1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እስራኤል-ዩናይትድ ስቴትስና የእየሩሳሌም ነዋሪዎች

ዓርብ፣ ሚያዝያ 15 2002

ምሥራቃዊ እየሩሳሌም ዉስጥ 200 000 አይሁዳዉያን፥ 260 000 ፍልስጤማዉያን ይኖራሉ።ራማት ሽሎሞን የተባለዉ የአይሁድ መኖሪያ ሠፈር ንፁሕ እና ዘመናይ ነዉ

https://p.dw.com/p/N4qn
ሠፈራ መንደሩምስል AP

22 04 10

እስራኤል ምሥራቃዊ እየሩሳሌም ዉስጥ አዳዲስ የአይሁድ መኖሪያ መንደሮች ለመገንባት ያሳለፈችዉን ዉሳኔ እንድታጥፍ ዩናይትድ ስቴትስ ያቀረበችዉን ጥያቄ በድጋሚ ዉድቅ አድርጋዋለች።ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትናያሁና ባለሥልጣኖቻቸዉ የሠፈራ-መንደር ለማስገንባት ከያዙት አቋም ፈቅ አላሉም። የእስራኤል ባለሥልጣናት መላዋ እየሩሳሌም የእስራኤል ርዕሠ-ከተማ ነች እንዳሉም ነዉ። ምሥራቃዊ እየሩሳሌምን የጎበኘዉ ክሌመንስ ፈርክኖተ ያካባቢዉን ነዋሪዎች አነጋግሮ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።
ምሥራቃዊ እየሩሳሌም ዉስጥ 200 000 አይሁዳዉያን፥ 260 000 ፍልስጤማዉያን ይኖራሉ።ራማት ሽሎሞን የተባለዉ የአይሁድ መኖሪያ ሠፈር ንፁሕ እና ዘመናይ ነዉ።አስራ-አምስት ሺሕ ከሚሆኑት ነዋሪዎቹ አብዛኞቹ ፅንፈኛ ኦርቶዶክስና ኦርቶዶክሶች ናቸዉ።ኒሲም ሠፈራ መንደሩ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ1990ዎቹ እንደተገነባ ባካባቢዉ ከሠፈሩት አይሁዶች አንዱ ናቸዉ።
«ይሕ እየሩሳሌም ነዉ።በሌሎቹ ክፍሎች ለምን ችግር አይኖርም? ሊያፈርሱት ሥለሚፈልጉት ሥለሌላዉ አካባቢ ሊናገሩ ይገባቸዋል።አዳዲስ መንደር አለ።ለምንድነዉ ሥለ ራማት ሽሎሞ ብቻ የሚናገሩት? እኛ እንደሌላዉ አካባቢ ሁሉ ለማዕከላዊ እየሩሳሌም ቅርብ ነን።ሥለዚሕ መንደር ይሕን ያሕል መነገሩ አይገባኝም።»

ኡሪ ሃያ ዘጠኝ አመቱ ነዉ።ከባለቤቱና ከሰወስት አመት ወንድ ልጁ ጋር አዉቶቡስ ይጠብቃሉ። ኡሪና ቤተሰቡ ከአርጀቲና ወደ እስራኤል ከፈለሱ ገና አመት ከመንፈቃቸዉ ነዉ።ራማት ሽሎሞን ቋሚ መኖሪያ አገኘሁ-ይላል ኡሪ።

«ያለ ሥጦታ ከእዉነተኛ ሠላም ይደረሳል።ሕሊናም ስሜትም የሚቀበለዉ መሬት ለሠላም ብሎ አባበል የለም።ሐብት-ንብሬተን የምሰጥ ከሆነ ሠላም አይደለም፥ ሌለኛዉ ወገን የኔን ሠላም አይፈልግም።እኔኑ እራሴን መብላት ነዉ-የሚፈልገዉ።እንደሚመስለኝ የአዲሱ የአሜሪካ ሥርዓት ችግር ይሕ ነዉ።እዚሕ ሥለሚከናወነዉ አይገባቸዉም።»
ግንባታዉ።ራማት ሽሎሞን አጠገብ ከሚገኘዉ ከፍልስጤሞቹ መንደር ሹፋት አንድ ቤት ይሰራል። የቢላል አቡ አልካም ጎረቤት ናቸዉ-ቤት ሰሪዉ።

«እሱ (ጎረቤቴ) ቤት ለመስራት እንዲፈቀድለት ካመለከተ አስር-አመት አልፎታል።ከአስር አመት በሕዋላ አሁን ተፈቀደለት።አምስት ልጆች አሉት።ልጆቹ ማግባት ይፈልጉ ነበር።ግን በመኖሪያ ቤት ችግር ምክንያት አንዳቸዉም ማግባት አልቻሉም።ፍቃዱን ለማግኘት አስር አመት ሙሉ ተሟግቷል።ብዙ ገንዘብ ከፍሏልም።»
የፍልስጤሞችን መብት ለማስከበር የሚታገለዉ የሲቢል ማሕበር እንደሚለዉ የግንባታ ፍቃድ እንዲሰጣቸዉ ካመለከቱ የእየሩሳሌም ነዋሪ ፍልስጤሞች መካከል የከተማይቱ አስተዳደር ፍቃድ የሰጣቸዉ ለአምስት ከመቶዉ ብቻ ነዉ።ከነዋሪዎቹ አንዱ አብዱላሕ እንደሚሉት ፍልስጤሞች የፕሬዝዳት ኦባማ መስተዳድር መፍትሔ መማጣቱን ይጠራጠራሉ።

«ሥለዚሕ የሠፈራ መንደር ኦባማ የሚሉት ነገር ካለ እንጠብቃለን።ሠፈራ መንደሩ ሕገ-ወጥ ነዉ።አይደለም?ይሕ ሠፈራ መንደር ሕገ-ወጥ ነዉ።አሜሪካኖች ራሳቸዉ ይሕን (ሕገ-ወጡን ምግባር) ለማስቆም የወሰዱት እርምጃ አለ? ምንም አላደረጉም።ሕገ-ወጥ ከሆነ እነሱ (እስራኤሎች) እንዲገነቡ ለምን ፈቀዱ።ልክነኝ አይደለም?ይሕ የሠፈራ መንደር ሕገ-ወጥ ነዉ።ከ1967 በሕዋላ-ነዉ። አይደል።ያስቆማቸዉ ሰዉ አለ።አንድ ጊዜ እንኳን ተዉ ያላቸዉ አንድ ሰዉ አለ።የለም።»

ሹፋት እንደ ሁሉም የአካባቢዉ መንደሮችና ከተሞች ሁሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ1967 በተደረገዉ የአረብ-እስራኤሎች ጦርነት እስራኤል በሐይል እስከያዘችዉ ድረስ በዮርዳኖስ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ነበር።

ክሌመንስ ፈረንኮተ

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