1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እስረኞች ተፈቱ፤ በዓል አክባሪዎች ተገደሉ፤ ቆሰሉም።ኢትዮጵያ

ሰኞ፣ ጥር 14 2010

ዘንድሮ ጥር-መስከረምን፤ የጥምቀት ማግሥት በዓል ኢሬቻን፤ ወልዲያ ቢሾፍቱን ሆኑ እንበል ይሆን? ሆኑም አልሆኑ የደስታ-ምስጋና፤ የጭፈራ ሆታዉ ክቡር በዓል በደም በሰዉ ደም ረከሰ። ዘማሪ፤ ጨፋሪ፤ ሆባዮች ተገደሉ። ቆሰሉ። ቅዳሜ።

https://p.dw.com/p/2rKTU
Äthiopien Protesten der Oromo in Bishoftu
ምስል REUTERS/File Photo/T. Negeri

የኢትዮጵያ መንግሥት እስረኞችን መልቀቁ፣ በሀገሪቱ የቀጠለው ተቃውሞ እና ግጭት

የኢትዮጵያ መንግሥት ይቅር ለፖለቲካ ብሎ በመቶ የሚቆጠሩ እስረኞች በፈታ ማግስት በኦሮሚያም፤ በአማራም መስተዳድሮች ይደረጉ የነበሩ ሕዝባዊ ተቃዉሞዎች፤ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እና ጥፋቶች ቀጠሉ። መንግሥት እስረኞቹን ይቅር ብሎ የፈታ እና ሌሎችን ለመፍታት የወሰነዉ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋት በሚል ነዉ። ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንዳስታወቁት ግን ባለፈዉ ሳምንት የተፈቱት ይፈታሉ ተብለዉ ከሚጠበቁት ፖለቲከኞች በጣም ጥቂቱ ናቸዉ። እስረኞቹ ከተፈቱበት ዕለት እስከትናንት ድረስ ከጪሮ እስከ ወልዲያ፤ ወትሮም የነበረዉ ተቃዉሞ አልተቋረጠም። የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎችም ወልዲያ ዉስጥ ተቃዋሚዎችን መግደል-ማቁሰላቸዉ ተዘግቧል። ለምን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

መስከረም 2009። በዓሉ ኢሬቻ፤ ሥፍራዉ ቢሾፍቱ ወም ደብረ-ዘይት ነበር።በወትሮዉ የመምስጋና ዜማዉ ምትክ -ተኩስ ተንደቀደቀበት፤በደስታ፤ ሳቅ ፤ ፌስታዉ  ፋንታ ዋይታ ተረገደበት። አስከሬን ተለቀመበት።ሐዘን አረበበት።ዘንድሮ ጥር-መስከረምን፤ የጥምቀት ማግሥት በዓል ኢሬቻን፤ ወልዲያ ቢሾፍቱን ሆኑ እንበል ይሆን? ሆኑም አልሆኑ የደስታ-ምስጋና፤ የጭፈራ ሆታዉ ክቡር በዓል በደም በሰዉ ደም ረከሰ።ዘማሪ፤ ጨፋሪ፤ሆባዮች ተገደሉ። ቆሰሉ። ቅዳሜ ይላሉ የወልዲያዉ ነዋሪ።ለሌላዉ የከተማዋ ነዋሪ እንደሚሉት ዕሁድም አላባራም።

Äthiopien Tote bei Anti-Regierungs-Protesten in Bishoftu
ምስል DW/Y. Gegziabher

የአማራ መስተዳድር ፖሊስ እንዳስታወቀዉ በወልዲያዉ ግጭት በትንሽ ግምት ሰባት ሰዉ ተገድሏል። አስራ-ሰባት ቆስለዋል። ከሟቾቹ አንዱ፤ ከቁስለኞቹ ሁለቱ ፖሊሶች ናቸዉ።ሌላ ግጭት፤ ተጨማሪ ግድያ፤ ሌላ መርዶ ሌላ ዋይታ። ወልዲያ በግጭት- ግድያ፤ በቃጠሎ ጢስ ጠለስ የታበጠችዉ ከቢሾፍቱ እስከ ጨለንቆ፤ ከአምቦ እስከ ጪናቅሰን የሚገኙ ከተሞች የደም አበላቸዉን አጥበዉ፤ ማቅ ከላቸዉን ሳያወልቁ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈዉ ሳምት እስረኞችን የፈታ እና ሌሎችን ለመፍታት ቃል የገባዉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአወዳይ እስከ ጎንደር፤ ከባሌ እስከ በደሌ፤ ከኮንሶ እስከ ባሕዳር ዳር በነበሩ ተቃዉሞ፤ ግጭት፤ ግድያ እና የንብረት ዉድመትን ያስከተለዉን ቅሬታ ለማቃለል፤ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እንደሆነ አስታዉቆ ነበር።ወልዲያ ሌላ የግጭት-ግድያ ማዕከል ሆነች።ለምን?

