1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ክትባት ቢገኝ አፍሪካ መሸመት ትችላለች?

ረቡዕ፣ ሐምሌ 15 2012

​​​​​​​አሜሪካን ጨምሮ የናጠጡት አገራት በሙከራ ላይ ከሚገኙ 23 የኮሮና ክትባቶች ተስፋ ሰጪዎቹን ጠቀም አድርገው በማዘዝ አስቀድመው እጃቸው ለማስገባት በመሯሯጥ ላይ ይገኛሉ። ይኸ የበለጸጉ አገራት ጥረት በሙከራ ላይ የሚገኙት ክትባቶች ፍቱንነት ቢረጋገጥ እንኳ በፍትሐዊነት ለደሐዎቹ የመዳረሱን ጉዳይ አጠራጣሪ አድርጎታል።

https://p.dw.com/p/3feyJ
Corona Impfstoff wird gestestet.
ምስል picture-alliance/SvenSimon/F. Hoermann

ፍቱን የኮሮና ክትባት ቢገኝ አፍሪካ መሸመት ትችላለች?

በዓለም ዙሪያ በሙከራ ላይ ከሚገኙ በርካታ የኮሮና ክትባቶች መካከል በብሪታኒያው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና አስትራዜኔካ የተባለ የመድሐኒት አምራች ኩባንያ እየዘጋጀ የሚገኘው "በሰው ላይ ጉዳት የማያደርስ እና የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያዳብር" ሆኖ በመገኘቱ ተስፋ ሰጪ ሆኗል። ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ክትባቱ በ1,077 ሰዎች ላይ ተሞክሮ በ56 ቀናት ውስጥ ጠንካራ የመከላከል አቅም መገንባት ችሏል።

ሳይንቲስቶች ባለፈው ሰኞ ግኝታቸውን የሕክምና ምርምሮች ይፋ በሚደረጉበት ዘላንሴት የተባለ ጆርናል ለሕትመት አብቅተዋል። በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የጀነር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አድሪያን ሒል በሰው ላይ ጉዳት የማያደርስ እና የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያዳብር ሆኖ በመገኘቱ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር አድሪያን ሒል "ከ1000 ሺሕ በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ከተደረገው ሙከራ በኋላ የክትባቱ ደሕንነት ጥሩ እና አስተማማኝ መሆኑን አረጋግጠናል። ትልቁ ጉዳይ ደግሞ ክትባቱ በተሞከረባቸው ሁሉም ሰዎች ላይ ጥሩ በሽታ የመከላከል ምላሽ ተመልክተናል" ሲሉ ተናግረዋል። 

በመፅሔቱ ይፋ የሆነው የምርምር ውጤት ተባባሪ ጸሀፊ ሳራ ጊልበርት "ክትባታችን ስኬታማ ከሆነ እንዲህ አይነት ክትባቶች በብዛት ሊመረቱ ስለሚችሉ ተስፋ ሰጪ ምርጫ ነው" ብለዋል። ይፋ የተደረገው የምርምር ውጤት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ሳይንቲስቶቹ እንዳሉት ዕድሜያቸው የገፉትን ጨምሮ በሌሎች ሰዎች ላይ የክትባቱ ፍቱንነት ሊሞከር ይገባል።

የክትባቱን ፍቱንነት እና ደሕንነት ከማረጋገጥ ባሻገር በሚፈለገው መጠን ማምረት ኹነኛው ፈተና ነው። እንደ ፕሮፌሰር አድሪያን ሒል ያሉ ባለሙያዎች የኮሮና ወረርሽኝን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በርከት ያሉ ፍቱን ክትባቶች ያስፈልጋሉ የሚል አቋም አላቸው። 

"ሁለት ቢሊዮን ክትባቶች እንኳ በቂ ላይሆኑ ይችላሉ። ይኸን ያክል ማዘጋጀት ከቻልን እጅግ በጣም ትልቅ ስኬት ነው። በአንድ አመት ግማሽ ቢሊዮን ክትባት ተሰርቶ አያውቅም። ስለዚህ ሌሎች ክትባቶች ስኬታማ እንዲሆኑ እንፈልጋለን። ሥራውን እና ሸክሙን እንዲጋሩን እንፈልጋለን" ይላሉ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የጄነር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር አድሪያን ሒል።

