1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እውን ከብርሃን የሚፈጥን አለ?

ሐሙስ፣ የካቲት 22 2004

ከብርሃን የሚፈጥን አንዳች ነገር የለም ተባለ። የአልበርት አይንሽታይን ፤ የፊዚክስ ቀመር እስካሁን አልተሻረም! የፀሐይ ብርሃን 150 ሚሊዮን ኪሎሜትር አቋርጦ ፣ በ 8 ደቂቃ ውስጥ በምድራችን ላይ እንደሚፈነጥቅና፣ ብርሃን ከመስጠት ባሻገር

https://p.dw.com/p/14CC2
ምስል AP

ምድሪቱንም እንደሚያሞቅ የታወቀ ነው። ከብርሃን የሚፈጥን ምንም ነገር እንደሌላ ለአያሌ ዓመታት የተረጋገለጥትን ጉዳይ፣ የአውሮፓ የኒክልየር ምርምር ድርጅት ባለፈው መስከረም በአንድ 1/60 ቪሊዮንኛ ሴኮንድ የአቶም ቅንጣት ክፍልፋዮች (ኒውትሪኖስ) ይፈጥናሉ ሲል መግለጫ አውጥቶ እንደነበረ ቢታወስም፣ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ እንዳስታወቀው እርግጠኛ አለመሆኑን አስገንዝቧል። CERN እንዳለው ፣ የተጠቀሰው ውጤት የተመዘገበው በትክክል «ሶኬት» ውስጥ ባልተሰካ የኤልክትሪክ ሽቦ አማካኝነት ነው። ስለሆነም ፍተሻው በሚመጣው ግንቦት እንደገና እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዟል።

ጥቂት የፍጥረተ ዓለም ገንቢ ስለሚባለው የቁስ አካል ኢምንት ቅንጣትና ብርሃን ፣

አዎ፣ በተደጋጋሚ እንደሚባለው ፍጥረተ ዓለም ፣ ከ 13 ,7 ቢሊዮን ዓመት በፊት ነው በ«ታላቁ ፍንዳታ » በአንድ ሺህኛ ሴኮንድ ውስጥ ሊከሠት የቻለው ። ቁስ አካል ፤ እሳት የሚተፉ ከዋክብት፣ የራዱ ፕላኔቶች፤ ሁሉም የተገኘው በዚሁ እጅግ ኃይለኛ ፍንዳታ (Big Bang)አማካኝነት ነው። ለፍንዳታ ያበቃውን እሳት ማን ፣ ምን ጫረው? ለዚህ ጥያቄ ፤ ከሥነ ፍጥረት ጠበብት መልስ የማግኘቱ ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ የሚነገር የሚቀመር ፤ የሚሰላ፤ የሚኮሰል ጉዳይም አይደል!

ፍጥረተ ዓለም ፤ ሀድ የለውም ! ወርድና ስፋቱ የት እየሌሌ ነው። ከአድማስ -አድማስ የሆነው ሆኖ፤ በአሁኑ ጊዜ ርዝመቱ 40 ቢሊዮን የብርሃን ዓመት መሆኑ ነው የሚነገርለት! በብርሃን ዓመት በሚቆጠርበት ርቀት የሚገኙ ሌሎች ዓለማትን የማሳሱ ጉዳይ ህልም እንጂ ገሐዳዊ ሊሆን መቻሉ፣ እጅግ ነው የሚያጠራጥረው።

ፍጥረተ ዓለም ፤ ደርዝ፤ ሥርዓት፤ የራሱ ስሌት ያለው ነው። እርግጥ፤ ከኛ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እምብዛም ሊጣጣም የማይችል ፤ እጅግ በላቀ ሁኔታ የተወሳሰበ መሆኑ ነው የሚነገርለት። የተፈጥሮ ሳይንስ ጠበብት የሚሰጡት ትንታኔ ከሂሳብ ቅመራው አያፈነግጥም። በማይዳሰሰውም ሆነ በጭብጡ ዓለም ፤ ቀመሩ ፤ ብዙውን ጊዜ ከእውነታ

