1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ካስትሮ፤ ለና በኢትዮጵያ ዘንድ

ሰኞ፣ ኅዳር 19 2009

«እኛ የጠላነዉ፤ ላጭር ጊዜም ቢሆን መሸነፋችንን በመገመት ነዉ።» «መሸነፋችንን።» ይሕቺ ቃል   ጦርነቱ የኢትዮጵያ-የሶማሊያ ብቻ ሳይሆን የኩባና የሶማሊያ፤የደቡብ የመንና የሶማሊያ መሆኑንም አረጋገጠች።ይሕቺ ቃል ጦርነቱ የሶቭየት ሕብረትና የዩናይትድ ስቴትስ፤ የሶሻሊስቱና የካፒታሊስቱ ዓለም ጦርነት፤ የቀዝቃዛዉ ጦርነት አካል መሆኑን አረጋገጠች።

https://p.dw.com/p/2TOp0
Kuba | Trauer um Fidel Castro
ምስል Getty Images/AFP/N. Duarte

ካስትሮና ኢትዮጵያ



በ1977 ኢትዮጵያ በድርቅ ተመትታ ዜጎችዋ በረሐብ ሲያልቁ «እኛ» አሉ-አሉ-ያኔ ሐቫና የነበሩ ኢትዮጵያዉያን «ለኢትዮጵያዉን የምንለከዉ ስንዴ የለንም፤ ቢኖረንም በቂ አይደለም።የምንልከዉ ግን አለን።ደማችንን።» እና የመጀመሪያዉ ሆነዉ ለኢትዮጵያ የሚላክ ደም ሰጡ። ፊደል ካስትሮ ሩዝ። አርብ ማታ አረፉ። 
                          
የትንሺቱ አፍሪቃዊት ሐገር ኬፕ ቬርዴ ፕሬዝደንት ዮርግ ካርሎስ ፎንሴካ «ግርማ ሞገስ» የተላበሱ እና አወዛጋቢ» መሪ አሏቸዉ ካስትሮን ባለፈዉ ቅዳሜ። የግዙፊቱ፤ የሐብታሚቱ፤ የዓለም አድራጊ ፈጣሪቱ የዩናይትድ ስቴትስ የ50 ዘመን ጠላት ሆነዉ አዋዛጋቢ የማይበሉበት ሰበብ፤ ምክንያት በርግጥ ሊኖር አይችልም።ለአብዛኛዉ ኩባዊ ግን ተወዳጅ፤ ቆራጥ፤ ፅኑ ጅግና፤ ደግና አዛኝ መሪ ነበሩ።ኩባ ለተማሩ ኢትዮጵያዉን ደግሞ ኢንጀር ደረጀ እሸቴ እንደሚሉት አባት ነበሩ።አቶ ዝናዉ ተሰማ አከሉበት።
                     
የቀድሞ ባልደረባዬ፤የቅርብ ወዳጄም ጋዜጠኛ ተፈሪ ለገሰ ካስትሮን እንደ ሐገር መሪ፤ እንደባለሥልጣን ወይም እንደ ታላቅ «አንቱ» አይላቸዉም።እንደ አባት ይወዳቸዋልና።እንደ ሩቅ ሰዉ በሁለተኛ ስማቸዉ አይጠራቸዉምም።በጣም ያቀርባቸዋልና።ፊደል-ይላቸዋል።ካስትሮን።ነፃ ኩባ፤ ነፃ፤ የተማረ፤ ጤናማ፤ ጠንካራና ሰላማዊ  ኩባዊ ካለ ካስትሮ አይታሰብም ነበር።
                           
ኩባ ትንሽ ደሴት ናት።የ11 ሚሊዮኖች ሐገር።ደሐ ናት።ረጅም ጊዜ የፀናዉ የዩናይትድ ስቴትስ ተደጋጋሚ ማዕቀብ፤ የሶቭየት ሕብረት መፈረካከስ፤ የኮሚንስቱ ዓለም መዳከም ሲታከልበት ድሕነቱ ጠንቷል።ተርባ ግን አታዉቅም።ማሐይም ዜጋ የላትም።በሕክምና እጦት የሚሞት ኩባዊ የለም።
አብዛኞቹ የደቡብ አሜሪካ ሐገራት የነገሰዉ የአደንዛዥ ዕፅ ንግድና ነጋዴ፤ ዘረፊ፤ ማጅራት መቺ፤ ገዳይ ለኩባዉያን  በመገናኛ ዘዴ  ከሚሰሙት የጎረቤት ሐገር ዜና ባለፍ አያዉቁትም። የጥቁር ነጮች ግጭት፤ ንቀት፤ ቁጭትን ኩባዉያን ከዩናይትድ ስቴትስ በሚሰራጭ ዘገባ  እንጂ በገቢር አያዉቁትም።ኩባ ማይም ዜጋ የላትም።ያልተማረ-የሚባለዉ ዘጠነኛ ክፍል ነዉ።ተፈሪ ለገሰ የካስትሮና የባልደረቦቻቸዉ የሥራ ዉጤት ይለዋል። ለኢትዮጵያዉን ፍቅር።                               
                               
