1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ60ዓመት በኋላ የፈረንሳይና የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ግንኙነት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 18 2012

በ1960ዓ,ም ነው በፈረንሳይ የቅኝ ግዛትነት ሥር ለ60 ዓመታት የቆዩት 14 የአፍሪቃ ሃገራት ነጻነታቸውን ያገኙት። ሆኖም የየሃገራቱን ይዞታ በቅርበት የሚያስተውሉ ወገኖች እንደሚሉት ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎቹ የአፍሪቃ ሃገራት እውነተኛ የሆነ ነፃነት ገና አላገኙም።

https://p.dw.com/p/3ftKw
Infografik Karte ECOWAS Staaten, Afrika EN

ከ60ዓመት በኋላ የፈረንሳይና የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ግንኙነት

በ1960ዓ,ም ነው በፈረንሳይ የቅኝ ግዛትነት ሥር ለ60 ዓመታት የቆዩት 14 የአፍሪቃ ሃገራት ነጻነታቸውን ያገኙት። ቤኒን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒቢሳው፣ ኮትዴቯር፣ ማሊ፣ ኒዠር፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦን እና ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ከቅኝ ተገዢነት ሲላቀቁ፤ በሚሊየኖች የሚቆጠሩት የእነዚህ ሃገራት ዜጎች ነጻነት፣ እፎይታና ተስፋ ሊሰማቸው እንደሚገባ ይታመናል።  ሆኖም በኮትዴቩዋር ሪፑብሊክ የነጻነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ አማካሪ የሆኑት ናታሊ ያምቢ እንደሚሉት ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎቹ የአፍሪቃ ሃገራት እውነተኛ የሆነ ነፃነት ገና አላገኙም።

«ነጻ ወጡ ከተባለበት ከ60 ዓመት በኋላ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎቹ የአፍሪቃ ሃገራት እውነተኛ ነጻነትና ነፃ ግዛታቸውን ከፈተንሳይ ገና አላገኙም። እነዚህ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ የሆኑት ሃገራት ነጻነታቸውን ከማግኘታቸው አስቀድሞ ፈረንሳይ የአንዳንዶቹን ሕገ መንግሥት ለውጣለች። በዚህም ፓርላሜንታዊ የነበረውን አገዛዝ ለመለወጥ ወስናለች፤ ለምሳሌ ኮትዴቩዋር እስከ1959 ድረስ ፓርላሜንታዊ አገዛዝ ነበራት። ከዚያም ፕሬዝደንታዊ አገዛዝ በየሕገ መንግሥቱ ደነገጉ፤ ይህም በየሀገሩና ግዛቱ ያለው ሥልጣን በአንድ ሰው እጅ ማለትም በሀገር መሪው እጅ እንዲጠቀለል አደረጉ። እናም ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረውን አንድ ግለሰብ ተጠቅመው በዚያች ሀገር ላይ ይዞታቸውን ለማስቀጠል ችለዋል።»

በእነዚህ ሃገራትም የመማሪያ መጻሕፍት ከሚያካትቱት ይዘት አንስቶ የሚወሰነው በፈረንሳይ ነው። በዚያም ላይ የእነዚህ ሃገራት አብዛኞቹ ሥርዓቶች የሚመሠረቱት በፈንሳይ ቅጂ መሆኑንም ያነሳሉ።  

Frankreich Ambition Africa 2018 in Paris
ምስል DW/H. Tiruneh

የፈረንሳይ ተፅዕኖም  በእነዚህ ሃገራት በተለይ በወጣቶች ዘንድ በቀድሞ የቅኝ ገዢዎች ላይ ያሳደረው የቁጣ ስሜት መባባሱ ታይቷል። በዚህም ምክንያት ላለፉት 40 ዓመታት ለፕሬዝደንታዊ እጩነት የቀረቡ ተፎካካሪዎች ፍራንኮ አፍሪኬ ከሚሉት የፈረንሳይ ተፅዕኖ ለመላቀቅ ቃል ሲገቡ ቆይተዋል። እንዲያም ሆኖ ይህ ሁሉ ቃል ኪዳን ከተለመደ ንግግር አልፎ አልታየም ይላሉ በስኮትላንድ ሴንት አንድሪው ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ ፖለቲካ ፕሮፌሰር ኢያን ቴለር።

