1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከምዕራብ ወለጋ ሸሽተው አሶሳ የተጠለሉ ተፈናቃዮች አቤቱታ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 18 2014

በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳና አካባቢው ባለፈው ሳምንት ከተፈጸመ ጥቃት ሸሽተው አሶሳ የተጠለሉ ተፈናቃዮች መንግሥት ዕገዛ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ። የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ ከምዕራብ ወለጋ ዞን ሸሽተው በአሶሳ የተጠለሉ ከ2 ሺሕ 300 በላይ ተፈናቃዮች መመዝገባቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል

https://p.dw.com/p/43ZNw
Äthiopien Assosa Flüchtlinge
ምስል Negassa Dessalegn/DW

ከምዕራብ ወለጋ ሸሽተው አሶሳ የተጠለሉ ተፈናቃዮች አቤቱታ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ባቦ ጋምቤል ወረዳ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ህዳር 7 ቀን 2014 ዓ.ም ተፈጠረ በተባለው ግጭት ከ2ሺ በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተጠልለው ይገኛሉ። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች እንደተገናገሩት አሶሳ ከደረሱ ስድስት ቀናት የሆናቸው ሲሆን ከከተማው ማህበረሰብ በስተቀር ምንም ዓይነት ድጋፍ አላገኙም። ተፈናቃዮቹ መንግስት ድጋፍ እንዲደርገላቸውም ጠይቀዋል። በባቦ ጋምቤል ተፈጠረ በተባለ ጥቃት በርካቶች የቤተሰብ አባላታቸውን ማጣታቸውንም ተናግረዋል። 

አቶ ጌታሁን ዘውዱ በምእራብ ወለጋ ቦኒ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በወረዳው ቦኒ ቀበሌና ሌሎች ስፋራዎች ውስጥ ተፈጠረ በተባለ ጥቃት ተፈናቅለው ወደ አሶሳ ከተሻገሩት ዜጎች መካከል ናቸው። በወረዳው በተፈጠረው ግጭትም በርካቶች የገቡበት እንደማይታወቅ ገልጸዋል። አንድ ሺ የሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎችም ከአምስት ቀናት በፊት አሶሳ ከተማ የደረሱ ሲሆን በመንገድም  ቁጥራቸው በውል የማታወቅ ዜጎች መታገታቸውን ጠቁመዋል። 

Äthiopien Assosa Flüchtlinge
በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳና አካባቢው ባለፈው ሳምንት ከተፈጸመ ጥቃት ሸሽተው አሶሳ የተጠለሉ ተፈናቃዮች መንግሥት ዕገዛ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ።ምስል Negassa Dessalegn/DW

ከምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምበል ወረዳ ሙሜ ድልቢ ከተባለ ቀበሌ ወደ አሶሳ እንደሸሹ የሚናገሩት አቶ ትእዛዙ አራጌና ሌሎች ባለፈው ማክሰኞ ህዳር 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚኖሩበት ቀበሌ በተፈጠረው ግጭት መፈናቀላቸውን ተናግረዋል። ቀድሞ ከነበሩበት ቀዬ ወደ አሶሳ ከሸሹት ውጪ በርካታ አቅመ ደካሞች በስፍራው ጉዳት እንደረሰባቸውም ጠቁመዋል። ነዋሪውም ምንም ዓይነት ንብረቱን ሳይዝ ከስፍራው መሸሹንም ተናግረዋል። ቤተሰቦቻቸው የጠፉባቸው ዜጎችም መንግስት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ጉዳት አድራሾች ላይ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።

Äthiopien Assosa Flüchtlinge
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ ከምዕራብ ወለጋ ዞን ሸሽተው በአሶሳ የተጠለሉ ከ2 ሺሕ 300 በላይ ተፈናቃዮች መመዝገባቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋልምስል Negassa Dessalegn/DW

በአካባቢው ተከሰተ የተባለው ጥቃት አስመልክቶ ከምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደር በስልክ ማብራርያ ለመጠየቅ የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ ከምእራብ ወለጋ  ዞን የተያዩ ወረዳዎች ወደ አሶሳ ከተማ የሸሹ ከ2ሺ በላይ ዜጎች መኖራቸውን አብራርተዋል።  

የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከዚህ ቀደም በሰጠው ማብራሪያ ከምዕራብ ወለጋ የተለያዩ ወረዳዎች ከ10ሺ በላይ ዜጎች ወደ አሶሳ ዞን መሻገራቸውን አስታውቆ ነበር።  ከ2 ሳምንት በፊት ከ3ሺ በላይ ዜጎች ደግሞ ከዞኑ ቤጊና ቆንዳላ ከተባሉ ወረዳዎች መፈናቀላቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ነጋሳ ደሳለኝ
እሸቴ በቀለ