ፍቅር፤ አክብሮቱ እንዲሕ ተጀመረ።መጋቢት 14 1969።ሶማሊያን ለሰወስት ቀን የጎበኙት ፊደል ካስትሮ አዲስ አበባ ገቡ።አዲስ አበባን ሲጎበኙ ሁለተኛቸዉ ነበር።ዓላማቸዉ።ያኔ በጦር ሐል የደረጀችዉ የጄኔራል ዚያድ ባሬዋ  ሶሻሊስታዊት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሶማሊያን፤ በአብዮት የምትናጠዋን በጦር ሐይል ደካማዋን፤ የኮሎኔል መንግሥቱ ሐይለማርያም ሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያን እንዳትወር ለማግባባት ነበር።
ካስትሮ ከአዲስ አበባ ወደ ሰወስተኛዋ የአካቢዉ ሶሻሊስታዊት ሐገር ደቡብ የመን ተጓዙ።መጋቢት አስራ-አምስት። በሊቀመንበር  መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚመራዉ የኢትዮጵያ መንግሥት የመልዕክተኞች ጓድ ማምሻዉን ተከተላቸዉ።
«አደን የደርሰነዉ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት ግድም ነበር።የኩባና የሶማሊያ መልዕክተኞች ቀድመዉን ደርሰዋል።» ይላሉ ኮሎኔል መንግሥቱ «ትግላችን» ባሉት መፅሐፍ።ፊደል ካስትሮና ምክትላቸዉ፤ የየመኑ ሶሻሊስታዊ ፓርቲ መሪ አብዱልፈታሕ ዑስማኤልና ተከታዮቻቸዉ የሸመገሉት ድርድር ያለ ዉጤት አበቃ።ዚያድ ባሬ ሌሊቱኑ ወደ ሞቃዲሾ ተመለሱ።
መንግሥቱ ወደ አዲስ አበባ ከመመለሳቸዉ በፊት ካስትሮን አነጋገሩ።«ጓድ ፊደል ሲቀበሉን ጦርነቱን ገጥመን ፤የተሸነፍን ይመስል በጣም በማዘንና በመጨነቅ ሊያፅናኑን ሞከሩ።» ይላሉ መንግሥቱ።ቀጠሉ።«ሶማሌዎች ዉጊያዉን ሊያሸንፉ ይችላሉ።በጦርነቱ ግን አሸናፊዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነዉ። በማለት እኛ መልሰን አፅናናቸዉ።»
ካስትሮ መለሱ፤- «ልክ ናቸሁ በጦርነት አሸናፊዉ አብዮት ነዉ። እኛ የጠላነዉ፤ ላጭር ጊዜም ቢሆን መሸነፋችንን በመገመት ነዉ።» «መሸነፋችንን።» ይሕቺ ቃል   ጦርነቱ የኢትዮጵያ-የሶማሊያ ብቻ ሳይሆን የኩባና የሶማሊያ፤የደቡብ የመንና የሶማሊያ መሆኑንም አረጋገጠች።ይሕቺ ቃል ጦርነቱ የሶቭየት ሕብረትና የዩናይትድ ስቴትስ፤ የሶሻሊስቱና የካፒታሊስቱ ዓለም ጦርነት፤ የቀዝቃዛዉ ጦርነት አካል መሆኑን አረጋገጠች።
ኩባና የመን ወታደሮቻቸዉን ወደ ኢትዮጵያ ሲያዘምቱ ሶቬት ሕብረት ዘመናይ ጦር መሳሪያዋን አሰብ ላይ፤ በኮሎኔል መንግሥቱ ሐይለማርያም ቋንቋ «ዘረገፈችዉ።» የኢትዮጵያና የኩባ፤የኢትዮጵያና የየመን ወዳጅነት በደም ተሳሰረ።በጦርነቱ አባቶቻቸዉን ያጡት ኢትዮጵያዉን ለትምሕርት ወደ ኩባ ሲሄዱ ደግሞ በደም የተለሰነዉ ወዳጅነት ወደ ሁለተኛዉ ትዉልድ ተሻጋገረ።
                               