«ለመለወጥ እንደሚፈልጉ እንዲህ ያለውን ነገር ይናገራሉ ግን ደግሞ  ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የንግድ  እንዲሁም የፖለቲካ ፍላጎቶቹ አሁንም በጣም ጠንካሮች መሆናቸው ስለሚረዱ ከሁለቱም ወገን እውነተኛ የሆነ ግንኙቱ ላይ መሠረታዊ ማስተካከያ ሲያመጡ አልታየም።»

ለመሆኑ የአፍሪቃ ምሁራንም ሆኑ የፈረንሳይ የፍራንኮ አፍሪኬ መላቀቅ እንዴት ተሳናቸው? በጎርጎሪዩዮሳዊው 1962 ዓ,ም ነው የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ቻርልስ ደ ጎል በአማካሪያቸው ዣክ ፎካርት አማካኝነት ፍራንኮ አፍሪኬን ያቋቋሙት ፍራንኮ አፍሪኬ ዓላማው በፈረንሳይና የቅኝ ግዛቶቿ በነበሩት ሃገራት ምሁራን መካከል የግንኙነት ሰልሰለት መገንባት ነው። ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ካነጋገራቸው አንዱ በብሪታኒያው ቻተም ሀውስ የአፍሪቃ ፕሮግራም አማካሪ ፖል ሜሊ እንደሚሉት ይህ ከስኬት እንዳይደርስ ትልቁን ሚና የሚጫወተው የምሁራኑ የግል ፍላጎት ነው። ፎካርት ይህን ትስስር የመሰረቱት በግለሰቦች አማካኝነት በመሆኑም ግንኙነቱ ግላዊ፣ ግልፅነት የጎደለውና በጣም ቁጥጥር የታከተለበት ነውም ይላሉ። በዚህም የየሃገራቱ መሪዎች መፈንቅለ መንግሥትን ለመከላከል ከፈረንሳይ ለሚያገኙት ወታደራዊ ከለላ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ስልታዊ በሆነ መንገድ የተፈጥሮ ሃብቶችን ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል። እናም ዛሬ ፈረንሳይ አፍሪቃ ውስጥ ያላት ሕልውና ጠንካራ ነው፤ ይህም ከዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ቀጥላ በሦስተኝነት ደረጃ ያስቀምጣታል።

Die Währung Franc CFA
ምስል Getty ImagesI. Sanogo

በወታደራዊውም ቢሆን 4500 የፈረንሳይ ወታደሮች በምዕራብ አፍሪቃ ተሰማርተዋል። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱትም በጎርጎሪዮሳዊው 2007ዓ,ም 12 ሺህ የፈረንሳይ ወታደሮች አፍሪቃ ውስጥ በተለያየ ተልዕኮ ሥር ተሰማርተዋል። ባሉበት ሀገርም ከወታደራዊ አገልግሎት በተጨማሪ የማማከር ሙያ ያላቸው ሲሆኑ ለአገዛዞቹ ድጋፍና የማረጋጋት ሥራ ያከናውናሉ። ናታሊ ያምቢ ይህ ሁሉ ተስፋ አስቆራጭ ነው ይላሉ።

«ከሥርአቱ በተጨማሪ የየሪፐብሊኩ ፕሬዝደንቶች ይህ እንዲቀየር አይሹም። የሕዝባቸውን ፍላጎት ከማስጠበቅ ይልቅ የፈረንሳይን መንግሥት ማገልገሉ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። ነገር ግን ሕዝቡም ሆነ ወጣቱ እውነተኛ ነጻነትና ቅጥ ያጣ ወዳጅነት እንዲሁም ጤናማ ባልሆነ መንገድ ከፈረንሳይ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲቆም በግልፅ ይጠይቃል።»