አይርቅም። እንዲያውም አንዳንድ የፊዚክስ ሊቃውንት ፍጥረተ ዓለም በአጠቃላይ የሂሳብ ቀመር ነው ባዮች ናቸው።

ያም ሆኖ ፣ አንዲት ኢምንት ቅንጣት፣ ለፍጥርተ-ዓለም መዘርጋት፤ ለፍጥረተ ዓለም ቁስ አካላት ግኝት፣ መሠረት ሆኗል የሚለው ነባቤ-ቃል፣ እስካሁን ሊቀ-ሊቃውንቱን ሁሉ እንዳስደከረ መገኘቱ ሐቅ ነው። በሳይንስና ቴክኖሎጂ የገሠገሡ ታላላቅ መንግሥታት ፣ እዚህም ላይ በአውሮፓ፣ 21 መንግሥታትን ያስተሣሠረው የአውሮፓውያን የኑክልየር ተመራማሪ ድርጅት (CERN)ባለፉት 22 ወራት፤ የፍጥረተ- ዓለምን ምሥጢር አገኛለሁ ብሎ የተያያዘውን የቤተ-ሙከራ ምርምር እንደገፋበት ነው። በታዋቂው የብሪታንያ የፊዚክስ ሊቅ፤ የ 83 ዓመቱ አዛውንት ፒትር ሂግስ ስም፤ የሚጠራውን «ሒግስ-ቦሰን» ማለትም የአቶም ክፋይ የሆነውን ፣ የፍጥረተ ዓለም ገንቢ ጡብ ወይም የእግዚአብሔር ቅንጣት እየተባለ የሚነገርለትን ኢምንት ቁስ አካል በቤተ-ሙከራ ምርምር አማካኝነት ለማግኘት ፤ እንደተባለው ጥረቱ ይደረግ እንጂ እስካሁን የተሳካ ውጤት ማግኘት አልተቻለም።

የተባለው ቅንጣት፤ ከታላቁ ፍንዳታ በኋላ፣ ለከዋክብትና ፕላኔቶች መፈጠር መሠረት በመጣል ፣ ህይወት ያለው ነገር እንዲገኝ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረም ነው የሚነገረው።

የእግዚአብሔር ቅንጣት የተሰኘውን አባባል በመሠረቱ፤ ሳይንቲስቶች አይስማሙበትም። ይህ አባባል በፍጹም ሳይንሳዊ አገላለጽ እንዳልሆነ ጠበብቱ ያምናሉ።

ግራም ነፈሰ ቀኝ፤ የፊዚክስ ሊቅ ፒትር ሂግስ ፣ እ ጎ አ በ 1964 ዓ ም ፣ የ ፍጥረተ ዓለም ገንቢ ጡብ ስለተባለው «ሂግስ ቦሰን» የሠነዘሩት ነባቤ-ቃል፣ ተጨባጭነት ያለው ነው? አይደለም? እስከመጨረሻው ምርምሩ በ CERN የሚቀጥል ይሆናል።

በፈረንሳይና እስዊትስዘርላንድ ድንበር ላይ በሚገኘው በትኅተ-ምድር 100 ሜትር ጥልቀት ውስጥ በተገነባው 27 ኪሎሜትር ዙሪያ ጥምጥም መሿለኪያ ድልድይ መሰል ቦታ ላይ የሚገኘው የአውሮፓውያኑ የኑክልየር ምርምር ጣቢያ(CERN) ፤ ባለፈው መስከረም ወር 3ኛ ሳምንት ላይ የአቶም ንዑሳን ቅንጣቶች (ንውትሪኖስ)ከሞላ ጎደል ከብርሃን ፍጥነት በላቀ ሁኔታ እንደሚመጥቁ አስታወቆ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን ፤ ውጤቱ ፤መቶ- በመቶ በማያስተማምነበት አጠራጣሪ ሁኔታ መግለጫ መስጠቱ ትክክል እንዳልሆነ ያኔም ቢሆን የተቃወሙ ጠበብት እንደነበሩ ተመልክቷል። ከእነርሱም መካካል አንዷ፣ በሃምበርግ ዩኒቨርስቲ የሚገኙት የፊዚክስ ምሁር Caren Hagner ናቸው።

