1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ክዋሜ ንክሩማህ

ሐሙስ፣ ጥር 10 2010

ክዋሜ ንክሩማህ ነጻ እና የተባበረች አፍሪቃን በማለማቸው ብሎም ጋና ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ተላቃ ነጻነቷን እንድታውጅ ባደረጉት የመሪነት ተጋድሎ ክብርን ተጎናጽፈዋል። ኾኖም ሕይወታቸው በድል ብቻ የተሞላ አይደለም። ከዐሥር ዓመት ግድም የሥልጣን ቆይታ በኋላ በወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ሲወገዱ ጋናውያን ፈንጥዘዋል።

https://p.dw.com/p/2r61j
DW African Roots- Kwame Nkrumah
ምስል Comic Republic

የንኩሩማህ ታሪክ እነሆ!

ሽቅብ በሚንፏለለው ሰው ሠራሽ ፏፏቴ መሀል የጋና ውድ ልጅ፤ የክዋሜ ንክሩማህ መካነ-መቃብር መዲናይቱ አክራ ውስጥ በጉልኅ ይታያል። ግዙፉ የመቃብር ቤት ለኚህ አፍሪቃዊ ፈርጥ የሚመጥን መታሠቢያ ነው። 

ጽሑፍ: ጎልድ ኮስት ተብላ በምትጠራው የብሪታንያ ቅኝ ግዛት ተወለዱ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1930ዎቹ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል ንክሩማህ መርከብ ውስጥ ተደብቀው ተጓዙ፤ ከዚያም ወደ ብሪታንያ አቀኑ። በእነዚህ 12 ዓመታት ውስጥ ንክሩማህ ውጭ ሀገር በሚገኙ የአፍሪቃ ፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል። በ1947 ዓ.ም. ወደ ሀገር ቤት በመመለስም ለቅኝ-ግዛት አስተዳደሩ ራስ ምታት ኾኑ።  ከዐሥር ዓመት በኋላ ንክሩማህ ነጻ በወጣችው አዲሲቱ ጋና የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚንሥትር በመኾን፤ በ1960 ዓ.ም. የሀገሪቱን የመጀመሪያ የፕሬዚዳንት በትረ-ሥልጣን ጨበጡ። ይኽ ለንክሩማህ በቂያቸው አልነበረም ይላሉ በክዋሜ ንክሩማኅ ዩኒቨርሲቲ የሣይንስ እና ሥነ-ቴክኒክ ክፍል የታሪክ መምሕርቷ ዶክተር ቪልሔልሚና ዶንኮር።  

"ክዋሜ ንክሩማህ ለጋና ብቻ በማይለውና ለመላው አፍሪቃ በቆመው ርእያቸው ልዩ አለያም አቻ አልባ ነበሩ። ለዚያም ነበር ከመላው የአኅጉሪቱ ነጻ መውጣት ጋር ካልተሰናኘ በስተቀር የጋና ነጻነት ምሉዕ አይደለም የሚለውን ዝነኛ ንግግራቸውን በ1957 ዓ.ም. ያሠሙት።"

DW African Roots- Kwame Nkrumah
ምስል Comic Republic

ይኽ ለአንዲት አፍሪቃ የተቀነቀነ ርእያቸውም ነበር ክዋሜ ንክሩማህን በአኅጉሪቱ እና ከአኅጉሪቱ ውጪ ዝናን ያጎናጸፋቸው። ኾኖም አንዳንዶች ይኽ ዝና ንክሩማህ የቤታቸውን ጣጣ እንዲዘነጉ አድርጓቸዋል ብለው ያምናሉ። በእርግጥ ሥልጣን በያዙ በመጀመሪያዎቹ ሰሞን የጋና ኢንዱስትሪን ለማነቃቃት ያደረጉት ጥረት ተስፋ ሰጪ መስሎ ቢታይም ቅሉ፤ በ1966 ዓ.ም. በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ሲነሱ ለሀገሪቱ የተዉላት ነገር ቢኖር የሚንፏቀቅ ምጣኔ ሐብትን እና አንዳች ማምረት ያልቻሉ ውድ ፋብሪካዎችን ነበር። የፖለቲካ ታሪክ ተመራማሪ እና ጋናዊ ፖለቲከኛው ፕሮፌሠር ማይክ ኦቁዋይ የንክሩማህ ዘመን ምን ይመስል እንደነበር እንዲህ መለስ ብለው ያስታውሳሉ።   

