1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኅብረተ ሰብየመካከለኛው ምሥራቅ

ከሊባኖስ ለመመለስ ከ3000 በላይ "ሰነድ አልባ"ኢትዮጵያውያን ተመዝግበው እየጠበቁ ነው

ረቡዕ፣ ጥቅምት 11 2013

"ሰነድ አልባ የሆኑ ልጆችን ወደ አገር ቤት የመመለስ ምዝገባ አሁን ለዘጠነኛ ዙር ነው የተሰራው። ከዚህ በፊት ስምንት ጊዜ ተሰርቷል" ያሉት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ቆንሱል ጄኔራል አቶ ተመስገን ኡመር ለዶይቼ ቬለ እንዳስረዱት በአንድ ሳምንት 3 ሺህ 289 ኢትዮጵያውያን ተመዝግበዋል።

https://p.dw.com/p/3kFV1
Libanon Beirut | entlassene Haushaltshilfen aus Äthiopien
ምስል Mekdes Ylima

በኤኮኖሚያዊ ቀውስ ከላሸቀችው ሊባኖስ ከ3000 በላይ "ሰነድ አልባ" ኢትዮጵያውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ በቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ቆንሱል ጄኔራል አቶ ተመስገን ኡመር ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። 

መቀመጫውን በቤይሩት ከተማ ያደረገው ቆንስላ ጽህፈት ቤት ባለፈው ነሐሴ ባደረገው ዘጠነኛ ዙር ምዝገባ በአጠቃላይ 3 ሺህ 289 ዜጎች መመዝገቡን አቶ ተመስገን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምዝገባው ተቋርጦ የቆየ ሲሆን በቅርቡ አስረኛ ዙር እንደሚጀመር የገለጹት አቶ ተመስገን ቁጥሩ እንደሚጨምር ይጠብቃሉ።

"ሰነድ አልባ የሆኑ ልጆችን ወደ አገር ቤት የመመለስ ምዝገባ አሁን ለዘጠነኛ ዙር ነው የተሰራው። ከዚህ በፊት ስምንት ጊዜ ተሰርቷል" ያሉት አቶ ተመስገን ለዶይቼ ቬለ እንዳስረዱት በአንድ ሳምንት ብቻ 3 ሺህ 289 ኢትዮጵያውያን ተመዝግበዋል። ከእነዚህ መካከል 123 ኢትዮጵያውያን ዛሬ አዲስ አበባ ደርሰዋል። 

ሊባኖስ በገጠማት ኤኮኖሚያዊ ቀውስ፣ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ እና በቅርቡ በቤይሩት ከተማ ተከስቶ የነበረው ፍንዳታ ባስከተለው ጫና ምክንያት የአገሪቱ ዜጎች ኢትዮጵያውያንን እየቀጠሯቸው እንዳልሆነ ያስረዱት አቶ ተመስገን "ራሳቸው ያመጧቸውንም ልጆች ደሞዝ እየከፈሉ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

"ከአሠሪዎቻቸው ሸሽተው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቤት ኪራይ ምግብ እና የተለያዩ ወጪዎችን በራሳቸው ነው መቻል ያለባቸው፤  ሥራ ሲያገኙ ነው የሚሰሩት፤ አሁን ካለው ኹኔታ አንፃር እጅግ ተጋላጭ ናቸው። ምክንያቱም በፊት ነፃ ነበሩ። ቤት ከተቆለፈባቸው ይሻላሉ። አሁን ግን አመት ያህል ሥራ አልሰሩም" ያሉት አቶ ተመስገን  "እንወጣለን ብለው መጮህ ከጀመሩ አመት ገደማ ሆኗል"  ብለዋል።

Libanon Beirut Migranten-Arbeiter | Protest vor Konsulat von Kenia
ወደ 250,000 የሚገመቱ የቤት ሰራተኞች በሊባኖስ እንደሚገኙ ይገመታል። አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን፣ የፊሊፒንስ እና የስሪ ላንካ ዜጎች ናቸው። የኬንያ እና የሴራ ሊዮን ዜጎችም ይገኛሉምስል Anwar Amro/AFP

