1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ካርታ፤ የኢትዮጵያዊው ወጣት እቅድ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 21 2008

በየትኛውም የኢትዮጵያ ከተማ አንድን ቦታ በቀላሉ ለማግኘት ወይም ለመለየት የሚያችል ወጥ የአድራሻ ስርዓት የለም። በቅንጡ (ስማርት) የእጅ ስልኮች አድራሻ ለማግኘት ወይም አቅጣጫ ለመጠቆም የሚችሉ ማስተናበሪያዎችም ግልጋሎታቸው ውስን ነው። ወጣት ቴዎድሮስ ወንደሰን ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ማስተናበሪያ በመስራት ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/1IfRD
Addis Ababa (Äthiopien)
ምስል picture alliance/landov

ካርታ፤ የኢትዮጵያዊው ወጣት እቅድ

አዲስ አበባ፤ እንደ መናገሻ ከተማነቷ ያልዘመነች ግን ደግሞ ከዓመት ዓመት እንዳሻት የምትሰፋ ከተማ።መናገሻ ከተማ ሆና ከመቶ አመታት በላይ ብትዘልቅም፤የአፍሪቃ ሕብረት እና የአፍሪቃ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማት መቀመጫ ብትሆንም ዛሬም ዘመናዊና ዘላቂ አድራሻ ጠቋሚ የላትም። አዲስ አበባ ላይ አንድን ቦታ በቀላሉ ያለምንም መጉላላት ማግኘት እንዲህ ቀላል አይደለም። ከከተማዋ አስተዳደር ስያሜ የተሰጣቸው አውራ ጎዳናዎቿ በነዋሪዎቿ ዘንድ የሚታወቁበት ስያሜም ወጥ አይደለም። ለአስቸኳይ የእሳት አደጋና የአንቡላንስ አገልግሎት አድራሻን በመጠቆም በፍጥነት ማግኘት የሚያስችሉ በኢንተርኔት የሚታገዙ የቅንጡ ስልኮች ማስተናበሪያዎች (አፕልኬሽን) አዲስ አበባ ላይ አይሰሩም። እኒህን መሰል ግልጋሎቶች ዛሬም ድረስ በተለምዶ ተቀባይነት ያገኙ መጠሪያዎችን ይጠቀማሉ። አድራሻ ፍለጋ እና ጥየቃ የአዲስ አበባ መገለጫዎች ናቸው። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂው ወጣት እቅድ ይህን ችግር ለመፍታት ያለመ ነው።
ኢትዮጵያ ከ1946 ዓ.ም. ጀምሮ የካራታ ስራን የሚከውን ተቋም አላት። ለዓመታት ለካርታ ስራ የሚያስፈልጉ መረጃዎች ቢሰበሰቡም በዘመናዊ መንገድ ተሰንደው ለአጠቃቀም ምቹ በሆኑ የኢንተርኔት ግልጋሎቶች አልቀረቡም። የጉግል አቅጣጫ ጠቋሚ ግልጋሎት ከአዲስ አበባ መንገዶች እና የመኖሪያ መንደሮች ስያሜዎች እና አድራሻዎች መጠቆም የሚችለው እጅጉን ጥቂቶቹን ብቻ ነው። ቴዎድሮስ ወንድሙ ካርታ በተሰኘው እቅድ እንደ ጉግል የአድራሻ መፈለጊያ እና የአቅጣጫ መጠቆሚያ የአውራ ጎዳና ስያሜዎችን ከመጠቀም ይልቅ የክፍለ-ከተማ፤ወረዳ እና የቤት ቁጥርን መርጧል።
የቴዎድሮስ ወንድሙ እና ባልደረቦቹ ካርታ እቅድ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የሥራ ፈጠራ ባለሙያዎች ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ተካፋይ መሆን ችሏል። ውድድሩ በድረ-ገጽ በሚሰጥ ድምጽ መሰረት የሚካሄድ ሲሆን ለውድድር ከቀረቡ 1075 ጀማሪ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መካከል ምርጥ 100 ውስጥ መግባት ችሏል። ውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አዳዲስ እና ወጣት ስራ ፈጣሪዎችን ለመገናኛ ብዙሃን እና እቅዶቹን በገንዘብ ሊደግፉ ከሚችሉ ባለ መዋዕለ-ንዋዮች ጋር የማስተዋወቅ ዓላማ አለው።
በአውራ ጎዳና አድራሻዎች መሰረት ግልጋሎት የሚሰጠው ግዙፉ ጉግል ማፕ አድራሻ እና አቅጣጫ በመጠቆም የሚስተካከለው የለም። ግልጋሎቱ ላርስ እና የንስ በሚባሉ ሁለት የዴንማርክ ወንድማማቾች የተጀመረ እቅድ የነበረ ቢሆንም በጎርጎሮሳዊው 2004 ዓ.ም. ጉግል ኩባንያ ገዝቶት አቀራረቡ እና ስፋቱ እንዲሁም የመገልገያ መንገዶቹ ተስፋፍተዋል። ጉግል ማፕ በድረ-ገጽ እና ቅንጡ የእጅ ስልኮችን ጨምሮ በተሽከርካሪ ላይ በሚገጠሙ አጋዥ አቅጣጫ ጠቋሚዎች አገልግሎት ያቀርባል። ተጠቃሚዎች ያሉበትን አድራሻ በዚሁ ግልጋሎት መሰረት ለሚፈልጉት ሰው ማጋራትም ይችላሉ። የአምቡላንስ፤እሳት አደጋ እና የቤት ለቤት አገልግሎት አቅራቢዎች በጉግል ማፕ ቀላል ሆነዋል። ይህ ግን ኢትዮጵያን አይጨምርም። የኢትዮጵያን ከተሞች፤የቱሪስት መዳረሻዎች፤የተቋማት አድራሻዎች በጉግል ማፕ ላይ ማግኘት ቢቻልም መረጃው ጥልቀት የለውም። በድምጽ እና ምስል የተደገፈ የአቅጣጫ ጥቆማውም ውስን ነው። ለመሆኑ የቴዎድሮስ ካርታ ከጉግል በምን ይለያል?
ቴዎድሮስ የካርታ አድራሻ እና አቅጣጫ መጠቆሚያ በተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎት እንዲያርብ ለማድረግ ማቀዳቸውን ተናግሯል። አገልግሎቱ ወጥ የአድራሻ አገልግሎት መስጫ ለሌላቸው አገሮች የማስፋት ሃሳብም አላቸው። በሙከራ ላይ የሚገኘውን የካርታ ማስተናበሪያ ወይም አፕልኬሽን ማንኛውም ሰው በእጅ ስልክ መሞከርም ይችላል።

Äthiopien Hausbau
ምስል DW/E. Bekele


እሸቴ በቀለ


ሒሩት መለሰ