የተቃዋሚዉ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ፤ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ በትክክል ስላለመለሰ የሚል መልስ አላቸዉ። የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉጌታ አበበ በበኩላቸዉ መንግስት የወሰደዉ እርምጃ መዉሰድ ከሚገባዉ በጣም ጥቂቱን መሆኑ ነዉ ባይ ናቸዉ። በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር እና የስትራቴጂ ጥናት ዳሬክተር አቶ መረሳ ፀሐይ ከሁለቱ ፖለቲከኞች ለየት ያለ መልስ አላቸዉ። አቶ መረሳ እንደሚሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጠረዉ መቋሰል እሲከወገድ ጊዜ መፍጀቱ አይቀርም።

የኢትዮጵያ መንግስት ክሳቸዉን ተቋርጦ በምሕረት እንዲፈቱ ከወሰላቸዉ 528 እስረኞች መካከል ከፌደራል እስር ቤቶች 115 ከደቡብ ኢትዮጵያ ደግሞ 361 እስረኞች ባለፈዉ ረቡዕ መፈታታቸዉ ተዘግቧል።ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እስረኞቹ ከመፈታታቸዉ በፊት ባስታወቁት መሠረት የተፈቱት አብዛኞቹ የፖለቲካ እስረኞች መሆን አለባቸዉ።

የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት በተለያዩ እስር ቤቶች በመቶ የሚቆጠሩ መሪዎቹ፤ አባላቱና ደጋፊዎቹ እንደታሰሩበት በተለያዩ ጊዚያት አስታዉቋል።የድርጅቱ  ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ዛሬ እንዳሉት ከታሰሩት የድርጅቱ አባላት ዉስጥ እስካሁን የተለቀቀዉ አንድ ብቻ ነዉ። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እንደሚሉት ደግሞ መንግስት በምሕረት ከለቀቃቸዉ እስረኞች መሐል አንድም የሰማያዊ ፓርቲ አባል እና መሪ የለም።

PK von Äthiopiens Generalstaatsanwalt
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ከእስር ተለቀቁ ከተባሉ 476 ፖለቲከኞች ዉስጥ በመቶ ከሚቆጠሩ የሁለቱ ፓርቲ እስረኛ አባላት ወይም መሪዎች መካከል የተለቀቀዉ አንድ ብቻ ከሆነ፤ በርግጥ የተባለዉን ያክል ቁጥር ያላቸዉ እስረኞች ተለቅቀዋል? ፖለቲከኞችስ ናቸዉ? ያዉ ጥያቄ ነዉ።ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት የለቀቀዉን ያክል እስረኞች የለቀቀና ለመልቀቅ ቃል የገባዉ ብሔራዊ መግባባት እና የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋት እንደሆነ በተደጋጋሚ አስታዉቋል።

ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ፤ የኢሕአዲግ ሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ ዉሳኔንና የመንግሥትን  እርምጃ ቀቢፀ-ተስፋን በበጎ ተስፋ የሚለዉጥ ይሉታል። ጥሩ ጅምር። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ ግን በፖለቲካ ተንታኙ አስተያየት አይስማሙም።መንግስት እስረኞች ለመፍታት የገባዉን ቃል መጀመሪያ በትክክል ተግባራዊ ማድረግ አለበት። አከታትሎ ሌሎች ርምጃዎችን መዉስደ ይገባዋል። ለዉጥ ተፈጥሯዊ ነዉና።

የመኢአድ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ደግሞ እስረኞች በትክክል ከተፈቱ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እና የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋት አንዱ ግን ትንሹ እና የመጀመሪያዉ ርምጃ ነዉ ባይ ናቸዉ።መንግሥት የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚለዉን ሁሉ የሚያሳትፍ ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመፍጠር ቆራጥ መሆን አለበት።አለበለዚያ  በአቶ ሙሉጌታ አገላለፅ «አንዱን ጥሎ ሌላዉን አንጠልጥሎ» የሚሆን የለም።

ሕዳር 2008 በኦሮሚያ መስተዳድር የተጀመረዉ ተቃዉሞ መላዉ ኦሮሚያን፤ አብዛኛዉን የአማራ መስተዳድር እና ከፊል ደቡብ መስተዳድርን አዳርሷል።በተቃዉሞ ሰልፈኛዉ እና በፀጥታ አስከባሪዎች፤ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ አዋሳኝ ድንበሮች መካከል በየጊዜዉ በተፈጠረ ግጭት የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደዘገቡት በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ቆስለዋል። በመቶ ሺሕ የሚጠሩ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል። በቢሊዮን የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟል።

Infografik Karte Proteste und Ausschreitungen in Äthiopien 2016

ለሟች ቁስለኛ ተፈናቃዮቹ የተሰጠ ካሳ የለም።መንግስት ለደረሰዉ ጥፋት ተጠያቂ የሚላቸዉን ወገኖች ለፍርድ እንደሚያቀርብ ባለሥልጣናቱ በተደጋጋሚ ቢናገሩም እስካሁን አንድም ሰዉ በይፋ ለፍርድ አልቀረበም።የዚያኑ ያሕል መንግሥት ከካቢኔ ሹም ሽር እስከ እስረኞች መልቀቅ የተለያዩ እርምጃዎችን ቢወስድም ተቃዉሞዉን ለማስቆም የተከረዉ የለም።አቶ መረሳ እንዳሉት ያሰጋ ነበር።ያሳዝናልም። የከእንግዲሁስ? ያስፈራል።

አስፈሪዉን እዉነት ለማስቀረት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ እንደሚሉት ገዢዉ ፓርቲ መዘየድ አለበት። ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ ፀሕይ ግን አስፈሪዉን ሁኔታ ለማስቀረት መጀመሪያ ሠላም ማስከበር፤ ቀጥሎ ድርድር መደረግ አለበት ባይ ናቸዉ።

እንደገና ሠላም ማስከበር።እንደገና ድርድር።የኢትዮያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ በሐገር ዉስጥ ከሚንቀሳቀሱ ተቃቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መደራደር ከጀመረ ዓመት ደፈነ።ድርድሩ ቀጥሏል።ሕዝባዊ ተቃዉሞ፤ ግድያዉም አላባራም።ሕዝብ እና መንግስት፤ መንግስትና ተቃዋሚ ይግባቡ ይሆን? መቼ? ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