1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤቦላ እና የቁጥጥሩ እርምጃ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 13 2006

እስከከዛሬ ከ1,100 ሰዎች በላይ ሕይወት ያጠፋው እና ምልክቱም ከ2,100 በሚበልጡ ሰዎች ላይ የታየው የኤቦላ በሽታ የብዙዎቹን የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት መንግሥታትን አሳስቦዋል። ኤቦላ ወደየሀገሮቻቸው እንዳይዛመት የሰጉት ሀገራት ያየር ማረፊያዎቻቸውን እና ወደቦቻቸውን በሽታው ከተከሰተባቸው ሀገራት ለሚመጡ መንገደኞች ዘግተዋል።

https://p.dw.com/p/1Cx9J
Ebola Ausbruch Monrovia 17.08.2014
ምስል Reuters

ወደ ውጭ የሚሄዱ መንገደኞችንም ትኩሳት መቆጣጠር ጀምረዋል። እነዚህ ርምጃዎች በርግጥ የኤቦላን ስርጭት ማከላከል መቻላቸው ግን ብዙዎች እያጠያየቁ ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት ከጥቂት ቀናት በፊት የኤቦላ ስርጭት አብዝቶ ያሰጋታል ያላት ኬንያ ከትናንት እኩለ ሌሊት ጀምራ ድንበርዋን ለጊኒ ፣ ለላይቤርያ እና ለሲየራ ልዮን ተጓዦች ድንበርዋን ዘግታለች። የኬንያ አየር መንገድም ከዛሬ ጀምሮ ወደ ላይቤሪያ እና ወደ ሲየራ ልይዮን አይበርም። ኮት ዲቯርም ኤቦላ ከታየባቸው ሀገራት የሚመጡ መርከቦች በባህር ክልሏ እንዳያልፉ ከልክላለች። ናይጀሪያ ደግሞ የሰውነቱ ሙቀት ከ37 ዲግሪ ሴልሲየስ ያልበለጠ መንገደኛን ብቻ ነው በአይሮፕላን እንዲጓዝ የምትፈቅደው። እነዚህ ርምጃዎች ውጤታማ መሆናቸውን በሞቃት ሀገራት ስለሚታዩ በሽታዎች ምርምር የሚያካሂደው የሂርሽ ማዕከል ባልደረባ ዲተር ሆይዚንገር እንደሚጠራጠሩት ገልጸዋል።

Nigeria Flughafen in Abuja Ebola Kontrolle
ምስል picture-alliance/dpa

« በበረራው ጉዞ ላይ ገደብ ማድረጉ የበሽታውን ስርጭት በመከላከሉ ረገድ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት የሚገኙበትን ግራ የመጋባት ሁኔታ የሚያሳይ ነው። እርግጥ፣ ይህ በሽታውን ለመከለከል ሊወሰድ የሚችል አንድ ርምጃ ነው። በአየር ማረፊያዎች የሚደረገው ትኩሳት የመቆጣጠሩ እና የሰውነት ሙቀት የመለካቱ ዘዴ ግን መቶ በመቶ ይሰራል ለማለት አያስደፍርም። »

ምክንያቱም፣ ይላሉ ሆይዚንገር፣ ይህ ዘዴ በኤቦላ ተኀዋሲ የተያዘን እና ጉንፋን የያዘውን ሰው መለያየት አይችልምና። ከቁጥጥሩ በኋላ በኤቦላ ያልተያዙ ግን ትኩሳት ያለባቸው ሰዎች ምን ይደረጋሉ? እነሱም በተከለለ ቦታ እንዲቆዩ ይደረጋል? ግና ብዙ መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች አሉ።

በበርሊን የጉዞ እና የሞቃት ሀገር በሽታዎች ተከታታይ ማዕከል ባልደረባ ቶማስ የሊኔክም በኤቦላ በሽታ እስካሁን አራት ሰዎች የሞቱባት ናይጀሪያ በአየር ማረፊያዎችዋ የጀመረችውን ትኩሳት የመቆጣጠሩን እና የሰውነት ሙቀት የመለካቱ ዘዴ አስተማማኝ ውጤት የማያስገኝ ሆኖ ነው ያገኙት፤ ምክንያቱም፣ ብዙ ሰው ቁጥጥር በማይደረግባቸው አውቶቡሶች ነው የሚጓጓዘው። ምንም እንኳን ኬንያ ውስጥ በሽታው ባይሰራጭም የኮርያ አየር መንገድ ወደ ኬንያ የሚያደርገውን በረራ ከነገ ጀምሮ ለመሰረዝ ወስኖዋል። ይህንን የኮርያ ውሳኔ የሊኔክ የተጋነነ ብለውታል።

Elfenbeinküste Warnung vor Ebola in den Straßen von Abidjan Straßenszene
ምስል Reuters

« የኤቦላን ተኀዋሲ በተመለከተ በወቅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተወሰደ ያለው ርምጃ የተጋነነ ነው። እንደሚታወቀው ኤቦላ የሚተላለፈው ከበሽተኛው ከሚወጣው ፈሳሽ ነገር ጋ በሚደረግ ቀጥተኛ ንኪኪ ብቻ ነው። »

በንኪኪ ከሚተላለለፈው ከኤቦላ ይበልጥ የሳምባ ነቀርሳን የመሳሰሉ በሽታዎች የሚተላለፉበት ሁኔታ ከፍ ያለ ነው፣ ምክንያቱም በሽታውን የሚሸከመው ተኀዋሲ በአየርም ሊተላለፍ ይችላል። በዚያም ሆነ በዚህ፣ አፍሪቃውያት ሀገራት አሁን እየወሰዱት ያለው ርምጃ ታድያ ሕዝባቸውን ስጋት ከመፍጠር አልፎ የሚበጀው ነገር እንደማይኖር የገለጹት ዲተር ሆይዚንገር እንዳስረዱት፣ በወቅቱ የሚያስፈልገው የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ሕዝቡ በየሀገሩ ካሉት የጤና ባለሙያዎች ጋ ተባብሮ እንዲሰራ ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው።

ሂልከ ፊሸር/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