1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮ-ጣልያናዊትዋ ከያኒ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 21 2008

« አማርኛዬ ዉኃ እንደሚያፈስ የተቀደደ ጀርኪና አይነት ነዉ። ወደ ጣልያን ስመጣ 14 ዓመቴ ነበር። እዚህ እንደመጣሁ የሃገሬን ናፍቆት አልቻልኩትም ነበር። ሃገሬን የማያት ከወለደችኝ እናቴ በላይ አርጌ ነዉ።»

https://p.dw.com/p/1JXLt
Gabriella Ghermandi Schrifstellerin CD Cover
ምስል Gabriella Ghermandi

ኢትዮ-ጣልያናዊትዋ ከያኒ



ትዉልደ ኢትዮጵያዊ ጣልያናዊትዋ ጋብርኤላ ጋርማንዲ ትባላለች። ጋብርኤላ የአራዳ ልጅ ለዛዉም የመሃል ፒያሳ መሆንዋን ስትናገር በኩራት ነዉ። ጤና ይስጥልኝ አድማጮች እንደምን ሰነበታችሁ ከጣልያናዊ አባትዋና ከኢትዮጵያዊት እናትዋ ጋር ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል በታች ላይ በነበረዉ መኖርያ ቤታቸዉ ማደጓን የምትገልፀዉ ጋብርኤላ እስከ 14 ዓመትዋ ረስ ኢትዮጵያ ኖራ አባትዋ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ወደ አባትዋ ሃገር ወደ ጣልያን መምጣትዋን ትናገራለች።
« እምዬ ኢትዮጵያ አንቺ የቅድስት ሃገር የማዉቀዉን ያህል ስላንቺ ልናገር። ባይታወርነቱ ብቻዬን ሲጫነኝ ኢትዮጵያዊነት ነዉ መጽናኛ የሆነኝ። »
ጋብሪላ ጋርማንዲ የወራሪ ጣልዓን ፋሽስትን ግፍ በተመለከተ ባሳተመችዉ መጽሐፍዋ ነዉ በመጀመርያ በጣልያን ብሎም በሌሎች የምዕራባዉያን ሃገራት እዉቅናን ያገኘችዉ፤ ከዝያም ይህ የድርሰት ስራዋ ወደ ኪነ-ጥበቡ እንድትገባ መንገድ እንደጠረገላት ትናገራለች። አባትዋ ጣልያን ሃገር ከመኖር ኢትዮጵያ በነጻነት መኖርን ይወዱ ስለነበር ከቤተሰቦችዋ ጋር ወደ ጣልያን ሳትሄድ መቆየትዋን ከዝያ ግን 13 ዓመት ሲሞላት አባትዋ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸዉ በ14 ዓመትዋ በእናትዋ ፈቃድ ወደ ጣልያን መምጣትዋን ጋብርኤላ አጫዉታናለች። ጋብርኤላ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቃለ ምልልስን የጀመረችዉ ስምዋን በማስተዋወቅ ነበር። « ስሜ ጋብርኤላ ጋርማንዲ ይባላል። » ሙዚቀኛ ነሽ?
«በእዉነቱ ለመናገር እኔ ራሴ ራሴን ማን ብዬ እንደምጠራ አላዉቅም። እንደዉ ዝምብዬ የሃገሬ ወዳጅ ነኝ ብል ይሻለኛል። እንደዉ በመጀመርያ ነገር የአገሬ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነኝ ብል ይሻለኛል። ከኢትዮጵያ ፍቅር የተነሳ በመጀመርያ በደራሲ መስመር አርት ዉስጥ ገባሁኝ ከዝያ ወደ ፐርፎርማንስ ገባሁ፤ ከዝያም ነዉ ሙዚቃን የጨመርኩት »
« እምዬ እምዬ፤ የአክሱም ላሊበላ የፋሲል ግንቦችዋ የሃረር የጀጎል ድንቅ ጥበቦችዋ፤ የሶፍመር ዋሻ ልዩ ሃይቆችዋ፤ ባላትዋ ያኮራል ብሄረሰቦችዋ። በ13 ወር ፀጋ ፈጣሪ ያደላት ፤ ተከባብሮ የሚኖር ኩሩ ህዝብ ያለባት ፤ የራስዋ የሆነ ፊደል ቀመር ያላት፤ ኢትዮጵያ ሃገሬ ታሪካዊ እኮ ናት። »
ምንድን ነበር መጽሐፍ ነበር የምትጽፊዉ ነበር ማለት ነዉ?
