1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአፍሪቃ የተዘረፉ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች

ዓርብ፣ ሰኔ 28 2011

«ቅርሶቻችን ለማስመለስ በዲፕሎማቲክ መልኩ የመጠየቅ ሥራ እንጂ የማስገደድ ሁኔታ የማይቻል ነዉ። ስለሆነም በዲፕሎማሲዉ እየሰራን ነዉ። ባለፈዉም ከብሪታንያ የአፄ ቴዮድሮስን ቁንዱላ በባህልና ቱሪዝም ጥያቁ አስመልሰናል።በሱዳን ይገኛል የተባለዉን የአፄ ዮሃንስ ከአንገት በላይ የራስ ቅልን ለማስመለስ የኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለሥልጣን እየሰራ ነዉ።»

https://p.dw.com/p/3Lb4j
Museum für außereuropäische Kunst Quai Branly
ምስል picture-alliance/dpa/S. Glaubitz

«ቅርሶችን ከሃገር ተዘርፈዉ እንዳይወጡ እየሰራን ነዉ» የቅርስ ጥበቃ

«ሃገራት ይዘዉ የሚገኙትን የተዘረፉ ቅርሶች ወደ የሃገሮቻቸዉ ለመመለስ ፍላጎት ሊኖራቸዉ ይገባል። እኛም ዴፕሎማቲክ በሆነ መልኩ እንዲመልሱን የመጠየቅ ሥራ እንጂ የማስገደድ ሁኔታ የማይቻል ነዉ። ስለሆነም በዲፕሎማሲዉ እየሰራን ነዉ። ባለፈዉ ጊዜ ከብሪታንያ የአፄ ቴዮድሮስን ቁንዱላን በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጥያቄ አስመልሰናል። በሱዳን ይገኛል የተባለዉ  የአፄ ዮሃንስ የራስ ቅልን ለማስመለስ የኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለሥልጣን እየሰራ ነዉ።» በኢትዮጵያ ቅርስና ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ፈንታ በየነ ለዶቼ ቬለ«DW» ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደ ነዉ።  

Deutschland Bonn Ausstellung "Dogon - Weltkulturerbe aus  Afrika"
ምስል picture-alliance/dpa/H. Kaiser

በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ በሰሜን ምዕራባዊትዋ የጀርመን ከተማ ብሬመን የጀርመን ቤተ-መዘክር ማኅበር ባካሄደዉ ጉባዔ ማኅበሩ በጀርመን የቅኝ ግዛት ዘመን ከአፍሪቃ ወደ ጀርመን የገቡና በሃገሪቱ ቤተ-መዘክሮች የሚገኙ ቅርሶችን ታሪካዊነታቸዉን ለማጥናትና ይዞታቸዉን ለመጠበቅ ብሎም ለየባለቤቶቻቸዉ ለመመለስ ተጨማሪ ገንዘብና የሰዉ ኃይል እንደሚያስፈልግ ገልፆአል። በእለቱ ዝግጅታችን የጀርመን የቤተ-መዘክር ማኅበር ጉባዔ እንደምታን ይዘን ከኢትዮጵያ የተዘረፉ ጥንታዊ ቅርሶችን ለማስመለስ እየተካሄ ስላለዉ እንቅስቃሴ እንቃኛለን። ባለፈዉ የካቲት ወር በጀርመንዋ ከተማ ሽቱትጋርት የሚገኘዉ ቤተ-መዘክር ከናሚቢያ የመጣ አንድ ጥንታዊ መጽሐፍ ቅዱስ፤ የከብት ማገጃ ጅራፍ ወይም ከጅማት የተሰራ አለንጋ መሰል ነገር እንዲሁም ጥንታዊ የአዉስትራልያ ሰዎች አፅምን ወደመጡበት ሃገራት መልሶአል።   