በእርግጥ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በርካታ አገራት እና ተቋማት የየራሳቸውን ክትባት ለማዘጋጀት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ የጤና ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ማይክ ራየን እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በሰው ላይ ሙከራ የተጀመረባቸው 23 እጩ ክትባቶች ይገኛሉ። በአፍሪካ እስካሁን የአንድ ክትባት ሙከራ በሰው ላይ ተጀምሯል።

ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በመተባበር በክትባት ፍለጋው በመሳተፍ ላይ የሚገኘው አስትራዜኔካ የተባለ የብሪታኒያ እና ስዊድን ኩባንያ ነው። ባለፈው ሰኞ የክትባት ሙከራው ተስፋ ሰጪ መሆኑን የሚጠቁመው መረጃ ይፋ ከሆነ በኋላ በዓለም ገበያ የአስትራዜኔካ የአክሲዮን ድርሻዎች ዋጋ በ1% ጨምሯል።

UK Uni Oxford meldet Durchbruch bei Corona-Impfstoff | AstraZenec
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና አስትራዜኔካ ሙከራ ላይ የሚገኘው ክትባት ከአምስት ወራት በኋላ ሥራ ላይ ሊውል ይችላልምስል picture-alliance/dpa/A. Grant

ብሪታኒያ አስቀድማ 100 ሚሊዮን ክትባቶች አዛለች። ጃፓን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን እና ኔዘርላንድስ በተለያየ መጠን ይኸንን ክትባት እጃቸው ለማስገባት ከአስትራዜኔካ ተመሳሳይ ስምምነት ፈጽመዋል። ስፔን፣ ብራዚል እና ቻይናን የመሳሰሉ አገሮች ተመሳሳይ ፍላጎታቸውን ገልጸው ከኩባንያው መነጋገር ከጀመሩ ሰነባበቱ። አር-ፋርም የተባለው የሩሲያ መድሐኒት አምራች ኩባንያ ይኸንንው ክትባት በሩሲያ ለማምረት ከአስትራዜኒካ ሥምምነት መፈራረሙን ባለፈው ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም አረጋግጧል።

የኮሮና ተሕዋሲ ክትባት ቅርምት

የበለጸጉት አገራት ለኮሮና ክትባት ቅርምት የጀመሩት ገና ደሕንነታቸውና ፍቱንነታቸው ሳይረጋገጥ ነው። ፖለቲከኞች እና የማሕበረሰብ ጤና ባለሙያዎች ፍቱን የኮሮና ተሕዋሲ ክትባት በፍትኃዊነት ሊዳረስ ይገባል የሚል አቋም ቢኖራቸውም እስካሁን ያለው ዓለም አቀፍ አሰራር ደሐ አገራትን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ የናጠጡት የሚፈልጉትን እጃቸው እንዲያስገቡ ሊያደርግ ይችላል።

ፖለቲከኞች፣ የመድሐኒት እና የጤና ኩባንያ መሪዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጫና ካልተደረገ የኮሮና ክትባቶች ፍቱንነታቸው ተረጋግጦ ሥራ ላይ እንዲውሉ ሲፈቀድ የናጠጡ አገራት ዜጎቻቸውን አስቀድመው ለመከተብ ክትባቶቹን ሊያከማቹ እንደሚችሉ አክቲቪስቶች ያስጠነቅቃሉ። 