Frankreich l Macron wirbt für Sahel-Initiative
ምስል Getty Images/AFP/G. Horcajuelo

በፈረንሳዩ የዓለም አቀፍና ስልታዊ ግንኙነት ተቋም ረዳት ተመራማሪ ካሮሊን ሮውዚ ግን በዚህ አይስማሙም። ፈረንሳይ የቅኝ ግዛቶቿ በነበሩት የአፍሪቃ ሃገራት ላይ ያላት ተፅዕኖ በፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ አስተዳደር ለመለወጥ እየተሞከረ ነው ሲሉም ይሞግታሉ።

«ራስ የመቻሉ ነገር ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኗል ማለት ባይቻልም ከ60 ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር የሚነጻጸር አይደለም። ፈረንሳይም ሆነች ፕሬዝደንት ማክሮ ይህን ለመለወጥ እየሞከሩ ነው። በዚህ ለውጥ አማካኝነትም በፈረንሳይና አፍሪቃ መካከል አዲስ ታሪክ ሊጀመር ነው።»

ለዚህ ማሳያም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ የተገፋውን «አፍሪኬ ፍራንስ» የተሰኘው የፈረንሳይና የአፍሪቃ መንግሥታት ጉባኤ ይጠቅሳሉ። በዚህ ጉባኤም ሁለቱም በጋራ አፍሪቃ ውስጥ በመጪዎቹ አስርት ዓመታት ለማከናወን የታቀደውም ከተሞች የማስፋፊያ ፕሮጀክት በመንደፍ መፍትሄውንም በጋራ ለመፈለግ ታቅዷል። ለናታሊ ያምቢ ግን ይህም ቢሆን የቃላት ጨዋታ ነው። «ፍራንክ አፍሪኬም ሆነ አፍሪኬ ፍራንስ» ለውጥ የለውም። እንደውም ግንኙነቱን ይበልጥ የከፋ ሊያደርገው ይችላልም ባይ ናቸው።

ፈረንሳይ በአፍሪቃ ያላትን ሚና ካጣች ዋጋም አይኖራትምም ነው የሚሉት። ይህ እንዳይሆን ይሻሉ ያሏቸው ማክሮ አፍሪቃ የማትሻውን ነገር ለመጫን እየሞከሩ እንደሆነም የሚናገሩት ያምቢ የምዕራብ አፍሪቃ የጋራ መገበያያ ሃሳብን በምሳሌነት ያነሳሉ።

«ኤኮ ፕሮጀክት በጣም የቆየ ነው። የኤኮዋስ የድሮ ፕሮጀክት ነው። ፈረንሳይ ታዲያ ስሙን ብቻ እንቀይረው ብላ ወሰነች። የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ትብብር ፕሮጀክትን ወስዳ ስሙን ለወጠች። እናም ስሙን ብቻ በመለወጥ ስልቱ የተቀየረ የሚመስል ጨዋታ መሆኑ ነው። ይህ የአፍሪቃ ሃገራት ተነሳሽነት ሊሆን ይገባው ነበር። በፈረንሳይ ሊቀረጽ ወይም ይፋ ሊደረግ ወይም ሊታቀድ አይገባውም ነበር።»

