1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢድ አል-ፈጥር እና የኢትዮጵያዊያኑ ሮሮ

እሑድ፣ ሰኔ 18 2009

ዓለም ኢድ አልፈጥርን ሲያከብር ሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ አየር ማረፊያ ቢሄዱም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በደንበኞች ሰነድ ውል ላይ የተቀመጠውን ደንብ ሳያከብር በመቅረቱ ሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያውያ ዓለም አቀፍ  ትምህርት ቤት ለመቆየት መገደዳቸው ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/2fM2P
Äthiopien  Rückkehr
ምስል DW/S. Shibiru

MMT (Beri Riyadh) Ethiopian returnees stranded in Riyadh on Eid - MP3-Stereo

1438ኛው የኢድ ዓልፈጥር በዓል በመላው ዓለም ተከ፡፡ የሁለቱ ቅዱሳን መስጊዶች መገኛ እና የእስልምና እምነት ማዕከል በሆነችው በሳዑዲ ዓረቢያ በዓሉ ከታወጀበት ከትላንት ምሽት ጀምሮ ፌሽቲያና ደስታው እንደቀጠለ ነው፡፡ ዛሬ ማለዳ ሙስሊም ምእመናን በጋራ ጸሎት ለፈጣሪ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከረመዳን የበዓል ድባብ በተቃራኒው የሳዑዲ መንግሥት የሰጠው  የ«ውጡልኝ» ቀነገደብ ሳይጠናቀቅ  ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ትኬት ቆርጠው ሕጋዊ የጉዞ ሰነዳቸውን አሟልተው ከሁለት ቀን በፊት ሳዑዲ አየር ማረፊያ የተገኙ ከ400 በላይ ኢትዮጵያዊያን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ መሄድ አልቻሉም፡፡

ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቃሉ መሰረት መጓጓዣ አውሮፕላን አለማቅረቡ ነው። ኢትዮጵያዊያኑ ተመላሾች በሪያድ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት መማሪያ ክፍሎች ውስጥ በተጨናነቀ መልኩ ውሎ እና አዳራቸውን አድርገዋል። 

ሪያድ ከትናንት ምሽት ጀምሮ በበዓል ድባብ ውስጥ ናት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ 1438ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ነው። የአንድ ወር ጾም ጸሎት ማብቂያ ፤ ጾሙ በሰላም በመጠናቀቁም ለፈጣሪ ምስጋና ማቅረቢያ ነው የዛሬው በዓል፡፡ 

በማለዳም በርካታ ኢትዮጵያዊያን በሚገኙበት የሪያዱ የመንፉአ ግዛት የማለዳ ጸሎት ስርዓት ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችም ወንዶችም ከነልጆቻቸው በማለዳው የምስጋና የጋራ ጸሎት ላይ ተገኝተዋል፡፡

Äthiopien  Rückkehr
ምስል DW/S. Shibiru

ከመንፉአ ምዕራባዊ አቅጣጫ ሙረባ በተባለው የሪያድ አንድ ክፍል የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ እና የመማሪያ ክፍሎች ግን የኢድ በዓል ሳይሆን የምሬት የእንግልት እና የድብርት ድባብ ሰፍኖባቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዓልን ሀገር ቤት ከቤተሰብ ጋር ለመዋል አቅደው የሳዑዲ የምህረት አዋጅ ቀነ ገደብ ሳይጠናቀቅ ሀገር ቤት ሊገቡ የጉዞ ሰነድ አሟልተው ትኬት ቆርጠው ሳዑዲ አይሮፕላን ማረፊያ ቢገኙም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በደንበኞች ሰነድ ውል ላይ የተቀመጠውን ውል እና ደንብ ሳያከብር መቅረቱ ነው፡፡

ከነዚህም በተጨማሪ አብሀ ከተባለው የሳዑዲ ዓረቢያ ደቡባዊ ግዛት ከርዕሰ መዲናው ሪያድ 1 ሺህ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው ፡፡ ከሪያድ አዲስ አበባ በትራንዚት ወይንም በሽግግር ጉዞ ትኬት ቆርጠው የመጡ ከ60 በላይ ሴትችም ወንዶችም ኢትዮጵያዊያን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እጣ ፈንታቸው  የሪያዱ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ቅጥር ነው፡፡ የስታር ኤየርላይንስ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሪያድ ቢሮ ኃላፊን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ያደረኩት ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያም ሆነ የየትኛውም ስመ ጥር አየር መንገድ ቃሉን ሳያከብር ሲቀር ለደንበኞች የሚያደርገው የቃልም ሆነ የተግባር መስተንግዶ አንዱም ቢሆን በኢትዮጵያዊያን ደንበኞች ዘንድ አልተከበረም፡፡

Äthiopien  Rückkehr
ምስል DW/S. Shibiru

በርካታ ሻንጣዎቻቸውም ሆነ እነርሱ ለቀናት እና ለሰዓታት በሳዑዲ አየር ማረፊያ ክብረ ነክ በሆነ ሁኔታ መስተንግዶ ከመነፈጋቸውም በላይ ምሽቱን እንዲያሳልፉ የተደረገውም በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ እና የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ነው፡፡

የሳዑዲ መንግስት የሰጠው የዘጠና ቀናት የውጡልኝ የምህረት ጊዜ ተጠናቋል፡፡ የመጣው ይምጣ ብለው መውጣት የማይፈልጉት ዜጎች እንዳሉ ሆነው መውጣት ፈልገው የመውጫ ሰነድም ሆነ የአይሮፕላን ቲኬት በእጃቸው የያዙትም እንኳን አብዛኞቹ አስፈላጊውን አገልግሎት እያገኙ አይደለም፡፡ ሁሉም እንደሚሉት በማንኛውም ደቂቃ የሳዑዲ መንግስት ህገወጥ ያላቸውን በአፈሳም ሆነ በማንኛውም መንገድ በቁጥጥር ስር ማዋል ይጀምራል የሚል ስጋት ሰፍኗል፡፡ ምናልባትም ለአብዛኞቹ መኖሪያ ፍቃድ አልባ ኢትዮጵያዊያን የሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ጽህፈት ቤት የአይናቸው ተስፋ ሆኗል፡፡

የሳዑዲ መንግስት በሰጠው የዘጠና ቀናት የምህረት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ለማስወጣት ከማሳመን ጀምሮ ሀገር እስከ ማድረስ ድረስ ባለፉት ዘጠና ቀናት ምን ያህል አቅዶ ምን ያህሉን ፈጽሞ ይሆን ሰሞኑን እንቃኘዋለን፡፡

ስለሺ ሽብሩ
ማንተጋፍቶት ስለሺ