በተለይ አሜሪካ በቅርቡ የኮሮና ሕሙማንን ለማከም የሚያገለግለው ሬምደስቪር የተባለ መድሐኒት በከፍተኛ መጠን ከሸመተች በኋላ በርካቶች ስኬታማ ክትባት ሲገኝ በዓለም ገበያ የከፋ የክትባት ግብይት ቅርምት ሊመጣ ይችላል የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል። አሜሪካ ለሶስት ወራት የሚሆን የሬምደስቪር መድሐኒት ሙሉ በሙሉ የገዛችው ባለፈው ሰኔ 2012 ዓ.ም መጨረሻ ነበር። አሜሪካ የኮሮና ሕሙማንን በፍጥነት ለማገገም የሚያግዘውን መድሐኒት ጠቅልላ ስትሸምት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሐ አገራት ቀርቶ ለአውሮፓ እና ሌሎች ያደጉ አገራት እንኳ ያስተረፈችው አልነበረም። 

አሁን በሙከራ ላይ የሚገኙትን እና ገና ፍቱንነታቸው ያልተረጋገጠውን ክትባቶች እንደ ብሪታኒያ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ ያሉ አገራት በሚሊዮኖች በማዘዝ እጃቸው ለማስገባት እያደረጉ ያለው ጥረት ይኸንንው ሥጋት አጠናክሮታል። ሥጋቱ ከሚጫናቸው መካከል የኦክስፋም ኢንተርናሽናል የጤና ፖሊሲ አማካሪዋ አና ማሪዮት ይገኙበታል።

"ትልቁ ፍርሐታችን የመድሐኒት አምራች ኩባንያዎች የዚህን ወረርሽኝ የሕክምና መፍትሔዎች ያለ በብቸኝነት ከተቆጣጠሩ ከኩባንያዎቹ ጋር የሁለትዮሽ የግዢ ውል የመፍጠር አቅም ባላቸው የናጠጡት አገራት መካከል የጨረታ ጦርነት የምናይበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ ምክንያት የክትባቶች እና መድሐኒቶች አቅርቦት በተወሰኑ አካላት እጅ ይወድቃል። በመላው ዓለም የሚኖረው አቅርቦትም ፍትኃዊ መሆን አይችልም" ሲሊ አና ማሪዮት አስጠንቅቀዋል።

አፍሪካ ምን ማድረግ ትችላለች?

ፍቱን የኮሮና ክትባት ብቁ ሆኖ ሥራ ላይ እንዲውል ሲፈቀድ የአፍሪካ ኅብረት ሥርጭቱ በአምራቾች እና በኩባንያዎች መካከል በሚደረግ የተናጠል ድርድር ከሚከወን ይልቅ አኅጉር አቀፍ ሥርዓት እንዲኖረው ይሻል። 

የአፍሪካ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ንኬጋሶንግ እንዳሉት የተናጠል ሙከራ ክፋት ባይኖረውም አፍሪካ ግን በተቀናጀ መንገድ ክትባቱን ለማግኘት የምትችልበት መንገድ ያሻታል።

ዶክተር ዶክተር ጆን ንኬጋሶንግ ዳይሬክተር "በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ላድርግ። አምራቾች በተናጠል ከአገሮች ተደራድረው ከሚያቀርቡላቸው ይልቅ አኅጉራዊ የሆነ ማዕቀፍ እንዲኖረው እንፈልጋለን። የተለያዩ አገሮች ወይም አምራቾች የሚያደርጉትን ጥረት መቆጣጠር አንፈልግም። ይሁንና አቅርቦቱ የተቀናጀ መሆን አለበት" ሲሉ ከአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ አሳስበዋል። 

Blutprobe für Covid-19 Coronavirus Test im Labor
በዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ የጤና ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ማይክ ራየን እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በሰው ላይ ሙከራ የተጀመረባቸው 23 እጩ ክትባቶች ይገኛሉምስል picture-alliance/Zoonar/R. Kneschke

የአውሮፓ ምክር ቤት እና የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራቶች ፓርቲ አባል የሆኑት ፒተር ሊዘ "አውሮፓ ማንኛውንም ነገር ከተቀረው ዓለም መጋራት ትፈልጋለች" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ሊዘ ይኸን ያሉት የኮሮና መድሐኒቶች ወይም ወደፊት ሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉ ክትባቶች ፍትኃዊ ግብይት መነጋገሪያ በሆነበት በዚህ ወቅት ነው።

