎረቤት አገራት መሰደድን እንደ አማራጭ እንደሚወስዱ ይናገራል።።በዚያው በአገራቸው አነስተኛ ስራዎችን የሚሞክሩ የመኖራቸውን ያክል ጥቂቶች ወንጀለኛ ይሆናሉ። የማሊ መንግስት ባለስልጣናት የጽንፈኛ ታጣቂዎች ዒላማ የሆኑትን ወጣቶች ለመታደግ የሬዲዮ ቅስቀሳዎችን ያደርጋሉ። ብዙ የማሊ ወጣቶች ግን ሽብርተኝነት መጥፎ ነው ተብለው እንዲነገራቸው አይፈልጉም።ምክንያቱም ይላል-ብራም ፖስቱመስ «አብዛኛዎቹ የማሊ ወጣቶች አስቀድመው ስለሚያውቁት ሽብርተኝነት መጥፎ መሆኑ እንዲነገራቸው አይፈልጉም። የማሊ መንግስት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከፈረንሳይና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ ይደረግለታል። ወጣቶች ሽብርተኝነትን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የማሊ መንግስት ዋንኛ ትኩረት የአገሪቱን ዳር ድንበር በማስጠበቁና ሰሜናዊውን የአገሪቱን ክፍል ማረጋጋት ነው።»

ከአንድ አመት በፊት በኬንያው የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ በፓሪስ የተፈጸሙት የሽብር ጥቃቶች ዒላማ ያደረጉት ወጣቶችን ነበር። አብዛኛዎቹ ጥቃት ፈጻሚዎችም በዚሁ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ሶፋን የተሰኘው የዩናይትድ ስቴትስ የጸጥታና የደህንነት ጥናት ተቋም ይፋ ባደረገው ዘገባ «እስላማዊ መንግስት መስርቻለሁ» የሚለውን ታጣቂ ቡድን መሰል ጽንፈኞችን የሚቀላቀሉ ወንዶች አማካኝ እድሜ ከ18-29 እንደሆነ አትቷል። ሽብር አብዝቶ በሚያሰጋት ማሊ የሚታየው የሙዚቃና የውይይት ባህል ወጣቶችን ከሚታደጓቸው ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ብራም ፖስቱመስ ተናግሯል።

Ansar Dine Kämpfer in Mali
ምስል Romaric Hien/AFP/GettyImages

«ከወጣቶች ለወጣቶች የሚተላለፉ መልዕክቶችን ለማግኘት በማሊ በተለይም በዋና ከተማዋ ባማኮ በከፍተኛ ቁጥር የሚገኙት የራፕ ሙዚቀኞች መመልከት አስፈላጊ ነው። በወጣቶች አስተሳሰብ ላይ ከፍ ያለ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በራሳችሁ ልታፍሩ አይገባም የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ፤ ከ1, 000 ዓመት በላይ የቆየውን የማሊ ታሪክ ለዛሬ ወጣቶች በማስተዋወቅ ሚና ይጫወታሉ። ሌላው ሁሉም ሰው በቤቱ ሬዲዮ አለው። የውይይት፤ የሃሳብ ልውውጥ እና የስልክ መሰናዶዎችን ያዳምጣሉ። በስተመጨረሻ ይነጋገራሉ። በባማኮ በሚገኝ ማንኛውም የመኖሪያ ሰፈር ሻያቸውን ፉት እያሉ እስከ ውድቅት ለሌት ድረስ ከጸሐይ በታች ስላለ ማንኛውም ነገር ሲጨዋወቱ ያመሻሉ። »

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