1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ የመን የቀጠለዉ ስደት

ረቡዕ፣ ኅዳር 21 2009

በጦርነት ወደምታመሰዉ የመን የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የተመ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አመለከተ። ከቀጠለዉ ግጭት እና የከፋ የሰብዓዊ ሁኔታ በተቃራኒ ካለፈዉ ጥር እስከያዝነዉ ኅዳር ወር ድረስ ከአንድ መቶ ሺህ የሚበልጡ ከአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ የፈለሱ ተሰዳጆች የመን መግባታቸዉን ድርጅቱ ትናንት ይፋ ባደረገዉ መግለጫ ጠቅሷል።

https://p.dw.com/p/2TWie
Jemen Zerstörung
ምስል Reuters/A.Mahyoub

(CMS) UNHCR HA migrants - MP3-Stereo

በዚህ ጊዜ ዉስጥ ብቻም ቢያንስ 79 ሰዎች ወደ የመን ሲጓዙ ሞተ ባህር ዉስጥ ሰጥመዉ ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል።

የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR በተጠቀሰዉ ጊዜ ዉስጥ ግጭት ወደጠናባት የመን ከገቡት ተሰዳጆች አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ መሆናቸዉን ነዉ ያመለከተዉ። 90 ሺህ ገደማ። 17 ሺዎቹ ደግሞ ከሶማሊያ ነዉ የተሰደዱት። የዚህ ዓመቱም ሆነ ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ወደ የመን የገቡት ከ90 ሺህ በላይ ተሰዳጆች የዛሬ 10 ዓመት ከነበረዉ ጋር ሲነፃፀርም ግጭቱና የፀጥታዉ ስጋት በተባባሰበት ወቅት የተሰደዱት በብዙ ሺዎች በልጠዋል። ያኔ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2006ዓ,ም ማለት ነዉ ወደ የመን የተሰደዱት 25 ሺህ 898 ነበሩ UNHCR እንደመዘገበዉ። ከኢትዮጵያም ሆነ ከሶማሊያ የሚሰደዱት ወገኖች ከጅቡቲዋ የወደብ ከተማ ኦቦክ፣ ከፑንትላንዷ ቦሳሶ እንዲሁም ከሶማሊያ በመነሳት ቀይ ባህርን ወይም የኤደን ባህረ ሰላጤን በአደገኛ ሁኔታ አቋርጠዉ ነዉ የመን የሚገቡት። አማን ዮርዳኖስ የሚገኙት በUNHCR የየመን ቃል አቀባይ ሻቢያ ማንቱ የመን ለረዥም ጊዜ የስደተኞች መስህብ ሆና መቆየቷን ይናገራሉ።

«ከምሥራቅ አፍሪቃ ለሚሰደዱ እና ጥገኝነት ለሚፈልጉ ሰዎች የመን ታሪካዊ መዳረሻ ሆና ቆይታለች። ይህ ለግማሽ ምዕተ ዓመት የነበረ ነዉ፤ ቁጥሩም ቢሆን የአሁኑ ግጭት ከመጀመሩ በፊትም እየጨመረ መጥቷል ። አሁን ባለዉ የግጭት ሁኔታ ደግሞ እየጨመረ መሄዱ እየታየ በመሆኑ የበለጠ ትኩረትና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነዉ። ምክንያቱም በዚህ መካከል ለአደጋ እና ጉዳት የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነዉ። ይህ ከዚህ ቀደም አልነበረም።»

UNHCR-Logo
ምስል UNHCR

UNHCR እና ሌሎች ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ከአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ በአደገኛ የጉዞ ሁኔታ ወደ የመን የሚደረገዉ ስደት አሳሳቢ መሆኑን በተደጋጋሚ ያመለክታሉ። አደገኛዉን የባህር ላይ ጉዞ ፈፅመዉ የብስ የሚረግጡት ስደተኞችም በግጭት የሚተራመስ አካባቢ ከመግባታቸዉ በተጨማሪ ለተለያዩ ጥቃቶች እና የጉልበት ብዝበዛ እንደሚጋለጡም ያሳስባሉ። UNHCR በመግለጫዉ እንዳመለከተዉ አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት የተፈፀመባቸዉ፤ ምግብና ዉኃ የተከለከሉ፤ በግዳጅ ገንዘብና ንብረታቸዉን የሚቀሙ፣ ቁም ስቅል የሚፈፀምባቸዉ እና በሕገ ወጥ ሰዉ አዘዋዋሪዎች የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ የሚደረጉ እንዳሉ መረጃዎች ደርሰዉታል። በዘፈቀደ የሚታሠሩ፣ ተይዘዉም ተገደዉ ወደመጡበት የሚባረሩ መኖራቸዉን መስማቱንም አመልክቷል። በየመን ለረዥም ጊዜ የቀጠለዉ ግጭትም ቨህገወጥ ሰዎችን ከሀገር ወደ ሀገር ለሚያሸጋግሩትም ሆነ አስፈራርተዉም ሆነ አስገድደዉ ለሚዘርፉት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቅሷል። ወደ የመን ከገቡት አብዛኞቹ ኢትዮጵያዉያን እንደመሆናቸዉ ለስደት ያበቃቸዉ መሠረታዊ ምክንያት ተጣርቶ እንደሆን ለቀረበላቸዉ ጥያቄ ሻቢ ማንቱ ሲመልሱ፤

