1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬንያ፤ ናይሮቢ በተቃዉሞ ተንጣለች

ዓርብ፣ ሐምሌ 15 1997

የኬንያ ፓርላማ የህገ መንግስት ረቂቅ ዉይይቱ ላይ ህዝቡን አላሳተፈም በሚል መነሻ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በመቶዎች የሚቆጠር ለተቃዉሞ ሰልፍ የወጣዉ ህዝብ ከፓሊስ ጋር ግጭት ፈጥሯል።

https://p.dw.com/p/E0jk

ከማክሰኞ ጀምሮ ከተማዋን ሰላም ያሳጣትን ይህን የህዝብ ተቃዉሞ ለመግታት የመንግስት ፓሊሶች እየጣሩ ቢሆንም እንደሰልፉ አስተባባሪዎች አስተያየት ከሆነ ተቃዉሞዉ የሚቆም ሳይሆን ቀጣይነት ይኖረዋል። በግጭቱም የተጎዱ ሲኖሩ ፓሊስ ጥቂቶቹን ማሰሩ ታዉቋል።
ፓርላማዉ የህዝቡን ህገ መንግስት በማርቀቅና በማፅደቅ ሂደት የመሳተፍ መብት ቀምቷል፤ ሃሳባቸዉም እነሱ እንደፈለጋቸዉ ቆራርጠዉ ማንም የማይቀበለዉ ህግ ህዝቡ ላይ መጫን ነዉ።
አሰራራቸዉም ብትፈልግ ተቀበል ባትፈልግ ተወዉ ዓይነት ነዉ። ለዚህ ነዉ ህዝቡ ተቆጥቶ መብቱን ለማስከበር ሰላማዊ ሰልፍ የወጣዉ ይላሉ ንዶሎ አሳሳ የህዝብ ንቅናቄ የተሰኘ ሲቪክ ቡድኖችን ያሰባሰበ የመብት ተቆርቋሪዎች ማህበር ተጠሪ።
ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ወደፓርላማዉ በማምራት የተቃዉሞ የጋራ ፊርማቸዉን ለህግ አዉጪዉ አፈጉባኤ ለማቅረብ ሃሳብ ነበራቸዉ።
በዚህ መሃል አድማ በታኝ ፓሊስ የብረት ኮፍያ፤ የድንጋይ መከላከያና አስለቃሽ ጭስ በመያዝ መንገዳቸዉን ዘግቶ አላሳልፍ አላቸዉ።
ይህ የእኛ ህገ መንግስት ነዉ! ፓርላማ አትንካዉ! የሚልና ሌሎች ድርጊቱን የሚያወግዙ መፈክሮች የያዙት እንባ የሚተናነቃቸዉ ሰልፈኞች በመጀመሪያ ወደፓሊስ ዋና መስሪያ ቤት በመሄድ ሰላም እንፈልጋለን በማለት መፈክር አስተጋብቷል።
ከፓሊስ ጋር ግጭት የተቀሰቀሰዉ ከዚህ ሂዱ አንሄድም ከሚል ንትርክ በኋላ ሲሆን ፓሊሶቹ ዉሃና አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመዉ ለመበታተን ሞክረዋል። በዚህ አጋጣሚም 5ተቃዋሚዎች በፓሊስ ተይዘዉ ከታሰሩ በኋላ ማምሻዉን መለቀቃቸዉ ታዉቋል።
የፓርላማ አባል የሆኑትና የኬንያ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነዉ የኬንያ አፍሪካ ብሄራዊ አንድነት በምህፃረ ቃሉ ካኑ ፓርቲ አባል ዊልያም ሩቶ ለጋዜጠኞች እንደገለፁት ኬንያዉያን መብታቸዉ የሆነዉን ከመጠየቅ የሚያስቆማቸዉ ምንም ዓይነት የፓሊስ ኃይል አይኖርም።