እንደ አቶ ተመስገን ከሆነ ለኢትዮጵያውያኑ ጉዞ የሊባኖስ መንግሥት የኢሚግሬሽን እና ደሕንነት መስሪያ ቤት ያለው አሰራር "ትልቅ እንቅፋት" ሆኗል። "ለእያንዳንዷ ልጅ መቼ [ወደ ሊባኖስ] ገባች፤ ፓስፖርት ቁጥሯ ምንድነው? ማን ጋር ትሰራ ነበር? ተከሳለች ወይ አልተከሰሰችም? በአገሪቱ በሌላ ወንጀል ትፈለጋለች? አትፈለግም? የሚሉ መረጃዎች ይሰበስባሉ። ያ በእጅ ነው የሚፃፈው። ያን ሰርተው፤ አጣርተው እነዚህ ልጆች መሔድ ይችላሉ ብለው ሲመልሱልን ጊዜያዊ የጉዞ ሰነድ (ሊሴ ፓሴ) እናዘጋጃለን" ሲሉ ሒደቱን አስረድተዋል።

አቶ ተመስገን እንደሚሉት ቆንስላው ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንን ሰነድ ካዘጋጀ በኋላ የመውጪያ ቪዛ ለማግኘት መልሶ ለሊባኖስ መንግሥት ጥያቄ ያቀርባል። ይሁንና ሒደቱ ረዥም ጊዜ ይፈጃል። "ባለው ልምዳችን እንኳ ወደ አራት መቶ ልጆች ለማስወጣት በሶስት ወር፤ በአራት ወር ቪዛ አታገኝም" ይላሉ።

የኢትዮጵያ ቆንስላ ሒደቱ የሚፋጠንበትን መንገድ ለማበጀት ካደረገው ጥረት በኋላ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ለሊባኖስ ፕሬዝዳንት ሚሼል ኦውን የችግሩን ጥልቀት የሚገልጽ ደብዳቤ መፃፋቸው ዕገዛ እንዳደረገ አቶ ተመስገን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያኑ ዶላር፣ ሥራ እና መመለሻ በጠፋባት ሊባኖስ

ወደ አገራቸው ለመመለስ ሲወተውቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የሚመለሱት በመደበኛ የአውሮፕላን በረራ ነው። የተመላሾቹን ጉዞ በማመቻቸው በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን የገለጹት አቶ ተመስገን ከተመለሱት 132 ሰዎች በተጨማሪ "ዛሬም የሚሔዱ አሉ። በየቀኑ በአንድ በረራ ከመቶ በላይ ሰው እየሆነ ነው የሚሔደው" ብለዋል።

"አስረኛ ዙር የዚህን ያህል ቁጥር ይመጣል ብዬ እጠብቃለሁ። ምክንያቱም ብዙዎቹ እየጠየቁ ናቸው። የአገሪቷም የኤኮኖሚ ኹኔታ ወደ ነበረበት ሊመለስ የሚችልበት ኹኔታ እያሳየ አይደለም። የኮቪድ ኹኔታ ቀጥሏል። ኤኮኖሚው አሁንም እንደተቀዛቀዘ ነው ያለው" ይላሉ አቶ ተመስገን።

በሊባኖስ በቀጣሪዎቻቸው ቤት የሚገኙም ሆነ በግላቸው የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ነባራዊ ኹኔታ ምክንያት ለቀው እንዲወጡ የመገደዳቸው ዕድል ከፍተኛ ነው።

"አሁን ይኸንን ካጋመስን ለምዝገባ ማስታወቂያ እናወጣለን። ብዙ ኢትዮጵያውያን ይወጣሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው" ያሉት አቶ ተመስገን ከአስር ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን እንደሚመዘገቡ ይጠብቃሉ።

በአሰሪዎቻቸው የሚጣሉት ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ

"የመሔድ ውሳኔያቸውን የሚለውጥ ነገር ቢያንስ በሚቀጥሉት ሶስት አራት ወራት ይመጣል ብዬ አላስብም" የሚሉት ኃላፊው ለጉዞ መክፈል የማይችሉ ወደ ኋላ ሊቀሩ እንደሚችሉ ያሰጋቸዋል።

"የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ እና የተለያዩ ቡድኖች አሉ። እነዚህ በራሳቸው ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ አለ። በጣም [የተቸገሩትን] የሚያግዛቸው አካል ከሌለ እኛም ወደላይ ማቅረባችን አይቀርም። እስካሁን ባለው ሁኔታ አብዛኞቹ በራሳቸው ነው ከፍለው እየሔዱ ያሉት። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ወደ ኋላ የሚቀሩ ይኖራሉ። ለእነዚህ ከኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ጋር መፍትሔ እየፈለግን ነው ያለንው" ብለዋል።   

እሸቴ በቀለ