1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሰሞኑ፦የነፍጠኛ ጉዳይ፤ የኤልያስ ስንብት፤ የኖቤል ሽልማት

ዓርብ፣ መስከረም 30 2012

በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሳምንቱ ውስጥ ሲያነጋገሩ ከሰነበቱ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት የሳበው የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በኢሬቻ በዓል ላይ ያሰሙት ንግግር ነው። ለንግግሩ የተሰጡ የድጋፍ እና የተቃውሞ አስተያየቶች ሳምንቱን ሙሉ ዘልቀዋል። የኤልያስ መልካ ስንብት እና የኖቤል ሽልማትም አበይት ጉዳዮች ነበሩ።

https://p.dw.com/p/3RALf
Äthiopien Shimeles Abdisa
ምስል DW/Yohannes G. Egzihaber

ከሰሞኑ፦የነፍጠኛ ጉዳይ፤ የኤልያስ ስንብት፤ የኖቤል ሽልማት

ሁለቱም በተወከሉበት የፖለቲካ ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው። የ60ዎቹ ትውልድ ጎልቶ በሚታይበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በወጣትነታቸው የፖለቲካ ስልጣንን መቅመሳቸውም ያመሳስላቸዋል። የኦሮሚያ እና የአማራ ክልልን እያስተዳደሩ ባሉ  የእህትማማች ፓርቲዎች አባልነታቸው በገዢው ግንባር ኢህአዴግ ጥላ ስር ተጥልለዋል። በድርጅት መተሳሰራቸውን ለማመልከት “ጓድ” የሚለውን መጠሪያ ከስማቸው በፊት የሚያስቀድሙት ሁለት ፖለቲከኞች ከሰሞኑ በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው የገጠሙት እንካ ሰላንቲያ የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር። እኒህ ፖለቲከኞች የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲው (ኦዲፒ) አቶ ታዬ ደንደአ እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲው (አዴፓ) አቶ አሰማኸኝ አስረስ ናቸው። 

ሁለቱ ወጣት ፖለቲከኞችን  ወደ ንትርክ የከተተው ጉዳይ ባለፈው አርብ መስከረም 23 በተካሄደው የኢሬቻ በዓል ዋዜማ ስነ-ስርዓት ላይ የተደረገ ንግግር ነው። ንግግሩን በመስቀል አደባባይ ለተሰበሰቡ በሺህዎች ለሚቆጠሩ የበዓሉ ታዳሚያን በኦሮምኛ ቋንቋ ያሰሙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ናቸው። ጠንካር ያሉ ቃላትን ያዘለው የአቶ ሽመልስ ንግግር የአማርኛ ትርጉም ፌስ ቡክን በመሳሰሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በፍጥነት ነበር የተሰራጨው። 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው የተጠቀሙት “ነፍጠኛ” የሚለው አጠራር ውዝግብ ቀስቅሷል። አቶ ሽመልስ በንግግራቸው “ዛሬ የሰበረንን ሰብረን፣ ከስሩ ነቅለን፣ ኦሮሞ በተዋረደበት ቦታ ላይ ድል አድርጓል” የሚለው አገላለጻቸውም አስተችቷቸዋል። “ነፍጠኛ አገር አቀና እንጂ አገር አላጠፋም” ሲሉ የተሟገቱ ግለሰቦች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየቶቻቸውን አስፍረዋል።ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ የአዴፓው አሰማኸኝ “እኔ ነፍጠኛው ሲሰደብ ያመኛል። ምክንያቱም አማራ ነኝ። ነፍጠኞች ወልደው፣ የሀገር ፍቅርን አሳይተው ያሳደጉኝ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኢትዮጵያዊነትን በክብር ያወረሱኝም ነፍጠኞች ናቸው። እናም ባለማወቅም ሆነ ሆን ብለው አማራን በነፍጠኝነት የሚዘልፉትን ልታገስ አልችልም” ሲሉ በንግግሩ መከፋታቸውን በግልጽ አሳውቀዋል። 