Italien Demonstration Anti-CFA in Rom
ምስል picture-alliance/NurPhoto/A. Ronchini

ፈረንሳይ ኤኮን በሲኤፍ ኤ ነው የለወጠችው፤ ሲኤፍኤ በፈረንሳይ ምህጻሩ የአፍሪቃ የፋይናንስ ማኅበረሰብ እንደማለት ነው። በዚህ የጋራ መገበያያ የሚጠቀሙት የአፍሪቃ ሃገራት ለሚከናወነው የውጭ ገንዘብ ልውውጥ 65 በመቶ የሚሆነውን በፈረንሳይ የገንዘብ ሚኒስቴር ማጠራቀም ይጠበቅባቸዋል። ከዩሮ ሊተካከል ይቃጣዋል የተባለው ይህ የጋራ ሸርፍ ሃሳቡ ድንቅ ቢሆንም ችግሩ ግን እያንዳንዱ የአፍሪቃ መንግሥት ምን ያህል ገንዘብ በፈረንሳይ ግምጃ ቤት እንዳለው አለማወቁ መሆኑን ፕሮፌሰር ኢያን ቴይለር ጠቁመዋል። በዚያም ላይ ቴይለር በዚህ መልኩ የሚሰባሰበውን ገንዘብ ፈረንሳይ የልማት ርዳታ የሚል መለያ መስጠቷ አይገባም ሲልም ይወቅሳሉ። ከቅኝ ተገዢነት የተላቀቁት የአፍሪቃ ሃገራት አሁን ከ60 ዓመታት በኋላ ወደ እውነተኛ ነጻነት መሻገር የሚችሉት ይህን በፈረንሳይ የተቀየሰላቸውን የጋራ ሸርፍ ወደመቃብር ሲልኩ ነው። ለዚህ የሚፈልጉት ደግሞ አፍሪቃን ማስቀደም የሚችሉ የአፍሪቃ ምሁራን ዝግጁነት እንደሚሆንም አጽንኦት ሰጥተዋል።   

Krise in Mali | ECOWAS | Nana Akufo-Addo und Boubou Cissé
ምስል Présidence du Mali

ማሊን በአንድ ወገን በአካባቢው የተጠናከረው የፅንፈኛ ሙስሊሞች በሌላ ወገን የሀገር ውስጥ ፖለቲካ ውዝግብ ከመንታ መንገድ ጥሏታል። ከትናንት በስተያ ሐሙስ ዕለት ባማኮ ላይ አምስት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት መሪዎች እንዲሁም የማሊ መንግሥትና ተቃዋሚ ኃይሎች በተገኙበት የተካሄደው ውይይት ያለውጤት ተጠናቋል። ውይይቱ ለማሊ ቀውስ የፈየደው ባለመኖሩም የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 20 ቀን 2012 ዓ,ም  የ15ቱ የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ ኤኮዋስ አባል ሃገራት በጉዳዩ ላይ አስቸኳ ጉባኤ በቪዲዮ ያካሂዳሊ። የሰኔጋል፤ የኮትዴቩዋር፣ የናይጀሪያ፣ ኒዠርና የጋና መሪዎች አስቀድመው ከፕሬዝደንት ኬይታ ጋር ከተወያዩ በኋላ ነበር ተቃዋሚዎችን አክለው የተነጋገሩት። ሆኖም ተቀናቃኞቹ ሊግባቡ አልቻሉም።   

 የወቅቱ የኤኮዋስ ሊቀመንበር የኒዠር ፕሬዝደንት ማሀማዱ ዩሱፉ ከስብሰባው በኋላ በሰጡት መግለጫ ተቋሙ ይህን ቀውስ ለመፍታት ጠንካራ ርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል። በሙስና፣ በአካባቢ የምርጫ ውጤት እንዲሁም የሀገሪቱ ሠራዊት በጅሃዲስቶች በመሸነፉ በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በቁጣ ጎዳና ላይ በመውጣት ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል። በዚህም የተመድ እንደሚለው 14 የተቃውሞው ሰልፈኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል።  የድርጅቱ የሰብያዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንም ማሊ ውስጥ ውጥረቱ በተባባሰበት በዚህ ወቅት አሁንም የፀጥታ ኃይሎች ከሚወስዷቸው የኃይል ርምጃዎች እንዲቆጠቡ አሳስቧል። በምህጻሩ M5-RFP በመባል የሚታወቀውን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ የሚመሩት ሳውድ አረቢያ የሰለጠኑት የሙስሊም ሃይማኖታዊ መምህር ማህሙድ ዲኮ የጀመሩትን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ፕሬዝደንት ኢብራሂም ባቡከር ኬይታ ሥልጣን ካለቀቁ በቀር አላቆምም ማለታቸው ቀውሱ ይዛመትብናል በሚል የማሊን ጎረቤት ሃገራት እያሰጋ ነው። የትናንት በስተያው ስብሰባ እንዳበቃም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እስካሁን ላቀረቡት ጥያቄ መፍትሄ ሊሆን የሚችል ምላሽ እንዳልተገኘ ተናግረዋል። ከጥያቄዎቻቸው መካከልም በሲቪሎች ላይ የተካሄደውን ግድያ የሚያጣራ ኮሚቴ ይቋቋም፤ እንዲሁም የሽግግር መንግሥት ይመስረት የሚሉት ይገኙበታል። የኒዠር ፕሬዝደንት ግን ፕሬዝደንቱ ሥልጣን ይልቀቁ የሚለውን በተመለከተ ኤኮዋስ ቀይ መስመር አስምሯል ብለዋል። አክለውም «በኤኮዋስ አባል ሃገራት ውስጥ ኢሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ለውጥ ተቀባይነት የለውም» ሲሉ ቁጥሩን ተናግረዋል።   

