1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወላጆችን ያለማወቅ ችግርና የኋላ መዘዙ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 25 2005

የማታውቃት ወላጅ እናቷ ከአጠገቧ ሆና፣ የማታውቃቸው እህት ወንድሞቿም አብሮ አደጎቿ ሆነው ለአስርት ዓመታት ኖራለች። ወጣቷ በማደጎ ነው ያደገችው። የዛሬው የወጣቶች ዓለም መሰናዶ «የአስተዳደር ችግርና የኋላ መዘዙ» በሚል ርዕስ ነዋሪነቷን በሊባኖስ ቤሩት ያደረገች የአንዲት ኢትዮጵያዊት ወጣትን ታሪክ ያስደምጠናል።

https://p.dw.com/p/18RZM
ምስል Getty Images/AFP
Discover Ashrafieh Sasin Platz
ምስል DW

አብሮ አደግ ጓደኞቿ እሷ ባታውቀውም እህት ወንድሞቿ ሆነው ከአጠገቧ አፈር ፈጭተው አድገዋል። በእድሜ የገፉት የማደጎ እናቷ ደግሞ «ከቤተክርስቲያን ደጃፍ ተጥለሽ አገኘሁሽ» እያሉ ቢያሳድጓትም ቅሉ ወላጅ እናቷን «ጎረቤቴ» እያለች ለዓመታት ኖራለች። ሆኖም ይህ ሁሉ ምስጢራዊነት ወጣቷ ትዳር ከመሰረተችና ልጆች ካፈራች በኋላ ድንገት በቅርቡ ይፋ ሆኗል። የአስተዳደጓ ውስብስብነት ከማኅበረሰቡ ጋራ የነበራትን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ትዳሯንም አመሳቅሎታል። ወጣቷን አሁን የምትኖርበት ሊባኖስ ቤሩት ስልክ ደውዬ አናግሬያታለሁ፤ ታሪኳን ታጫውተናለች። «የአስተዳደግ ችግርና የኋላ መዘዙ» የዛሬው የወጣቶች ዓለም መሰናዶ ርዕስ ነው፤ አብራችሁን ቆዩ።

ሁለት ልጆች አሏት። ወንዱ 8 ዓመቱ ሲሆን፤ ሴቷ ደግሞ ስድስት ዓመት ከመንፈቅ ሆኗታል። ወጣቷ ዓረብ አገር ሊባኖስ ቤሩት ውስጥ ተቀጥራ መስራት ከጀመረች 5 ዓመታት ተቆጥረዋል። እንደ በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለወጣቷ የሁለት ልጆች እናት ኑሮ በአረብ አገር አስቸጋሪነቱ እንዲህ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። «እማ፤ መቼ ነው ግን ከአጠገባችን ሳትርቂ አብረን የምንኖረው?» የልጆቿ ተደጋጋሚ ጥያቄ ነው። ወጣቷ ግን ጥያቄውን እንዲህ እንደዋዛ መፍታት የምትችለው አይነት አይመስልም። የህይወት ምስቅልቁ ገና ከማለዳው ነውና የጀመራት።

ለመሆኑ የእዚህች ወጣት ቤተሰቦች ለዓመታት ከአጠገቧ ሳይርቁ፤ በተለይ ወላጅ እናቷ ማንነታቸውን ደብቀው መኖሩን ለምን መረጡ? «ጓደኛዬ» የምትላት እህቷ «እናቴ» እያለች በእናቷ እቅፍ ስር ስታድግ ወጣቷ ስለምን ለማደጎ ተሰጠች? መልሱን ወደ በኋላ ላይ ከእራሷ ከወጣቷ አንደበት እንሰማለን።  

ወጣቷ ኑሮን አሸንፋለሁ ብላ ከአምስት ዓመታት በፊት ቤሩት ብትገባም ህልሟ ግን ዛሬም ድረስ ሊሳካ አልቻለም። የአረብ አገር ኑሮው እንደው «ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ» አይነት ነገር ሆኖ ዛሬም ድረስ ያባትታት፣ ይፈትናት ይዟል።

እስኪ አሁን ደግሞ ትንሽ ወደ ኋላ እንመለስ። ወጣቷ ማኅበረሰቡ የሚያደርስባትን መገለል ተቋቁማ  እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ዘለቀች። ከእዛ በላይ ግን መቀጠል አልቻለችም። በመሀከል ትዳር መሰረተች። የባለቤቷ ቤተሰቦች ወጣቷን «ማንነቷ፣ ምንጩዋ የማይታወቅ» ሲሉ በመንቀፍ ትዳሩን በፍፁም ሊቀበሉ አልፈለጉም። ልጃቸው ለትዳሩ የሚያወጣው ወጪ ላይ ሳይቀር ማንገራገር አበዙ።  እናም በሂደት ባለቤቷ ቤተሰቦቹ ጋራ የሚሰራውን ስራ ለቆ ወጣ።



የእዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ መንስኤው ወላጆቼን ያለማወቋ እንደሆነ ትገልፃለች ወጣቷ። ወላጆቻቸውን ሳያውቁ በማደጎ አለያም በአሳዳጊ ስር የሚኖሩ ልጆችና ወጣቶች ቁጥር በኢትዮጵያ ምን ያህል እንደሆነ በውል ባይታወቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን እየጨመረ እንደሆነ ይጠቀሳል። ታዲያ እነዚህ ልጆች ከማኅበረሰቡ ጋራ የሚኖራቸው መስተጋብር ምን ያህል በተፈተና የተሞላ እንደሆነ ማወቁ የሚያዳግት አይመስለኝም።  የሚገጥማቸው ከባድ የስነልቦና ቀውስም እንዲህ በቀላሉ ተገልጾ የሚታለፍ አይደለም።


«የአስተዳደግ ችግርና የኋላ መዘዙ» በሚል ርዕስ ትዳርና ሁለት ልጆቿን በትና በአረብ አገር የምትንከራተት የአንዲት ኢትዮጵያዊት ወጣት ታሪክን ያስደመጥንበት የወጣቶች ዓለም መሰናዶ በዚህ ይጠናቀቃል።  ዝግጅቱን በድጋሚ  የፌስቡክ አድራሻችን ውስጥ ታገኙታላችሁ፤ ገብታችሁ ተወያዩበት። መልካም ጊዜ፤ ጤናይስጥልኝ!
 

ምዕራብ ቤሩት ሐማራ የተሰኘው ሰፈር
ምዕራብ ቤሩት ሐማራ የተሰኘው ሰፈርምስል DW/M. Naggar

ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ ከፈለጉ ከታች ያለውን የድምፅ ምልክት ይጫኑ።


ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