1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

  ካሌ፤ የስደተኞች ምኞት ሞት አብነት

ነጋሽ መሐመድ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 21 2010

እኒያ ከብጥጣሽ ላስቲክ፤ ካርቶን፤ ኬሻ እና ቆርቆሩ እንደነገሩ የተወናካሩት የጫካ ዉስጥ ጎጆዎች ከምድር ተለነሰኑ።ዐሥር ሺዎች ይርመሰመሱበት የነበረዉ ሥፍራ ገና ሳር ቅጠል በቅጡ አላበቀለም ግን ሰዉ እንስሳ ዝር የማይልበት ጥብቅ ምድር ነዉ።

https://p.dw.com/p/2mpJt
Migranten in Calais beim gemeinsamen Mittagessen
ምስል DW/D.Pundy

የፈረንሳይ ትልቁ የስደተኞች መሰብሰቢያ ሥፍራ ከመሆኑ እኩል የአሳዛኝ አኗኗር ምሳሌ በመሆኑም ዝናን አትርፎ ነበር።የካሌ ጫካ።ብሪታንያ ለመሻገር የሚፈልጉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ስደተኞች ከዉድቅዳቂ ላስቲክ፤ቆርቆሮ፤ ካርቶንና እንጨት በሰሯቸዉ ጎጆ እና ድንኳኖች ዉስጥ ለበርካታ ዓመታት ኖዉረዉበታል።የፈረንሳይ መሪዎች «ሕገ ወጥ» ያሉት ግዙፍ ጣቢያ እንዲፈርስ ባዘዙት መሠረት ስደተኞች  ከወደብ ከተማይቱ ካሌ ተግዘዉ በመላዉ ፈረንሳይ ከተበተኑ ባለፈዉ ማክሰኞ ዓመት ደፈነ።በአካባቢዉ ሰዉ እንዳይደርስበት ታግዷል።ካሌ ግን፤ ክርስቲን ጋልመየር እንደዘገበችዉ፤ዛሬም ስደተኞች አላጣችም።ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

ወደ ብሪታንያ በሚያሻግረዉ የካሌ ዋሻ በር ላይ በትላልቅ፤ ድርብ ገደምዳማ ፊዳላት የተፃፈዉ መፈክር ዛሬም ይነበባል።ለንደን ኮሊንግ ይላል ጽሑፉ። «ለንደን ትጣራለች» እንበለዉ ይሆን? በር ዘግቶ ጥሪ።እስካምና ድረስ 10 ሺሕ ስደተኞች የተስፋ ምድራቸዉን «ከዋሻዉ ማዶ» አንጋጠዉ ያማትሩ ነበር።አምና ጥቅምት ግን የያኔዉ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦሎንድ ያን የስደተኞች መከማቺያ «አጥፉልኝ» አሉ

 
                           
«ይሕን ጣቢያ ሙሉ በሙሉ እና በማያዳግም ሁኔታ ማፍረስ አለብን።ጨርሶ ማጥፋት አለብን።ሥደተኞቹን ሌላ ሥፍራ ሥናሰፍር ሰብአዊነትንም ከግምት ማስገባት አለብን።»  
ጥቅምት 14።ትዕዛዝ ገቢር ሆነ።አዉቶቡሶች ተደረደሩ።ባንድ ጀምበር ሰባት ሺሕ ስደተኞች በመላዉ ፈረንሳይ ተበተኑ።በያላችሁበት የጥገኝነት ማመልከቻ አስገቡ ተባሉ።ለአካለ መጠን ላልደረሱ ጥቂት ስደተኞች ግን እርምጃዉ ሳይደግስ አይጣላም ዓይነት ነበር።ለንደን ጠራቻቸዉ።ብሪታንያ ተሻገሩ።
እኒያ ከብጥጣሽ ላስቲክ፤ ካርቶን፤ ኬሻ እና ቆርቆሩ እንደነገሩ የተወናካሩት የጫካ ዉስጥ ጎጆዎች ከምድር ተለነሰኑ።ዐሥር ሺዎች ይርመሰመሱበት የነበረዉ ሥፍራ ገና ሳር ቅጠል በቅጡ አላበቀለም ግን ሰዉ እንስሳ ዝር የማይልበት ጥብቅ ምድር ነዉ።አዉበርግ የተሰኘዉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት ምክትል ኃላፊ ፍራንሷ ጋኖክ እንደሚሉት ካሌ ስደተኛ ልታጣ አትችልም።
                                          
«ኢንግላንድ የምትርቀዉ አሁንም ሰላሳ ኪሎ ሜትር ነዉ።አሁንም ስደተኞችን ትማርካለች።»
ከተማይቱ ዉስጥ ሰባት መቶ ስደተኞች አሉ።አብዛኞቹ የአፍቃኒስታን፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ ዜጎች ናቸዉ።ስደተኞቹ  ተበታት ነዉ የሚኖሩት።የርዳታ ድርጅቱ ባልደረባ ሎዋ ቶሮንዴል እንደሚሉት ፖሊስም ስደተኞቹን ማደኑን አልተወም።
                                      
«ፖሊሶች በየሳምንቱ ሁለት-ሦስት ጊዜ እንደሚመጡ እናዉቃለን።ብዙ ጊዜ የሚመጡት ማታ፤ ሌሊት ወይም ማለዳ ነዉ።ስደተኞቹን ያንገላቷቸዋል።በአስለቃሽ ጋስ ያፍኗቸዋል።ልብሳቸዉን ይገፋሉ፤ ድንኳን ዉስጥ ካገኟቸዉም ድንኳኑን ያፈርሱባቸዋል።አንዳዴ የግል ዶክሜንታቸዉን እና ተንቀሳቃሽ ሥልካቸዉን ይቀሟቸዋልም።የሚጠጣ ዉኃቸዉን ሳይቀር በጢስ ይበክሉባቸዋል።»
የግብረ ሰናይ ድርጅቶቹን ወቀሳ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳስተባበሉ ነዉ።አዲሱ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ማኑኤል ማክሮ ከመጪዉ ታሕሳስ በኋላ አንድም ሥደተኛ ፈረንሳይ አዉራ መንገዶች ላይ እንዳይታይ ለማድረግ ዝተዋል።አዉቡርግ የተሰኘዉ ግብረ ሠናይ ድርጅት ምክትል ኃላፊ ፈራንሷ ገኖ የፈረንሳይ መንግስት ርምጃን ይቃወማሉ።

Winterdecken in der Lagerhalle der NGO Auberge des Migrants in Calais
ምስል DW/D.Pundy
Frankreich Abschiebung von Asylsuchenden
ምስል picture-alliance/NurPhoto/J. Pitinome

ነጋሽ መሐመድ 

አርያም ተክሌ