Asemahegn Aseres
ምስል DW/A. Mekonnen

ሁናቸው ጌትነት የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ “የነፍጠኛ ታሪክ የሚያኮራ እንጂ የሚያሸማቅቅ አይደለም። ነፍጠኛ አባቶቻችን ከባርነት ነጻ ያወጡን ባለውለታዎቻችን ናቸው” ሲሉ ተመሳሳይ ሀሳባቸውን አጋርተዋል። ይልማ ኪዳኔ በዚያው በትዊተር “አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ጠብቀው ያስረከቡን ከተለያዩ ክፍሎች የመጡ ነፍጠኞች ምስጋና እንጂ ስድብ አይገባቸውም” ብለዋል። አበባው አምባዬ “ለአገር ነጻነት ሲባል ነፍጠኝነት ይለምልም” በሚል ርዕስ ስር በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “በነፍጠኞች አኩሪ ጀብድ፣ ፋሽስት ወራሪ ሐይል ቅስሙን በመስበር፣ ነጻነቷን ያረጋገጠችና እና ያስከበረች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች። ነፍጠኛ መሆን ክብር እና ጀግንነት እንጂ ወንጀል አይደለም” ሲሉ ተሟግተዋል።

ቃበታ ከሮርሳ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ“ሀገር በነፍጥ አትገነባም” ሲሉ መሰል አስተያየቶችን ተቃውመዋል። “እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ነው ለዘመናት በመካከላችን የማይድን ጠባሳ ያኖረው። ሀገር የምትገነባው በእውቀት ነው። ነፍጠኛ እንኳን ለሀገር ለወንድሙም አልጠቀመም” ብለዋል። ነፍጠኝነትን ከአርበኝነት ጋር ያመሳሰሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች “ነፍጠኛ ነኝ” የሚል በሃሽታግ የታጀበ ዘመቻም ማካሄዳቸውን የታዘቡት የኦዴፓው አቶ ታዬ ደንደአ ምላሽ ያሉትን በፌስ ቡክ ገጻቸው አስነብበዋል።

Taye Dendea
ምስል Geberu Godane

አቶ ታዬ የአዴፓውን አቶ አሰማኸኝ በስም ጠቅሰው ባሰፈሩት ጽሁፍ “በኢትዮጵያ ነፍጠኝነት እና አማራነት አንድ ስለመሆናቸዉ የሚተርክ አመለካከት የለም። ካለም ትክክል አይደለም” ሲሉ ተሟግተዋል። “ነፍጠኝነት የአገዛዝ ስርዓት ነዉ። ያ ስርዓት ደግሞ በአማራ ህዝብ ስም ነገደ እንጂ ለደሀው አማራ ጉዳት እንጂ ጥቅም አላመጣም። የአማራ ህዝብ ዛሬም ከወንድሞቹ እኩል ወይም ይበልጥ በድህነት እየማቀቀ ነዉ። የእዚህ ህዝብ ችግር ከህዝባችን ችግር እኩል ይሰማናል” ብለዋል አቶ ታዬ። “የነፍጠኛ ስርዓት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ውድመትን አስከትሏል። የህዝቦችን ቁሳዊ እና መንፈሳዊ መብቶችን በጭካኔ አጥፍቷል” ሲሉም ከስሰዋል።

ማዲ ዮናስ በትዊተር “ነፍጠኛ የአማራ አቻ ላለመሆኑማ ‘መሬት ላራሹን’ ከፊት ሆነው የመሩት ባለታሪኮች አማራዎችም [ጭምር] መሆናቸው ምስክር ነው። ነገር ግን ባለፉት 29 ዓመታት በኢህአዴግ ዘመን አውድ ነፍጠኛ እየተባለ ግፍ የተፈጸመበት አማራ ብቻ ነው” በማለት ተከራክረዋል። መንግስቱ ዲ. አሰፋ በማህበራዊ ድረገጾች ላይ የተመለከቱትን እና ባለስልጣናት ጭምር የተሳተፉበትን መካሰስ ተችተዋል። “ያለፈው [ነፍጠኛ እና ገባር የፈጠረውን] ሥርዓት በመውቀስም ኾነ ያለልክ የጽድቅ ጸሃይ አድርጎ መሳል ለኛ ምንም አይጠቅመንም። ታሪካችንን ፖለቲካ ከወረረው ይኸው ውለን አድረን ዛሬም እዚያው ነን። እናንት ወጣት መሪዎች እንዲህ ዝቅ ካላችኹስ የዚህች አገር ተስፋ ምንድን ነው? ኧረ ተረጋጉ” ሲሉ ባለስልጣናቱን መክረዋል። 