በመሰረቱ ህጉ ለፓርላማዉ የቀረበዉ ረቂቁን አይቶ እንዲቀበለዉ ወይም ዉድቅ እንዲያደርገዉ ነዉ። ሆኖም የፓርላማዉ አባላት ህዝቡን ከግምት ሳያስገቡ በጋራ ረቂቅ ህጉን ፓርላማዉ እንዲያሻሽል መስማማታቸዉ የህዝቡን ቁጣ ቀሰቀሰ በማለትም አስረድተዋል።
ኬንያ ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ቀንበር ከተላቀቀች ጊዜ ጀምሮ መሪዎቿ ከመጠን ያለፈ ስልጣን እየያዙ ህዝቡን ሲያስጨንቁ የኖሩባት አገር ናት።
ይህ የኬንያ የአሁኑ መንግስት ወደስልጣን ለመዉጣት ቅስቀሳ በሚያካሂድበት ወቅት ስልጣን ከያዘ በ100 ቀናት ዉስጥ ህገ መንግስቱን እንደሚያሻሽል ቃል ገብቶ ነበር።
ወደስልጣን ለመዉጣትም የበቃዉ ለለዉጥ ዝግጁ በነበረዉ አመቺ ሁኔታ ተጠቅሞ ነበር። ሆኖም ስልጣንን ለሁለት ዓመታት ከቀመሰዉ በኋላ ስለጣፈጠዉ እንዳይወርድ ፍርሃት አደረበት በማለት የተቹት የሂዩማንራይትስዎች ጠበቃ ናጋንግ ቲዎንጎ ናቸዉ።
አካሄዱን በመቃወም ፓርላማዉን ከዚህ አልፈህ አትሂድ በማለት አደባባይ የወጣዉ ህዝብም ከፓሊስ ጋር ግጭት ፈጥሯል።
ማክሰኞ የጀመረዉ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ትናንትም በመቀጠሉ ቢያንስ 5 ሰልፈኞችና አንድ የፓሊስ አዛዥ መጎዳታቸዉ ተገልጿል።
ከተጎዱት መካከልም አንዱ በጣም መጎዳቱ ሲነገር ሌሎች ስምንት ሰዎች ደግሞ ታስረዋል።
የኬንያ ቀይ መስቀል አንድ ተቃዋሚ ሰልፈኛ ጭንቅላቱ ላይ ክፉኛ መጎዳቱን ሲገልፅ ሌሎች ሶስት የደረሰባቸዉ ጉዳት መጠናኛ መሆኑን አስታዉቋል።
በግርግሩ ወቅት ወደመሃል ከተማ ድንጋይ እየወረወሩ ይጓዙ የነበሩትን ተቃዋሚ ሰልፈኞች አድማ በታኞችና የፓርላማ ፓሊሶች በጋራ በመሆን በአስለቃሽ ጭስና ወደሰማይ በመተኮስ ሊበታትኗቸዉ ሞክረዋል።
CNN ምስል አስደግፎ እንደዘገበዉም ፓሊስ በቆመጥ ሰልፈኞቹን ክፉኛ ሲደበድብ ታይቷል።
ፓሊስ እንደሚለዉ ድንጋይ በመወርወር ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ ሰልፈኞች በወንጀል የሚጠየቁ ሲሆን ባጠቃላይ ሰልፈኞቹ ፈቃድ ሳይሰጣቸዉ በመዉጣታቸዉ ህገ ወጥ ለሆነዉ ተግባራቸዉ ተጠያቂ ይሆናሉ።
ማክሰኞ የተጀመረዉ ይህ የተቃዉሞ ሰልፍ ሳምንቱን ይቀጥላል ባይናቸዉ አስተባባሪዎቹ። ፓእራማዉ የህዝቡን ኃይል እስኪረዳ ድረስ ይላሉ የህዝቡን እርምጃ አጠናክረን በመቀጠል ሊያደርጉ ያሰቡት እናሰናክላለን።