« አዎ ፤ በእዉነት ላይ ያተኮረ የልብ ወለድ መጽሐፍ ነዉ ያሳተምኩት። በጣልያንኛም በእንግሊዘኛም ታትሞአል። መጽሐፉ ስለኢትዮጵያ አርበኞች በኢትዮጵያዊዉያን አስተሳሰብ አይነትን የሚያንፀባርቅ ነዉ። « Queen of Flowers and Pearls» ይሰኛል የመጽሐፉ አርዕስት።»
ጋብሪላ ጋርማንዲ የእናትዋን ጠጉር በመያዝዋ የተለያዩ ሹሩባን ተሰርታ የኢትዮጵያ ሰንቀላማ ያለዉን ልብስ አልያም ባህላዊ መስቀል ያለዉን ቲሸርት አድርጋ ነዉ ብዙ ጊዜ ከካሜራ ፊት የምትቀርበዉ ። ከእድሜዋ አብላጫዉን ጊዜ በጣልያን በማሳለፍዋ አማርኛ ቋንቋ ትንሽ ቢስቸግራትም ኢትዮጵያዊ ባህልዋን አጥብቃ እንደያዘች ትናገራለች። እስቲ ታሪክሽን ከመጀመርያ ጀምረሽ አጫዉችን አልናት ፤ አይ አማርኛዬ አለች በመቀጠል።
«አማርኛዬ ዉኃ እንደሚያፈስ የተቀደደ ጀርኪን አይነት ነዉ። ወደ ጣልያን ስመጣ 14 ዓመቴ ነበር። እዚህ እንደመጣሁም ሃገሬ በጣም ናፍቆኝ ነበር። ሃገሬን የማያት ከወለደችኝ እናቴ በላይ ነበር የማያት። ለ 17 ዓመት በናፍቆት ተጠልዬ ነዉ የኖርኩት። ከዝያ ከ17 ዓመት በኋላ የሆነ ሥራ ሰርቼ ብር አጠራቅሜ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሄድኩኝ። » ይህ በስንት ዓመተ ምህረት በሆኑ ነዉ?
« በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1995 ዓ,ም ነዉ እዝያ እንደሄድኩ እና ያደኩበትን ቤት እንዳየሁ ዉስጤ የነበረዉ ናፍቆት ሁሉ ወጣና በጣም አለቀስኩ፤ ከዝያም በጣም ታመምኩ ትኩሳቴ ሁሉ በጣም ከፍ ብሎ በጠና ታምሜ ነበር። በርግጥ በፊት ለዘላለም ሃገሬን ሳላይ የምኖር መስሎ ነበር የሚታየኝ። ከዝያም ከዚህ ጊዜ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በጣም መመላለስ ጀመርኩኝ። ከዚትዮጵያ ስወጣ በልጅነቴ ስለነበር፤ ስለኢትዮጵያ ብዙ ነገር ስላማላቅ በምመመላለስበት ጊዜ ስለኢትዮጵያ ይበልጥ ለማቀቅ ጥረት ማድረጌን ቀጠልኩ ። እኔን ወደ ኪነ-ጥበቡ እንደገባ ያደረገኝና የገፋኝ፤ የሃገሪ ፍቅር ነዉ። በዝያ ላይ ብዙ ዉጣ ዉረዶችን አሳልፍያለሁ። አባቴ ሕጻን ሆኜ ነዉ የሞተዉ፤ አባቴ ከሞተ በኋላ አባቴ ያፈራዉን ንብረት ሁሉ ደርግ ወርሶት ፤ እኔ እና እቴ የምንኖርበት ገንዘብ አጥተን ከሰፈር ከሚሰበሰብ የእድር ገንዘብ እየተሰጠን ነዉ ለአንድ ዓመት ያህል የኖርነዉ። ከዝያም ወደ ጣልያን ሃገር ስመጣ ለብቻዬ ነዉ የመጣሁት ምክንያቱም እናቴን ደርግ አለቅም አላት። እዚህ ጣልያን በልጅነቱ ብቻዬን ተቀመጬ ማንም ሳይረዳኝ ብቻ ብዙ ችግሮችን አሳልፍያለሁ። እና ይህን ሁሉ ሃዘን እንድቋቋም ያስችለኝ የነበረዉ፤ የሃገሬ ትዝታና ፍቅር ነዉ።» ኢትዮጵያ የት ነበር የኖርሽዉ?