የአቶ ሽመልስ ንግግር ያስነሳው ውዝግብ በጋዜጠኛ እና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባ ባለ አደራ ቤት ምክር ቤት (ባልደራስ) ለጠራው ሰላማዊ ሰልፍ መቀስቀሻ ሲውል በማህበራዊ ድረገጾች ላይ ተስተውሏል። አቤል ሽመልስ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ “የሽመልስ አብዲሳን ንግግር ሰምተህ የእስክንድርን ባልደራስ አለመደገፍ እንዴት ይቻላል?” ሲሉ ጠይቀዋል። የሀሳቡ ደጋፊዎች በመጪው እሁድ ጥቅምት 2 ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ሰላማዊ ሰልፍ እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶችን የሚያሳዩ ፎቶዎችን በየገጾቻቸው ሲያጋሩ ታይተዋል።በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ በደማቅ ሁኔታ የተከበረው የኢሬቻ በዓል እና ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የተነሳው ውዝግብ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተቆጣጠረበት በዚህ ሳምንት የብዙዎች መነጋገሪያ የነበረው ሌላው ጉዳይ የዕውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ የኤልያስ መልካ ህልፈት ነበር። የዛሬ ሳምንት መስከረም 23 ምሽት ህይወቱ ያለፈው እና ባለፈው ሰኞ ስርዓተ ቀብሩ የተፈጸመው ኤልያስ በብዙ ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ አፍቃሪያን ተዘክሯል። ከ400 በላይ ዘፈኖችን እንዳቀናበረ የተነገረለት ኤልያስን ከስራዎቹ ባሻገር በበጎ ስራዎቹ እና የህይወት ፍልስፍናው ምሳሌ እንደነበር ብዙዎች መሰክረዋል።

Äthiopien Musiker Elias Melka
ምስል Privat

ዓና የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ “ኤልያስ መልካ በ50 ወይ በ100 ዓመት አንድ ጊዜ የሚፈጠር፣ ልዩ ጥበብ የተካነ ጀግና ሰው ነበር” ሲሉ አወድሰውታል። “በተባረኩ ጣቶቹ ሙዚቃን ነፍስ የዘራባት ጎበዝ አረፈ። ኤልያስ መልካ ታጎድለናለህ፤ በሰላም እረፍ!” ሲሉ ሀዘናቸውን የገለጹት ደግሞ አዴሞ የተሰኙ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው። የፊልም ባለሙያው ዳዊት ተስፋዬ በበኩሉ ኤልያስን “የሰው ልክ፣ የሙዚቃ አድባር፣ የብርሃን ልጅ ” ሲል በትዊተር መልዕክቱ ገልጾታል። 

ሄኖክ ለማ በፌስ ቡክ “በጥበብ የእውነትን መንገድ ለመሄድ ፦ ብዙ የሚያደክም፣ ብዙ የሚያሰንፍ፣ ብዙ የሚያዝል፣ ብዙ የሚፈትን፣ ብዙ የሚያስከፍል፣ ተስፋን የሚያስቆርጥ ፈተና ባለበት በዚህ ስፍራ፤ የሚያጓጓው፣ የሚጣፍጠው፣ የሚያስጎመዠው፣ በቀላሉ የሚያስወድደው፣ በቀላሉ የሚያስሞግሰው፣ በቀላሉ የሚያቀማጥለው ዕንቁ ነገር በየደቂቃው ደጅን በሚያንኳኳበት፦ ለአቋሙ፣ ለህልሙ፣ ለእምነቱ በህይወቱ ምርጫን የመረጠ ፤ ምርጫውንም የኖረ የማይቻለውን መቻያ ምሳሌ ነው ኤልያስ መልካ” ሲል ዕውቁን የሙዚቃ ሰው አስታውሶታል።ጋዜጠኛ  ቆንጂት ተሾመም “ኤልያስ መልካ ለጥበብ ታማኝነቱን ሳያጎድል አርፏል። ለእምነቱም ሐቀኛ ነበር” ስትል ምስክርነቷን ሰጥታለች።

ዘሚኪ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ “ያደግንባቸው፣ የጎረመስንባቸው፣ ብዙ የፍቅር፣ የደስታ፣ የሃዘን ጊዜዎችን ካለፍንባቸው የ90ዎቹ ስራዎች ጋር ሁሌም በልባችን ትኖራለህ። ሞት ለማንም ባይቀርም በስራዎችህ ህያው ሆነህ ትኖራለህ” ሲሉ ለኤልያስ መልካ የስንብትን መልዕክታቸውን አሰፍረዋል። 