የጀርመን ቤተ-መዘክር ማኅበር ባለፈዉ ሰኞ ብሬመን ከተማ ላይ ባካሄደዉ ጉባዔ ከአፍሪቃ ተዘርፈዉ እና በጀርመን ቤተ-መዘክሮች የሚገኙ ጥንታዊና ባህላዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት አልያም ወደ መጡበት ሃገራት ለመመለስ የሚያስችል አዲስ መመርያ ማዉጣቱን ገልፆአል። ማኅበሩ ይፋ ያደረገዉ መመርያ ለመጀመርያ ጊዜ በጎርጎረሳዉያኑ 2013 ዓ.ም ይፋ ያደረገዉ ብሎም በጎርጎረሳዉያኑ 2018  ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ አሻሽሎ ያቀረበዉ እንደነበርም ተገልፆአል። በያዝነዉ ሳምንት ተሻሽሎ ለሦስተኛ ጊዜ የቀረበዉ ይኸዉ መመርያ ተዘርፈዉ የተወሰዱ የሰዉ ልጅ ቅሪት አፅሞችን መመለስ በሚያስችልበት ጉዳይ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተመልክቶአል።

Älteste äthiopische Bibelhandschrift
ምስል DW/ A.T.Hahn

የአፍሪቃ ሃገራት በቅኝ ግዛት እጅ ስር ከወደቁ ጊዜ ጀምሮ በአዉሮጳ ሃገራት መንግሥታት የተዘረፉ ቅርሶች እንዲመለሱ የአፍሪቃ ሃገራት በመወትወታቸዉ፤ ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን 2018 ዓ.ም የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ ሃገራቸዉ በቅኝ ግዛት ዘመን በዝርፍያም ሆነ በስጦታ መልክ ወደ ሃገርዋ አስገብታ በቤተ-መዘክሮች የያዘቻቸዉን እንዲሁም በየግለሰቡ ቤት የሚገኘዉን ታሪካዊ የአፍሪቃ ቅርስ ለማስመለስ የሕግ ማሻሻያ ካወጡ በኋላ አድናቆትን ተቸረዋል። ከቅኝ ግዛት ሃገሮች የተዘረፉ ቅርሶችን ለመመለስ ጥረት የጀመሩ የመጀመርያዉ የአዉሮጳ ሃገር መሪ መሆናቸዉም ተነግሮላቸዋል። የአፍሪቃ ሃገራት ቅርሶች ወደ ተዘረፉበት ሃገራት እንዲመለሱ የሚወተዉቱት ታዋቂዉ የሴኔጋል የኤኮኖሚ ባለሞያ ፌልዊን ሳር እና ፈረንሳዊዉ የቅርስ ታሪክ አዋቂ ቤኔዲክት ሳቮይ የማርኮን ርምጃ ለአፍሪቃ ሃገራት ታሪካዎ ቅርሶችን ለመመለስ የተጣለ አንድ የመሠረት ድንጋይ ሲሉም አሞካሽተዋቸዉ ነበር። በያዝነዉ ሳምንት ሰኞ የጀርመን ቤተ-መዘክር ማኅበር ያካሄደዉ ጉባዔ የተዘረፉ ቅርሶችን ለማስመለስ ትግል ለጀመሩት ለሴኔጋሉ የኤኮኖሚ ባለሞያ ፌልዊን ሳር እና ለፈረንሳዊዉ የቅርስ ታሪክ አዋቂ ቤኔዲክት ሳቮይ በ 2018 ዓ.ም ላቀረቡት ይፋዊ ጥሪ መልስ ለመስጠት ይሆን በሚል ከዶቼቬለ «DW» ከጀርመን ክፍል የባህል ዝግጅት ክፍል ጋዜጠኛ ሳቢነ ኦልዜ ለማኅበሩ ፕሬዚዳንት ኤከርት ኮነ ያቀረበ ጥያቄ ነበር። የጀርመኑ የቤተ-መዘክር ማኅበር ፕሬዚደንት ኤካርት ኮነ  እንደተናገሩት ከሆነ ቅርስን ለማስመለስ ትግል ለጀመሩት መልስ ለመስጠት የተካሄደ አይደለም።      

