1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

« ኤም ዲ ሲ» የገጠመው የመከፋፈል ስጋት

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 25 2006

በዚምባብዌ የተቃውሞ ፓርቲ የዴሞክራሲ ለውጥ እንቅስቃሴ፣ «ኤም ዲ ሲ » አመራር አባላት መካከል የተፈጠረው ልዩነት በፓርቲው ህልውና ላይ ስጋት ደቀነ። አጠቃላዩ ምርጫ ተካሂዶ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ከተመረጡ እና «ኤም ዲ ሲ » ከዛኑ ፒ ኤፍ » ጋ የመሰረተው ጥ/መንግሥት ካበቃ ወዲህ « ኤም ዲ ሲ » ትልቅ የመከፋፈል ችግር ገጥሞታል።

https://p.dw.com/p/1Bt3B
ምስል Reuters

በዚምባብዌ ባለፈው ነሀሴ፣ 2013 ዓም አጠቃላዩ ምርጫ ተካሂዶ የ90 ዓመቱ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ እንደገና ከተመረጡ እና በገዢው የ «ዛኑ ፒ ኤፍ» እና በትልቁ የሀገሪቱ ተቃውሞ ፓርቲ የዴሞክራሲ ለውጥ እንቅስቃሴ፣ በምህፃሩ፣ «ኤም ዲ ሲ » መካከል ከዛኑ ፒ ኤፍ » ጋ መስርቶት የነበረው ጥምር መንግሥት ካበቃ ወዲህ « ኤም ዲ ሲ » በሀገሪቱ ትርጉም እያጣ በመሄድ ላይ መሆኑን የፖለቲካ ታዛቢዎች ገልጸዋል። በሞርገን ቻንጊራይ የሚመራው « ኤም ዲ ሲ » ባጠቃላዩ ምርጫ በደረሰበት ሽንፈት ሰበብ በፓርቲው አንጃዎች መካከል በተፈጠረው ንትርክ ፓርቲው ትልቅ እክል ገጥሞታል።

ባለፈው የሳምንት መጨረሻ የፓርቲው ዋና ፀሐፊ ቴንዳይ ቢቲ ሞርገን ቻንጊራይ ከፓርቲው መታገዳቸውን ማስታወቃቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን ተከተሎ ቻንጊራይ ደጋፊዎቻቸውን በማሰባሰብ ባለፈው ማክሰኞ «ኤም ዲ ሲ » ባለፈው ,ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው ዓመፅ ተሳትፈዋል ያላቸውን ስምንት የፓርቲው አመራር አባላትን፣ ቴንዳይ ቢቲን ጭምር ማገዱን በበኩላቸው ገልጸዋል።

Robert Mugabe
ምስል picture-alliance/AP Photo

«ባመፁ የተሳተፉ ሰዎች የግድ ሞርገን ቻንጊራይን ከድተዋል ማለት አይደለም። የከዱት ህዝቡን ነው። ድርጊታቸው ይህን አሳይቶዋል። እነዚህ ወገኖች አሁን የራሳቸውን አዲስ ፓርቲ አቋቁመዋል። መልካም ዕድል እንመኝላቸዋለን። አሁን የ «ኤም ዲ ሲ » አባል ነን ሊሉ አይችሉም። አይደሉምና። »

ካ,ለፉት 15 ዓመታት «ኤምዲ ሲ» ን በመምራት ላይ ያሉት ሞርገን ቻንጊራይ እአአ ከ2008 ዓም በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ካሸነፉ በኋላ፣ ገዢው የ«ዛኑ ፒኤፍ » ፓርቲ በ«ኤምዲሲ» አባላት ላይ ክትትል በማሳረፉ ከ2ኛው ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ መራቃቸው የሚታወስ ነው። የምራጭውን ውጤት ተከትሎ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ውዝግብ ለማብቃት የደቡባዊ አፍሪቃ መንግሥታት የልማት ድርጅት፣ በምሕፃሩ «ሳዴክ» ባካሄደው ሸምጋይነት በሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች መካከል የሥልጣን መጋራት ስምምነት መሠረት። ቻንጊራይ በጠቅላይ ሚንስትርነት የመሩት ጥምር መንግሥት ተመሠረተ። ይሁንና፣ እአአ በ2013 ዓም በተካሄደው ምርጫ ፓርቲያቸው ለተሸነፈበት ድርጊት ቻንጊራይ ተጠያቂ ናቸው በሚል ከራሳቸው ፓርቲ ብርቱ ነቀፌታ ተሰነዘረባቸው፤ ትችታ ካቀረቡት መካከል አንዱ የፓርቲው ቃል አቀባይ ቻርልስ ማንጉንጌራ ኤም ዲ ሲ የመከፋፈል ስጋት እንደተደቀነበት አመልክተዋል።

« ጥያቄው የሰፊው የፓርቲ አባላት ድጋፍ አለኝ ሳይሆን፣ የፓርቲውን መርህ እና እሴት አከብራለሁ የሚለው ነው ወሳኙ ጉዳይ። «ኤም ዲ ሲ» ዴሞክራሲን፣ ኃይል አልባ እንቅስቃሴ እና የተለያዬ አስተሳሰቦች የሚሉ መርሆችን መሠረት አድርጎ ነው የተቋቋመው። »

SADC Gipfel in Südafrika Morgan Tsvangirai und Tendai Biti
ምስል picture-alliance/ dpa

የቻንጊራይ ተቺዎች የፓርቲው መሪ እነዚህን መርሆች አላከበሩም በሚል ነው ተቃውሞ የሚያሰሙት። እርግጥ፣ «ኤምዲሲ»፣ በተለይ ቻንጊራይ ስራቸውን በማከናወኑ ረገድ የገጠማቸውትልቅ እክል እና በስራቸው አመርቂ ውጤት ባስመዘገቡት በሌሎቹ ለምሳሌ የኤኮኖሚ ሚንስትሩ፣ ቴንዳይ ቢቲ ወይም የትምህርት ሚንስትሩ ዴቪድ ኮልትሀርትን በመሳሰሉት የ«ኤምዲሲ» ሚንስትሮች አንፃር ቻንጊራይ ውጤት አለማስገኘታቸው በፓርቲው አንጃዎች መካከል ለተፈጠረው ንትርክ ድርሻ ሳያበረክት እንዳልቀረ የደቡባዊ አፍሪቃ የጥናት ማዕከል ባልደረባ ፒትር ሪፕከን ገልጸዋል። አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ አሁን በ«ኤም ዲ ሲ» ውስጥ ለሚታየው ክፍፍል ተጠያቂው የ90 ዓመቱ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ እና ገዢው «ዛኑ ፒ ኤፍ» ፓርቲያቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