«እዉነት ነዉ አብዛኞቹ የመጡት ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ነዉ። ከ88ሺህ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ፤ 17 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ የሶማሊያ ዜጎች ናቸዉ። የስደታቸዉ መሠረታዊ ምክንያት በየመን በኩል አልፈዉ በባህረ ሰላጤዉ አረብ ሃገራት አካባቢ የኤኮኖሚ ዕድል የመፈለግ ወይም ከሀገራቸዉ ግጭትም ሆነ ክስ ሸሽተዉ በየመን ከለላ ለመፈለግ ነዉ። እዚያ የደረሱትን አዳዲስ መጪዎች የመመዝገብና የትኞቹ ጥገኝነት እንደሚፈልጉ የማጣራት ሥራዎችን ቀጥለናል። ነገር ግን በጉዞ ላይም ሆነ አንዴ የመን ከገቡ በኋላ ስለሚያጋጥማቸዉ ያለዉ መረጃ በጣም ዉሱን ነዉ።»

እንደ UNHCR አብዛኞቹ ወደ የመን የሚሰደዱ ወገኖች አንድም ተታለዉ ነዉ አንድም ስለ የመን የወቅቱ የፀጥታ ይዞታ በቂ መረጃ የላቸዉም። ካለፈዉ ዓመት መጋቢት ወር አንስቶ የፕሬዝደንት አብደረቦ ማንሱር ሃዲን መንግሥት ከሁቲ አማፅያን ጥቃት ለመከላከል በሳዉድ አረቢያ መሪነትየሚካሄደዉ የአየር ጥቃት የመን ዉስጥ በቋፍ የነበረዉን የፀጥታ ይዞታ አባብሶታል። በግጭቱም ከ7 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች አልቀዋል፤ ከሦስት ሚሊየን በላይ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸዉ ተፈናቅለዋል። በተባባሰዉ የየመን ግጭት እዚያ ለሚገኙ ተሰዳጆች የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የሚያደርገዉ ነገር ይኖር ይሆን? ሻቢያ ማንቱ፤

Anja Niedrighaus Preis 2016, Foto von Adriane Ohanesian
ምስል A. Ohanesian

«UNHCR ከለላ እና ጥገኝነት የሚፈልጉትን መርዳቱን እንደቀጠለ ነዉ። አዲስ ከሚመጡት መካከል በትክክል ከለላ የሚያስፈልጋቸዉን እየለየን፤ ተገቢዉን ርዳታ ማግኘታቸዉን እናረጋግጣለን። እንዲያም ሆነ በየመን ያለዉ ሁኔታን አዳጋች ቢያደርገዉም ሰዎች ስለሁኔታዉ እንዲያዉቁ ለማድረግ በጥንቃቄ እና በንቃት በመንቀሳቀስ ሰዎች ተገቢዉ መረጃ እንዲደርሳቸዉ እያደረግ ነዉ።» 

የመን ዉስጥ በቀጠለዉ ግጭት ጦርነት ምክንያት 80 በመቶ የሚሆነዉ የሀገሪቱ ዜጋ ሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ ሆኗል። ይህም ሀገሪቱ ተጨማሪ ስደተኞች የማስተናገድ አቋሟን ማሟጠጡ UNHCR አመልክቷል። የመን የምትገኝበትን ይህን ቀዉስ ባለማወቅ ወደዚያ የሚሰደዱትን ወገኖችን ለማስገንዘብም ድርጅቱ መዘጋጀቱን ሻቢያ ማንቱ ገልፀዋል።

«ወደ የመን የሚሰደዱት ሰዎች ወይ ስለወቅቱ ሁኔታ ትክክለኛ መረጃ የላቸዉም ወይም ደግሞ በሕገወጥ አሸጋጋሪዎች እና በወንጀለኞች የግንኙነት ሠንሰለት ተታለዉ ነዉ ሊሆን የሚችለዉ። ስለዚህ ከሚቀጥለዉ ወር ጀምረን የየመንን የወቅቱ ሁኔታ ምን እንደሚመስል የሚያስረዳ መረጃ ለማሰራጨት አቅደናል።»

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