Dogon Ausstellung
ምስል Robert T. Wall

«መልስ መስጠት የሚገባን አይመስለኝም የሚል አመለካከት ነዉ ያለኝ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቅርስን ለመመለስ አልያም ጠብቆ ለማቆየት አሁን ያወጣነዉ መመርያ ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የወጣ ነዉ። የዚህ ተሻሽሎ የወጣዉ መመርያ ግብ  ቅርስ ከተወሰደባቸዉ ሃገራት የመጡ ማኅበረሰቡች በጉዳዩ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነዉ። መልስ ከመስጠት ጋር ምንም የተያያዘ ጉዳይ የለዉም» ከተለያዩ የዓለም ሃገራት የተዘረፉና በጀርመን ቤተ-መዘክሮች የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችን ለማስመለስ ብሔራዊ ፍላጎትን ብቻ ሳይሆን በተለይ ዓለምአቀፍ ግንዛቤን ያካተተ መመርያ መዉጣቱን የጀርመኑ የቤተ-መዘክር ሊቀመንበር ተናግረዋል። ይህ ምን ማለት ይሆን?         

«ይህ ማለት በተለያዩ ሃገራት ከሚገኙ ቤተ-መዘክሮች ከመጡ 12 ምሁራን ጋር አዉደ ጥናት አካሂደናል።  ተመራማሪዎቹ ከተለያዩ የዓለም ክፍላት መምጣታቸዉ ለኛ መሰረታዊ ነገር ነበር። ከነዚህ ተመራማሪዎች ጋር ባለፈዉ ዓመት ፀደይ ወራት ላይ ጠንከር ያለ አዉደ ጥናት አካሂደን ነበር። በአዉደ ጥናቱ ቅርስን ለመመለስ የሚያችለንን መመርያ ለማሻሻል ዳግም አዲስ መመርያን ለመፃፍ ችለናል። በዚህ አዲስ የተሻሻለዉ መመርያ መጠገን የማይችሉ ቅርሶች አልያም ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸዉ የተወሰኑ ቅርሶችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደመጡበት ሃገራት መመለስ ለማስቻል የወጣ ነዉ። በሌላ በኩል የተዘረፉ ቅርሶች ያሉባቸዉ ቤተ- መዘክሮች የቅኝ ግዛትን ዘመን እና ቅርሶችን ለጎብኝዎች  በምን መልኩ እያቀረቡ ነዉ የሚለዉ ነጥብም ከዉጭ ሃገራት የመጡ የሥራ ባልደረቦቻችን ያከሉበት ነጥብ ነዉ። »      

Älteste äthiopische Bibelhandschrift
ምስል DW/ A.T.Hahn

የጀርመኑ የቤተ-መዘክር ማኅበር ፕሬዚደንት ኤካርት ኮነ ለምሳሌ ይሉ በመቀጠል፤ «ለምሳሌ ቅርሶቹ በሚገኙባቸዉ ቤተ-መዘክሮች ስለቅርሶቹ ምነት ከየት እንደመጡ ሊገልፅ የሚችል ቅርሱ ከመጣበት ቦታ የሆነና እና ስለጉዳዩ በጥልቀት የሚያዉቅ ሰዉ ለመቅጠር ያለመ ነዉ። ይህ ማለት ባህሉን የሚያዉቅና ለቤተ-መዘክሩ ጎብኝዎች በደንብ እና በግልፅ ማስረዳት የሚችል ማለት ነዉ። በተጨማሪም ቅርሱ ወደ ጀርመን እንዴት ሊገባ እንደቻለ ስንት ጊዜ እንደሆነዉ ይህ ቅርስ ለመጣበት ሃገር ምን ማለት እንደሆነ ሁሉ የሚዘረዝር ይሆናል። ለምሳሌ ከአፍሪቃ የመጡ ጥንታዊ ቅርሶች የሚታይበት በሽቱትጋርት በሚገኘዉ ሊንድን ቤተ-መዘክር ዉስጥ አዲስ የአፍሪቃ ቅርሶች መመልከቻ ክፍል በቅርቡ ተከፍቶአል። በዚህ የቤተ- መዘክሩ ክፍል በአፍሪቃ በቅኝ ግዛትና ከቅኝ ግዛት በኋላ ያለዉን ታሪክ የሚተርኩ ቅርሶች ይገኛሉ። »

