1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃዋሚዎች የውይይቱ መንፈስ “አዋጁን ተቀበሉ ነው” ሲሉ ተችተውታል

ረቡዕ፣ ኅዳር 21 2009

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው የኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ዛሬ ሰብስቦ አነጋግሯል፡፡ በስብሰባው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሾች ቢሰጡም ከውይይት እና ዘላቂ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ “አዋጁን ተቀበሉ“ የሚል መንፈስ ነበረው በሚል ተችተውታል፡፡

https://p.dw.com/p/2TXGl
Äthiopien Tote bei Anti-Regierungs-Protesten in Bishoftu
ምስል DW/Y. Gegziabher

Command Post meet with Opposition Parties FINAL - MP3-Stereo

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ ኮማንድ ፖስቱ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና ተወካዮች ጋር ያደረገው የግማሽ ቀን ስብሰባ የተካሄደው በተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ነበር፡፡ “ስብሰባው የተጠራው አንዳንድ የፓለቲካ ፓርቲዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ባቀረቡት ጥያቄ ነው” ሲል የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት ለፓርቲዎቹ በበተነው የጥሪ ደብዳቤ ላይ ጠቅሷል፡፡ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ አብዛኞቹ ፓርቲዎችም በስብሰባው ላይ መገኘታቸውን በቦታው የነበሩ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል፡፡

ስብሰባው የተመራው በመከላከያ ሚኒስትር እና የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት አቶ ሲራጅ ፈጊሳ ነው፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያረቀቁ ባለሙያዎች በአስረጅነት ተገኝተው ነበር፡፡ ባለሙያዎቹ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዝርዝር ገለጻ አድርገዋል፡፡

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ጥሪ ደርሷቸው በስብሰባው ላይ ከተገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አንዱ ናቸው፡፡ በኮማንድ ፖስቱም ሆነ በተቃዋሚዎች በኩል በስብሰባው የተነሱ ጉዳዮች ምን እንደነበሩ እንዲህ ያስረዳሉ፡፡

“በእነርሱ በኩል ገለጻ የተደረገው ኮማንድ ፖስቱ እና የጊዜያዊ አዋጁ ለምን እንዳስፈለገ፣ ምን ጉዳዮች እንደነበሩ እና በአጠቃላይ አዋጁን ነው ገለጻ ያደረጉት፡፡ የተነሱት ጉዳዮች በጠቅላላው መንግስት የተጠየቀው የህዝብን ጥያቄ ራሱን በማደራጀት በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ኮማንድ ፖስት ማቋቋሙ ምንድነው ጥቅሙ? ምን ያስገኛል? አሁን መንግስት ያቋቋመው በዘላቂነት ይህንን ችግር ይፈታዋል ወይ? የህዝብን ጥያቄ ይመልሳል ወይ? አግባብነቱ ምንድነው?” የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸውን ይናገራሉ፡፡

“[በአዋጁ] ምክንያት የተነሳ ብዙ ሰው በየቦታው እየታሰረ ነው፡፡ ለታሰሩት ደግሞ አፋጣኝ የሆነ መልስ አልተሰጠም፡፡ በትክክል ወንጀለኞች ናቸው የተባሉት በሙሉ ፍርድ ቤት አልቀረቡም፡፡ በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ነው የሚገኙት እና ጠቀሜታው ምን ድረስ ነው? ለዘለቄታው ለዚህች ሀገር የሚጠቅመው እና ሰላምን ለማምጣት ምን ያህል አስተማማኝ ነው? የሚሉ እና የመሳሰሉት የመብት ጥያቄዎች ናቸው የተነሱት” ሲሉ የስብሰባውን መንፈስ ያስረዳሉ፡፡  