Mali I Proteste gegen Ibrahim Boubacar Keita in Bamako
ምስል Reuters/M. Rosier

ፕሬዝደንት ባቡከር ኬይታ ማሊ ውስጥ ለዓመታት የዘለቀውን ከፅንፈኞች ጋር የሚካሄድ ውጊያ ማጠናቀቅ አልቻሉም የሚለው ከፍተኛ ጫና አስከትሎባቸዋል። 20 ሚሊየን ሕዝብ ያላት ድሀይቱ አፍሪቃዊት ሀገር ከጎርጎሪዮሳዊው 2012 ዓ,ም አንስቶ በምታካሂደው ውጊያ ምንም እንኳን የውጭ ሃገር ወታደሮች በስፍራው ቢኖሩም በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ከመኖሪያቸው ይፈናቀሉባታል።ከሚያዝያ ወዲህ በማሊ ቀውሱን ያባባሰው በተካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ላወዛገበው ውጤት ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ለገዢው ፓርቲ አድልቷል የሚለው ነው። በዚህ ምክንያት የተካረረው የፓለቲካ ውዝግብ በተቃዋሚዎችና የፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት አስከትሎ 11 ሲገደሉ 158 መጎዳታቸው ይበልጥ ቀውሱን አናረው። ለማደራደር የገባው ኤኮዋስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተካተቱበት የአንድነት መንግሥት እንዲመሠረት ሃሳብ ከማቅረብ አልፎ ለውዝግቡ መንስኤ የሆነው የምርጫ ውጤት ላይ ብይን ያሳለፉት የሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ዳኞች ያንን ውጤት ሊመረምሩ በሚችሉ ሌሎች ዳኞች እንዲተኩ ቢጠይቅም፤ ተቃዋሚዎቹ ፕሬዝደንቱ ከሥልጣን ይነሱ የሚለው ካልተካተተበት አንቀበልም ማለታቸው ድርድሩ ፍሬ እንዳያስገኝ እንዳደናቀፈ ታይቷል። ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ ባማኮ የሚገኙ አንድ አውሮጳዊ ዲፕሎማት ግን ተቃዋሚዎቹ የፕሬዝደንት ኬይታ ስንብት ላይ ትኩረት መስጠታቸው ያለውን ችግር ያለማገናዘብ እንደሆነ ነው የጠቆሙት። እሳቸው እንደሚሉትም ለሳህል አካባቢ የፀጥታ ይዞታ አደገኛ መንገድ ሊሆን የሚችል ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ማንም አይፈልግም። የኤኮዋስም አቋም ከዚህ የሚለይ አይመስልም። ለሁሉም ከሰኞው ስብሰባ በኋላ የሚያሳልፈው ውሳኔውና የሚወስደው ጠንካራ ርምጃ የማሊን ዕጣ ፈንታ ወሳኝ መስሏል።

ECOWAS-Gipfel in Abuja, Nigeria
ምስል Präsidentschaftsbüro Kap Verde

ሸዋዬ ለገሠ