ከብርሃን የሚፈጥን ምንም እንደሌለ ፣ የአእማቱም ሆነ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አይንሽታይን ፣ እ ጎ አ በ 1905 ዓ ም፤ የስበት ኃይል፤ ጊዜ ፤ የኃይል ምንጭና ቁስ አካል በተጣመሩበት ቅመራው ማረጋገጡ የታወቀ ሲሆን፣ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው፣ የአውሮፓው የኑክልየር ምርምር ጣቢያ(CERN)፣ ባለፈው መስከረም፤ ኢምንት የአቶም ቅንጣቶች «ኒውትሪኖስ» ከብርሃን ፍንጠቃ ፤ በ 60 ቢሊዮንኛ ሴኮንድ ፈጥነው ይንቀሳቀሳሉ በማለት ማስታወቁ ፤ በእርግጥም የተቻኮለ መግለጫ ነበር። ምንም በሌለበት ባዶ ቦታ (አየር ጭምር) ብርሃን ፣ ከሞላ ጎደል፣ በሴኮንድ 300,000 ኪሎሜትር ነው የሚፈነጥቀው።

የዓእማቱ ታላቅ ሳይንቲስት አልበርት አይንሽታይን ከብርሃን የሚፈጥን አለመኖሩን በምርምር ተመርኩዞ የቀመረው የፊዚክስ ነባቤ ቃል የሚሻር ከሆነ፤ በኅዋ ርቀትን ለማመላከት እንደመለኪያ የተወሰደውና «የብርሃን ዓመት» እየተባለ የሚጠቀሰውንም መለወጥ ግድ ይሆናል በማለት በዚህ ክፍለ ጊዜ አስተያየት መሠንዘራችንም ይታወስ ይሆናል።

ፍጥረተ ዓለም መጠኑ እጅግ እየሰፋና ፍጥነቱም እጅግ እየናረ በመሄድ ላይ መሆኑን ፤ በዚህ የምርምር ዘርፍ ላይ ያተኮሩ ጠበብት ይናገራሉ።

ፍጥረተ ዓለምን የሚያከንፈው፣ ከፍጥረተ ዓለም ዐበይት ምሥጢራት አንዱ መሆኑ የሚነገርለት፣ «ጽልመታዊ ኀይል (Dark Energy) የሚሰኘው ነው ። ይህ ደግሞ ፍጥረተ ዓለም ፣ መገመት በሚያዳግት ፍጥነት በሚጓዝበት የማያልቅ ጉዞ፣ ፕላኔታችን፤ ምድርና በውስጥዋና በላይዋ የሚኖረው ፍጡር ፤ ጸሐይና አጫፋሪዎቿ ፕላኔቶች፤ ጨረቃዎች፤ ስብርባሪ ከዋክብት ፤ በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ የሚገኙበት የኅዋ ቀጣና ፤ ፍኖተ ኀሊብ (MILKY WAY)በሰዓት 2,1 ሚሊዮን ኪሎሜትር ነው የሚከንፈው።

የ CERN ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ጀርመናዊው ሮልፍ ዲተር ሆየር ፣ በሚመጣው ግንቦት እንደገና የምርምሩ ሙከራ ተከናውኖ ፣ «ሂግስ-ቦሰንን ነጥሎ ማግኘት ቢቻል ምን ማወቅ እንችላልን? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲያብራሩ፣

«በመጀመሪያ፣ በአቶም ፊዚክስ ረገድ አንዱን የምርምር መንገድ የደረስንበት መሆኑን እናረጋግጣለን። ይህም፣ በፍጥረተ ዓለም፤ ዩኒቨርስ፤ ከ 4 እስከ 5 ከመቶ ቁስ አካልን የኃይል ምንጭ ክምችትን፤ ለማወቅ ይረዳናል። 95,96 ከመቶው ዩኒቨርስ በጽልመታዊ ቁስ አካል ጽልመታዊ የኃይል ምንጭ የተሞላ ነው። ሩቡ ጽልመታዊ ቁስ አካልዩኒቨርስን ለያይቶ የሚያከንፈው ነው። በዩኒቨርስ፣ ገና 96 ከመቶውን ቁስ አካልና የኃይል ምንጭ መገንዘብ ይኖርብናል። በሚመጡት 20 ዓመታት ብዙ ሥራ ነው የሚጠብቀን። ስለሆነም፣ ምርምራችን ተጠናክሮ መቀጠልይኖርበታል »ብለዋል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