1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣቱ ተመራማሪ በጀርመን ዩኒቨርሲቲ

ዓርብ፣ የካቲት 1 2005

ወጣት ቴዎድሮስ ደበበ ይባላል። እዚህ ጀርመን ሀገር የመጣው ከሳንባ ውጪ ተደብቆ የሚገኝ ቲቢን ፈልጎ የሚያጋልጥ የሕክምና መሳሪያ የሚፈለሰምበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው። 3 ዓመታት የሚዘልቀውን የቤተ-ሙከራና የመስክ ጥናት ለማካሄድ ጀርመን ከገባ ሶስት ወራትን አስቆጥሯል። ታዲያ በእዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በጀርመንኛ ቋንቋ መግባባት ሁሉ ጀምሯል።

https://p.dw.com/p/17aYh
Campus am Augustusplatz in Leipzig. Copyright: Swen Reichhold/Pressestelle der Universität Leipzig
Architektur der deutschen Universitäten Uni Leipzigምስል Swen Reichhold/Pressestelle der Universität Leipzig

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተመራማሪነት አገልግሏል ወጣት ቴዎድሮስ ደበበ። አሁን ደግሞ የዶክትሬት ማዕረግ ሊያሰጥ የሚችለውን ምርምር ማለትም ፒ ኤች ዲውን ለመቀጠል እዚህ ጀርመን ሀገር ይገኛል። የቋንቋ ትምህርቱን የሚከታተለው ቦን ከተማ ውስጥ ነው። ያነጋገርኩት ግን አማካሪ ፕሮፌሰሩን ለማነጋገር ወደ ፊት ምርምሩን የሚያካሂድበት ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበት የላይብዚሽ ከተማ ሄዶ ሳለ ነው።

የቲቢ ተህዋስያን በማጎሊያ መነፅር
የቲቢ ተህዋስያን በማጎሊያ መነፅርምስል picture-alliance/dpa

የወጣት ቴዎድሮስ ጥናት የሚያተኩረው በዚህ ከሣንባ ውጪ በሚገኘውና ፈልጎ ለማግኘት እጅግ አስቸጋሪ በሆነው ቲቢ ዙሪያ ምርምር ማካሄድ ላይ ነው። በተለይ በኢትዮጵያና እያደጉ ባሉ ሀገራት ውስጥ ከሳንባ ውጪ የሚገኝ ቲቢን ፈልጎ ለማግኘት እጅግ አዳጋች ነው። ወጣቱ ተመራማሪ ያብራራል።

ወጣቱ እዚህ ከፍተኛ ትጋትን የሚጠይቅ ምርምር ላይ ለመሳተፍ ከማመልከቱ አስቀድሞ በርካታ ጥረቶችን አድርጓል። ፓስተር ኢንስቲትዩት ፈረንሳይ ሀገር ውስጥ በሚሰጠው የክትባት ስልጠና ላይ ባለፈው ዓመት ተካፍሏል። ከዚያም ወደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመልሶ ከሳንባ ውጪ የሚገኝ ቲቢን የሚመረምር መሳሪያ እንዲሁም ክትባቱን ለማግኘት ታላቅ አስተዋፅኦ ሊያደርግ የሚችል የጥናት ዕቅድ ነደፈ። ጀርመን ሀገር ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተፃፃፈናም ላይብዚሽ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ጥናቱን ለመቀጠል ዕድሉን አገኘ። ቴዎድሮስ «የሰው ልጆች ወደ እዚች ምድር ስንመጣ ያለምንም ምክንያት አይደለም» ሲል ይቀጥላል።

በእርግጥም ተግባራዊ ጥረት ካላከልንበት በስተቀር ማንኛውም ነገር ምንም ያህል ጊዜ በጥልቀት ደጋግመን ብናስብት በራሱ ጊዜ አንዲት ጋትም ቢሆን ፈቅ አይልም። ለዚያም ነው እዚህ ጀርመን ሀገር ሲመጣ አንድም የጀርመንኛ ቃል የማያውቀው ወጣት ቴዎድሮስ በሶስት ወራት ያላሰለሰ ጥረት ብቻ በቋንቋው መግባባት ደረጃ የደረሰው። በእርግጥ መጀመሪያ ላይ አውሮጳ ሲደርስ ከተቀበለው ቀዝቃዛ የዓየር ጠባይ ባሻገር የማያውቀው ባህልና የቋንቋ ችግር ተደማምረው ተስፋ ወደ መቁረጡ ደረጃ አዳርሰውት ነበር።

የቲቢ ክትባት ምርምር
የቲቢ ክትባት ምርምርምስል picture-alliance/dpa

ወጣቱ ያን ሁሉ ውጣ ውረድ አልፎ አሁን ከሁሉ ነገር ጋር የተላመደ ይመስላል። እዚህ አውሮጳ የገና ሰሞን የተመለከተው የከተማ ገበያዎች በመብራቶች አሸብርቀው መታየታቸውና የህብረተሰቡ እንቅስቃሴ ያስገረመውን ያህል፤ የሰሞኑ የካርኒቫል ማለትም የፈንጠዝያ ባህሉም ሳያስደምመው አላለፈም። ከዚያ ሁሉ ባሻገር ግን ለሶስት ዓመት ግድም የሚዘልቀው ምርምሩን በትጋት ለመቀጠል ከወዲሁ ወገቡን ጠበቅ ማድረግ እንዳለበት ተረድቷል።

ወጣት ቴዎድሮስ ጥናት እና ምርምሩ ሰምሮለት ለእራሱም ለሀገሩም የሚጠቅመውን መሣሪያ እንዲፈለስም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ እየተመኘን ከወዲሁ እንሰናበታለን።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