"የንክሩማህ ዘመን ከማክተሙ በፊት ምንድን ነበር የኾነው? ለስኳር ፍጆታ እደላ በሚል በስታዲየም ውስጥ እንሰልፍ አልነበረም፤ ያስ እውነት አይደለም? እውነት ነው፤ ፋብሪካዎቹም ቢኾኑ የሚሠሩ አልነበሩም፤ ምክንያቱም መራመድ ከመቻላችን አስቀድሞ ሩጫውን ተያይዘን ነበራ። እናም ሰዉ ዝም ብሎ ርእይ ርእይ ርእይ ብቻ ባይል ይበጃል።"

ክዋሜ ንክሩማህ በአፍሪቃ ይፋለሙ የነበረው ቅኝ ግዛትን ብቻ አልነበረም፤ ካፒታሊዝምን ጭመር እንጂ። የአፍሪቃውያን ባሕሎችን እና ማኅበረሰባዊ ፍትኅን በሚያዋህድ ለየት ያለ የአፍሪቃ ሶሻሊዝም ላይም ጠንካራ እምነት ነበራቸው። ኾኖም ንድፈ-ሐሳብን ወደ ተግባር መተርጎም ቀላል አይደለም። ክዋሜ ንክሩማህ በገዛ ሀገራቸው ፖለቲካን የተመለከቱበት መነጽር በጽሑፍ ካቀረቡት ሶሻሊዝም ጋር የሚጣረስ ነበር። ይኽ መጣረስም እንደ ታሪክ ምሑሯ ቪልሔልሚና ዶንኮር ከኾነ የጋና መሥራች አባት ክዋሜ ንክሩማህ ጉዳይን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ እንኳን ትኩረት የሚስብ ርእሰ-ጉዳይ አድርጎታል።  

"ክዋሜ ንክሩማህ በኹለት ጉዳዮች ትኩረት የሚስቡ መሪ ነበሩ። በአንድ በኩል፦ ስለ ሶሻሊዝም እና ሌሎች ጉዳዮች በርካታ ስብከቶችን ያሰሙ ይመስላል። እውነታው ግን የሚያሳየው የፖለቲካ መርኆዋቸው በአጠቃላይ የግድ በሶሻሊስት ርእዮተ-ዓለም ሙሉ ለሙሉ የተቃኙ ነበሩ ማለት እንዳልኾነ ነው። ለእኔ ያ እጅግ በጣም ትኩረት የሚስብ ነው።"

DW African Roots- Kwame Nkrumah
ምስል Comic Republic

ከጋና ውጪ፤ ክዋሜ ንክሩማህ ይበልጥ ስማቸው የሚዘከረው የአፍሪቃ ኅብረት የፖለቲካ አስተሳሰብን ስኬታማ ለማድረግ ባደረጉት ጥረት ነው። 

"ወደ ነጻነት እንገስግሳ፤ አኹኑኑ ወደ ነጻነት። ነገ ደግሞ ወደ ተዋሃደች አፍሪቃ።"

ይኽ ርእይ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1999 ዓ.ም. የአፍሪቃ ኅብረት እንዲመሠረት በማድረግ በከፊልም ቢኾን እውን ኾኗል። ያኔ ክዋሜ ንክሩማህ ከመሥራች አባቶቹ እንደ አንዱ ተወድሰዋል።  

ኢሳቅ ካሌዲች/ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ 

 ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አንድ አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.