"አውሮፓ ክትባቱን እና የክትባቱን አሰራር ለተቀረው ዓለም ለማጋራት ዝግጁ የምትሆን ይመስለኛል" ያሉት ፒተር ሊዘ አሜሪካ ጠቅልላ የገዛችው ሬምደስቪር የተባለ መድሐኒት አመራረትንም ቢሆን ከባለቤቱ ጊሊያድ ሳይንስ የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ፈቃድ ሳይጠየቅ የሚመረትበትን መንገድ የአውሮፓ ኅብረት እንደሚፈልግም ገልጸዋል። እንዲህ አይነቱ አሰራር ለጥናት እና ምርምሩ ወጪ የሚያደርጉት ገንዘብ ለማይኖራቸው የአፍሪካ አገሮች የተስፋ በር ሊሆን ይችላል።

የአፍሪካ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ንኬጋሶንግ "በማንኛውም አገር ስኬታማ ሊሆን የሚችል ወይም ፍቱን እንደሚሆን የተረጋገጠ ክትባት ከተገኘ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ፈቃድ በመቀበል በአፍሪካ የሚገኙ የክትባት ኩባንያዎች እንዲያመርቱ እያበረታታን ነው። ዛሬ ፍቱን የሆነ አንድ ክትባት ቢኖር 7.8 ቢሊዮን ሰዎች ይፈልጉታል። ስለዚህ በተቻለ መጠን ክትባቱ በአንድ ቦታ ሳይገደብ በብዙ ቦታ ሊመረት ይገባል። ይኸን ክትባት ማምረት የሚችሉ ኩባንያዎች በአፍሪካ እንዳሉ እንተማመናለን" ብለዋል።

John N. Nkengasong Afrika Africa Centres for Disease Control
የአፍሪካ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ንኬጋሶንግምስል Getty Images/M. Tewelde

ጋቪ የተባለው ዓለም አቀፍ የክትባት አቅርቦት ጥምረት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሴዝ በርክሌ አሁን ያለው ሥርዓት ደሐ አገሮች ከናጠጡት ዕኩል ክትባት የማግኘት ዕድል እንደማይፈጥርላቸው ያምናሉ። ተቋማቸው እንደ ቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ያሉ የግብረሰናይ ድርጅቶች ፤ለጋሾች እንዲሁም እንደ የዓለም የጤና ድርጅት እና የሕፃናት መርጃ ድርጅት ያሉ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማትን በማጣመር የተቋቋመ ነው። በደሐ አገሮች የሚካሔዱ የክትባት መርሐ ግብሮችን ማመቻቸት፤ ማስተባር እንዲሁም እንደ ፖሊዮ እና ኩፍኝ ያሉ በሽታዎች እንዲጠፉ ለመሥራት የተቋቋመ ነው። የዓለም የክትባት ግብይትንም ሆነ ሥርጭት ጠንቅቀው የሚያውቁት ዶክተር ሴዝ ታዲያ በመጪዎቹ ጊዜያት ሥራ ላይ ሊውል የሚችል የኮሮና ተሕዋሲ ክትባት በፍትሐዊነት ለድሆቹ ሊደርስ የሚችልበት መንገድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

"በአሁኑ ወቅት የሁለትዮሽ ስምምነት ለሌላቸው በማደግ ላይ ለሚገኙት፤ መካከለኛም ይሁን ከፍተኛ ገቢ ላላቸው አገራት ክትባት የለም። ይኸን ችግር ለመቅረፍ እየሞከርን ነው። ይኸን ችግር ለመፍታት እኛ እያልን ያለንው ምንድነው- ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ክትባቱ ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገራት ዕኩል ሊያገኙ ይገባል። ይኸን ማድረግ ፍትኃዊ ነው። ከእነዚህ አገሮች ተገናኝተን በጉዳዩ ላይ እንወያያለን። ከአምራቾቹ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ኖሯቸው ክትባቱን የማግኘት ዕድል ያላቸው አገራት በእኔ እምነት ከሰልፉ ኋላ ሔደው መሰለፍ አለባቸው" ብለዋል።