Friedensnobelpreis 2019 an Abiy Ahmed | Bekanntgabe in Oslo durch Berit Reiss-Andersen
ምስል Reuters/NTB Scanpix/Stian Lysberg Solum

በበዓል ስሜት፣ በውዝግብ እና በሀዘን ሲላጉ ሳምንቱን ያሳለፉ ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች በዛሬው ዕለት ከኖርዌይ ኦስሎ በሰሙት ዜና ደስታ፣ ተስፋ እና ስጋታቸውን በስፋት ሲያጋሩ ውለዋል። መቀመጫውን በኦስሎ ያደረገው የኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የእዚህ ዓመት አሸናፊ መሆናቸውን ባሳወቀ በደቂቃዎች ውስጥ በርካቶች ደስታቸውን ገልጸዋል።

በላቸው መኩሪያ በትዊተር “በአንድ ወቅት የድህነት ማሳያ ተደርጋ ከምትነሳ ሀገር የመጣ ሰው፤ ተደማጭነት ያለው ሰላም አምጪ እና የለውጥ አነሳሽ በመሆን፤ ከፍተኛ ክብር ላለው ዓለም አቀፍ ሽልማት ተገቢውን ዕውቅና ማግኘቱን አልፍሬድ ኖቤል በህይወት ኖሮ ይህን ቢመለከት እንዴት ይኮራ” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ”ለኢትዮጵያ ታላቅ ዕለት” ሲል ሀሳቡን ያጋራው ጋዜጠኛ  አብይ ተክለማርያም የዛሬው ሽልማት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣናቸው የመጀመሪያዎቹ ወራት ላስመዘገቡት ስኬት የተበረከተ መሆኑን ጠቅሷል። “ሽልማቱ ያንን መተማመን፣ ርዕይ እና ቁርጠኝነት መልሶ እንዲያገኙ ያበረታታቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል። 

“ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሽልማቱ ይገባቸዋል” የሚል አቋም ያላቸው ቃልኪዳን ካሳዬ ሽልማቱ “ለሀገራችን ሰላም ይበልጥ ተግተው እንዲሰሩ ያደርግዎታል የሚል ተስፋ አለኝ” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል። ረድኤት ታምሬ በፌስ ቡክ ገጻቸው ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀዋል። “ይሄ ሽልማት በሀገር ውስጥ እየተፈጠረ ካለው ውጥንቅ ለአፍታም ቢሆን የሚያዘናጋ ሳይሆን ነገሮችን ቆም ብሎ መርምሮ አፋጣኝ እና ደፋር የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚጠቅም በር ከፋች እድል እንዲሆን እንመኛለን” ሲሉ የደስታ መግለጫ መልዕከታቸውን አስተላልፈዋል።

Friedensnobelpreis 2019 Äthiopien | Ministerpräsident Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/dpa/B. Pedersen

ኤልዛቤት ገብረክርስቶስ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ሸላሚዎቹ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር በኢትዮጵያ የተከሰቱ ችግሮችን ከግምት ማስገባታቸው ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ አንስተዋል። ሸላሚዎቹ “በእርሳቸው ሀገር ለተከሰተው ሞት፣ መፈናቀል እና አለመረጋጋት ግድ የላቸውም ማለት ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። “አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማትን ባያሸነፉ ነበር የሚደንቀኝ” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው የጻፉት ኢዛና ሃዲስ ምክንያቱ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምዕራባውያን የሚፈልጉትን ሁሉንም ነገሮች በማከናወናቸው መሆኑን አብራርተዋል። “እርሳቸው ምዕራቡ ለእኛ በትክክል የሚሹልን ናቸው። የኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እና የተቀባቡ የፖለቲካ ለውጦችን የሚያስተጋቡ ናቸው። የምዕራቡን ፍላጎት ለማርካት ያደረጉት ጥረት ከፍሏቸዋል” ብለዋል። 

መላዕከ ጸሀይ አበራ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ሽልማቱን ከኢትዮጵያ ጋር አያይዘውታል። “ኢትዮጵያ ወደቀች ሲባል እየተነሳች፣ ዛሬም ለወደፊቱም በልጆቿ ከፍ ብላ ትታያለች” ብለዋል ጸሀፊው የኖቤል የሰላም ሽልማቱን ተከትሎ በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት። 

ተስፋለም ወልደየስ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