ኢንጂነር ደረጀ።

Fidel Castro, Osvaldo Dortico, Ernesto "Che" Guevara, Augusto Martinez-Sanchez, Antonio Nunez-Jimenez, William Morgan, Eloy Guttierez Menoyo
ምስል picture alliance / AP Photo
Kuba Fidel Castro verleiht Chatami Orden
ምስል picture-alliance/dpa/N. Barroso
USA Exil-Kubaner jubeln nachdem Fidel Catro gestorben ist
ምስል picture alliance/dpa/G. De Cardenas

አቶ ዝናዉ ተስማ።ኩባ ከኢትዮጵያ ጦር ጎን ሆኖ የሶማሊያን ጦር እንዲወጋ ያዘመተችዉ ሠራዊት  15 ሺሕ ይገመታል።ኩባ ይሕን ያሕል ጦር ያዘመተችበትን ምክንያት ለማወቅ አንድ የኢጣሊያዊ ጋዜጠኛ ካስትሮን ባንድ ወቅት ጠየቃቸዉ።ካስትሮ መለሱ፤-ጋዜጠኛ ተፈሪ ይንገረን።
                         
ኩባዎች ኢትዮጵያን ከጥቃት ለመከላከል ሲዘምቱ የ1970ዎቹ የመጀመሪያዉ አይደለም።ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ቢያንስ አንድ ኩባዊ የጦር መኮንን ከኢትዮጵያዉያን ጎን ሆኖ ለኢትዮጵ ነፃነት ተዋግቷል።በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምሕር አቶ ዮናስ አሽኔ የዚያን ኩባዊ ተጋድሎ የኢትዮጵያና የኩባ ግንኙነት መጀመሪያ ይሉታል።
                                  
ዶክተር ተስፋዬ ተርጓሚ ናቸዉ። ኩባ ከተማሩ ኢትዮጵያዉን ወጣቶች አንዱ መሆን አለመሆናቸዉን ላሁኑ አናዉቅም።የምናዉቀዉ ኩባ ዉስጥ ያደጉና የተማሩ በሺ የሚቆጠሩ ሐኪሞች፤ መሐንዲሶች፤ ጋዜጠኞች፤ የፋብሪካ ቴክኒሻኖች ሌላም ኢትዮጵያዉያን ባለሙያዎች መኖራቸዉን ነዉ ።የዚሕ ሁሉ መሠረት አንድም ካስትሮ፤ ሁለትም መንግሥቱ ናቸዉ።ሁለተኛዉ ተሰደዋል።የመጀመሪያዉ፤-
                                      
«ዉድ ኩባዉያን፤  ለዜጎቻችን፤አሜሪካና በመላዉ ዓለም ለሚገኙ ወዳጆቻን፤ በጥልቅ ሐዘን መናገር አለብኝ።ዛሬ ሕዳር 25 2016 ከምሽቱ 10 ሰዓት፤ከ29 ደቂቃ ላይ የኩባ አብዮት መሪ ፊደል ካስትሮ ሩዝ አረፉ።»ታናሽ ወድማቸዉና ያሁኑ ያሁኑ የኩባ መሪ ራዑል ካስትሮ።
ዩናይትድ ስቴትስ ከስድስት መቶ ጊዜ በላይ የቃጣችባቸዉን የግድያ ሙከራ አምልጠዋል።የፈጣሪዉን ግን በርግጥ ማምለጥ አይችሉም። አልቻሉምም። አሜሪካ-ኩባዉያን ፈነጠዙ።ኩባዉያን ደነገጡ።በመላዉ ዓለም የሚገኙ የኩባና የካስትሮ ወዳጆች አዘኑ።እንደ ፖለቲከኛ አንደበተ ርትዕ፤ እንደ ሕግ ባለሙያ ለፍትሕ ተቆርቋሪ፤ እንደ አብዮታዊ ቆራጥ፤ እንደ ሰዉ ለደሐ አዛኝ ነበሩ።አንድ ግን ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ተዘጋ።አዲዮስ አሚጎስ። 

Iran Fidel Castro und Ebrahim Yazdi
ምስል entekhab
Kuba Fidel und Raul Castro
ምስል picture-alliance/dpa/A. Ernesto

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