ክትባት በትብብር

የኮሮና ክትባቶችን በበቂ መጠን አምርቶ ለዓለም አገራት በፍትሐዊ መንገድ የመሰራጨቱ ነገር የሚያሳስበው የዓለም ጤና ድርጅትን ጭምር ነው። ዶክተር ማይክ ራየን ከወደ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተሰማው ዜና ቢያስደስታቸውም ዓለም በሚፈልገው መጠን አምርቶ ማሰራጨቱ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ባለፈው ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረው ነበር። ቢሆንም ዶክተር ሚካኤል በጋቪ በኩል ክትባቶችን በመግዛት እና በማከፋፈል በአገሮች መካከል ፍትሐዊ የሥርጭት ሥርዓት ለመዘርጋት የታቀደበትን የኮቫክስ ሥርዓት ተስፋ አድርገዋል።

"ክትባቶች ፍቱን መሆናቸው ተረጋግጦ ሥራ ላይ እንዲውሉ ከተፈቀደ በኋላ ፈተናው በዓለም ዙሪያ ያለውን ፍላጎት ለመሙላት በሚፈለገው መጠን ማምረቱ ነው። ይኸ በራሱ ትልቅ ጥያቄ ነው። በብሪታኒያ፣ በአውሮፓ ኅብረት እና በአሜሪካ ይኸን እንቅፋት ለመቅረፍ የተለያዩ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የክትባቶች ዝግጅት እና ሥርጭትን ለማፋጠን የተዘረጋው መርሐ ግብር አካል የሆነው የኮቫክስ አሰራር አለ። ይኸ ክትባቶችን ቀድሞ በመግዛት እና በማከፋፈል በአገሮች መካከል ፍትሐዊ የክትባት ሥርጭት ሥርዓት ለመዘርጋት የታቀደ ነው። አሁን ባለበት ቁመና ግን በዓለም ላይ ለሁሉም ክትባት ማቅረብ አይችልም" ሲሉ ተናግረዋል። 

Schweiz PK Michael Ryan WHO
በዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ የጤና ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ማይክ ራየንምስል picture-alliance/Keystone/S. Di Nolfi

በዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ የጤና ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ማይክ ራየን "ክትባቶች ለአገልግሎት ዝግጁ ሲሆኑ መጀመሪያ ማን የትኛውን ክትባት ያገኛል የሚለውን መለየት አለብን። ክትባቶች በፍትሐዊ መንገድ መሰራጨታቸውን ለማረጋገጥ በዓለም ጤና ድርጅት እና አጋሮቹ ውስጥ የሚገኙ ባልደረቦቻችን ተገቢ የክፍፍል ሥርዓት ለማበጀት በርትተው እየሰሩ ነው" ሲሉ አክለዋል። 

ዶክተር ማይክ የኮሮና ክትባት ፍትሐዊ ሥርጭትን ለማረጋገጥ የዓለም አገራት ኮቫክስ የተባለውን ጥምረት እንዲቀላቀሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። እርሳቸው እንዳሉት ይኸ ጥምረት አገራት "የኮሮና ክትባትን ለመላው የሰው ልጅ በፍትሐዊነት ለማከፋፈል በሚደረገው ጥረት የሚፈጠሩ ሥጋቶችንም ሆነ ትርፉ ለመጋራት" ያስችላል።

ባለፈው ግንቦት መጨረሻ የተመሠረተው ኮቫክስ (Gavi Advance Market Commitment for COVID-19 Vaccines) አምራቾችን በገንዘብ በመደገፍ በቂ ክትባቶች ተመርተው በማደግ ላይ ያሉ የሚባሉት ደሐ አገሮችም ከናጠጡት ዕኩል የኮሮና ክትባት እንዲያገኙ ለማድረግ የታቀደ ነው። በመጀመሪያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በማሰባሰብ በጋቪ ድጋፍ በሚደረግላቸው አገሮች የጤና ሰራተኞችን እና ተጋላጭ ሰዎችን ለመከተብ ታቅዷል። ከ150 በላይ አገራት በዚሁ ሥርዓት ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሆነዋል።      

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