ከኢትዮጵያ በስርቆትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይ ወደ አዉሮጳ የገቡትን ታሪካዊ ቅርሶች ለማስመለስ ምን ያህል ጥረት ይደረግ ይሆን? በኢትዮጵያ ቅርስና ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ፈንታ በየነ እንደሚሉት ከሆነ ከኢትዮጵያ ተዘርፈዉ የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ እየተደረገ ያለዉ ጥረት በመስርያ ቤታቸዉ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሃገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤንባሲዎችም በኩል ሥራዉ ቀጥሎአል።

« እንደሚታወቀዉ ከሃገራችን በተለያዩ ምክንያቶች ከሃገራችን የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ የተለያዩ ጥረቶች ይካሄዳሉ። የሃገር ቅርስን ለማስመለስ በኢትዮጵያ ቅርስና ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ እንደ ሃገር ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለማስመለስ እየተንቀሳቀስን ነዉ ያለነዉ። ለምሳሌ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን መጥቀስ ይቻላል። በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤንባሲዎች እና ቆንስላ ጽ/ቤቶችም እንዲሁም በሃገር ቤት ከባህልና ቱሪዝም ሚ/ር ጋር በመተባበር እየሰራን እንገኛለን።»   

Dogon Ausstellung Dogon Trog
ምስል Robert T. Wall

ከኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘርፈዉ የሚወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ ጥረት እየተደረገ እየተሰራ ነዉ የሚል መልስን መስማት የተለመደ ነዉ። በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶችን እዉነት ለማስመለስ ምን ያህል እየተሰራ ነዉ? ምን ያህልስ እዉን ይሆናል ተብሎ ይታመናል?

«በርግጥ ከሃገር የተወሰዱ ቅርሶችን ለማስመለስ በዲፕሎማሲ መንገድ እንጂ የማስገደዱ ሁኔታ የማይቻል ነዉ። በዚህ ጉዳይ እየሰራን ነዉ። ቅርስን በተመለከተ በቅርቡ ኢትዮጵያ በሚገኘዉ የፈረንሳይ ኤንባሲ ዉይይት አካሂደን ነበር። በዉይይቱ ከፈረንሳዉያኑ ወገን እንደተነገረዉ፤ በአንደኛ ደረጃ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን ነዉ። በሒደት ግን በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ኤንባሲዎቻችን ጋር በመተባበር በዲፕሎማሲ በራሳቸዉ ፈቃድ እንደመልሱልን የማድረግ ስራን እየሰራን ነዉ። ከዚህ ወጭ በአሁኑ ወቅት የተሻለ አማራጭ የለንም። አሁን ለምሳሌ ቅድም እንደተናገርኩት በሱዳን የአፄ ዮሃንስ የራስ ቅል እንዳለ ይነገራል። እሱን ለማስመለስ እንደ የቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን፤ ለኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በደብዳቤ ልከን ራስ  ቅሉ እንዲመለስልን ስንል ደብዳቤ ጽፈንላቸዉ ነበር። መልሱን እየተጠባበቅን ነዉ።»   

በሱዳን የአፄ ዮሃንስ የራስ ቅል ይገኛልል ብለዉ ነበር ይህ ምን ያህል እዉነት ነዉ?

« ያዉ እኛም ከሚነገረዉ ነዉ። በርግጥ አጥንተን እና እርግጠኛ ሆነን አይደለም። ከዚህ በፊት የደርግ መንግሥት ሊቀመንበር የነበሩት መንግሥቱ ኃይለማርያም አንድ ወቅት ሱዳንን በጎበኙበት ወቅት፤ በሙዚየም ዉስጥ የአፄ ዮሃንስ ራስ ቅል እንደሚገኝ እንደተነገራቸዉ ተናግረዉ እንዲመለስ ሲሉ መናገራቸዉ ይታወቃል……»

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