“የአስቸኳይ ጊዜ ባይደነገግ ኖሮ በሀገሪቱ ውስጥ ትልቅ ብጥብጥ ይፈጠር እንደነበር እና መንግስትን እሰከማናጋት ሊደርስ እንደሚችል” ለጥያቄዎች በተሰጠ ምላሽ መገለጹን አቶ ሙላቱ ይናገራሉ፡፡ አዋጁ ባይታወጅ ኖሮ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ህልውና ራሱ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችል እንደነበር ማብራሪያ መሰጡትንም ተናግረዋል፡፡

Äthiopien Anti-Regierungs-Protesten
ምስል REUTERS/T. Negeri

“ሰላም አሰፍኗል” በሚል በኮማንድ ፖስቱ ተደጋግሞ የተሞካሸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ስብሰባውን የጠሩት መሞከራቸውን አቶ ሙላቱ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን በውይይቱ በሁለቱም ወገኖች የተነሱት ጉዳዮች እልባት ሳይበጅላቸው ስብሰባው መጠናቀቁን ይገልጻሉ፡፡

“ሁለቱም [ወገን] ያለው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ እያንዳንዱ የራሱን ሀሳብ ይዞ እንደወጣ ነው የተረዳሁት፡፡ እንድ መግባቢያ ወይም ነጥብ ላይ ደርሰን ይሄ ነው ብለን የወጣንበት ነገር የለም፡፡ ገለጻ ተደረገ፣ ጥያቄ ተጠየቀ፣ ይሄ ነው ተቀበሉት አይነት ነገር ነው እንጂ አዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኑን ቁጭ ብለን ለማየት [አልቻልንም]፡፡ ለመጠየቅ ብዛትም ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሁሉም ለጥያቄው መልስ ያገኘ አይመስለኝም” ይላሉ አቶ ሙላቱ፡፡   

በስብሰባው በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች እንደነበሩ ቢነገርም የአዋጁን መደነገግ የተቃወሙ ግን ላለመገኘት ወስነው ቀርተዋል፡፡ በፓርቲ አመራሮች ዘንድ በተፈጠረ የመሪነት ውዝግብ ውስጥ የሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ በስብሰባው ላይ እንዲገኝ ተጋብዞ እንደነበር ደብዳቤውን የተቀበሉት አቶ ይልቃል ጌትነት ይናገራሉ፡፡ “በሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበርነት በምርጫ ቦርድ ዘንድ የምታወቀው እኔ ነኝ፤ ከኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያትም ደብዳቤ ውሰዱ የሚል ጥሪ የደረሰው ለእኔ ነው” የሚሉት አቶ ይልቃል በስብሰባው ላለመገኘት መምረጣቸውን እና ምክንያታቸውን ያስረዳሉ፡፡

“በአጠቃላይ ይህ ነገር አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን አንዳስፈላጊ ነገር አድርገው ባፈጻጸሙ ላይ ማብራሪያ የመስጠት አይነት ዝንባሌ ያለው መንፈስ ሆኖ ስላገኘሁት እኔ ደግሞ በመሰረቱ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ስገመግመው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው በአንድ ሀገር ልዩ ጦርነት፣ ድርቅ፣ ረሃብ እና ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ነገሮች ሲፈጠሩ ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ነገሮች አልፎ አልፎ አንዳንድ ቦታዎች እንኳ ቢኖሩ ከአካባቢ ፖሊስ እና ከደንብ አስከባሪዎች ያለፈ ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል ምንም ዓይነት ነገር ስለሌለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁ በራሱ ትክክል አይደለም፤ ተገቢ አይደለም ብዬ ስላማምን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመቀበል መሄድ በጉዳዩ ላይ እንደማመን ስለሚቆጠር ስብሰባው ላይ አልተገኘሁም” ብለዋል፡፡

የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት ጽህፈት በስብሰባው ዙሪያ ማብራሪያ ለመስጠት ፍቃደኛ መሆኑን የገለጸ ቢሆንም የሚመለከተውን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብንደውልም ምላሽ የሚሰጠን ማግኘት አልቻልንም፡፡

ተስፋለም ወልደየስ 

ኂሩት መለሰ