« የኖርነዉ አዲስ አበባ ኤርኒኮ ኬክ ቤት በታች ጋር ካለዉ ቁልቁለት መንገድ ላይ ባለዉ አካባቢ ላይ ነበር የኖርነዉ፤ ተወልጄ ያደኩትም እዝያዉ ነዉ። አባትሽ ኤርኒኮ ኬክ ቤት ይጋግሩ ነበር ምን ይሰሩ ነበር።?
« አባቴ የመንገድና የመኖርያ ቤት ኮንስትራክሽ ዉስጥ ነበር የሚሰራዉ። ለምሳሌ የጉመር የሻይቅጠል ፋብሪካን እሱ ነዉ የገነባዉ። »
ጋብርኤላ በአማርኛ ቋንቋ ማንበብን ትችላለች መጻፍ ግን እንደሚቸግራት አጫዉታናለች ፤ ጣልያንኛ ቋንቋም ቢሆን ከጣልያኖቹ ትበልጣለች እንጂ እንደማታንስ ለአንባቢ ባቀበችዉ መጽሐፍዋ አስመስክራለች። ታድያ ይህ ታሪክ ነክ ልቦለድ መጽሐፍዋ ዉስጥ ጣልያንን ሰላቶ በማለትዋ ምን አስተያየት እንደተሰጣት እንዲህ ነግራናለች።
« እኔ ብፈልግ ሙሉ በሙሉ ጣልያናዉዊ መምሰል እችላለሁ ደግሞም ነኝ። ይህን ስል የጣልያንን ባህል ጠንቅቄ አዉቃለሁ፤ አማርና ቢያስቸግረኝም ፤ ጣልያንኛ ቋንቋን ግን በደንብ እናገራለሁ ከማንኛዉም ጣልያን ጋር መወዳደር እችላለሁ። የኔ መጽሐፍ ራሱ ብዙ ሽልማትን አገኝቶአል። አንድ ጊዜ መጽሐፊን ሽልማት ሊሰጡት የመረጡት ኮሚቴዎች ፤ ሽልማቱን በእጄ ሲሰጡኝ አንዱ የኮሚቴ አባል ፣ «አንቺ በመጽሐፍሽ ጣልያን ሰላቶ ብለሽ እንዴት ሰደብሽን፤ ጣልያንና ቋንቋሽን ግን አልቻልነዉም፤ ስለዚህ ነዉ ይህን ሽልማት የምንሰጥሽ። እንዲህ የሚጽፍ ሰዉ በቀላሉ አይገኝም። ስለዚህ ብፈልግ ሙሉ በሙሉ ጣልያን መሆን እችላለሁ፤ ማለት ለዚህ የሚያንሰኝ ምንም ነገር የለም ለማለት ፈልጌ ነዉ። ልቤ ግን ያለዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ። ከአገሬ ከኢትዮጵያ መለያየት አልችልም። »
የኢትዮጵያን ባህልስ እንዴት ታደርጊያለሽ ። የምትኖሪዉ ጣልያን ነዉ፤ በርበሪዉ ስሮዉ እንጀራዉ?
«ሳቅ,,,የኔ ቤት መቼም የጤፍ እንጀራ አይጠፋም። ለምሳሌ በዓመት ከቤተሰቤ ጋር ሁለቱ ሶስቴ ወደ ኢትዮጵያ እሄዳለሁ። ከኢትዮጵያ ስመለስ አንድ ሻንጣ ለበርበሬ ፤ ለእርጥብ እንጀራ፤ ለቅቤ ፤ በአጠቃላይ ቤቴ ዉስጥ የጎደለኝ የኢትዮጵያ ምግብን ሁሉ እይዛለሁ። እቤቴ የሚመጣ ሰዉ ራሱ በጣም ይስቃል። አንድ የኢትዮጵያ እንደም ነገር እንዲጎድለኝ አልፈልግም። በእዉነት ለመናገር ግን ቡና ማፍላት አልችልም፤ አልዋሽም።
«ተዉ በለዉ ተዉ በለዉ፤ ተዉ በለዉ ተዉ በለዉ፤ የጀግኖቹን ድንበር ወሰኑን አሳየዉ በደም በአጥንታችን ተከልሎአል በለዉ ፤ እንቢ ካለህ በለዉ፤ እንቢ ካለህ በለዉ፤ በለዉ፤ በለዉ፤ በለዉ፤ ያንን ሁሉ መሳርያ ሲጭን ሲያጋብስ ፤ የመርዝ ጋዝ ሳይቀር ቦንብ መትረየስ፤ የኢትዮጵያ ጀግና አልሞ ተኳሹ የሚስተነፍስ፤ አጨደዉ ከመረዉ ቆላዉ እንደገብስ፤ በለዉ፤ በለዉ፤ በለዉ »
ጋብርኤላ « ዝክር አጼ ቴዎድሮስ የተሰኘና ዘጠኝ ሙዚቃን ያካተ የሙዚቃ አልበምዋ የዓለም አቀፉን ሙዚቃ ሽልማት ለመወዳደር ቀርበዋል። ጋብርኤላን ጨምሮ ሦስት ጣልያን አራት አበሻና አንድ ተወዛዋዥ ያካተተዉ የሙዚቃ ቡድን ባለፈዉ ዓመት በጣልያን በርካታ የሙዚቃ ድግስንም አሳይቶአል፤ ሙዚቃዉም ተወዶላታል።
« ስራዉን ያቀረብነዉ ለአጼ ቴዮድሮስ ነዉ፤ ማለት ለአጼ ቴዮድሮስ ክብር፤ ዝክር። ለአጼ ቴዮድሮስ ለኔ ለሃገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም እንደ ምሳሌ የሚቀርቡ ምልክት ናቸዉ። ምክንያቱም ከዘር ሃገር ወጥተዉ የሕዝብ ሰዉ ሆነዉ፤ በፍላጎቱ በኃይሉ ግን ፤ በረቂቅ መንገድ የነገሰ ሰዉ ነዉ። እናም ብዙ ነገርን አሳይተዉናል። ሌላዉ የዉች ወራሪ ማለት እንግሊዞቹ ኢትዮጵያን ለመግዛት ሙከራ ሲያደርጉ የሃገራችንን ነጻነት የጠበቁ የመጀመርያ ንጉሳችን ናቸዉ። በሌላ በኩል በሃገራችን አሁን አሁን የሚታየዉ ሙዚቃ ወደድኩኝ አበድኩኝ የሚል ስለፍቅር ብቻ በመሆኑ ፤ የድሮ አይነቱ ፉከራና ሽለላ በመቅረቱ ነዉ። ለዚህ ነዉ ይህን ለማዜም የፈለኩት።
« ኸረ ጎራዉ፤ ኸረ ጎራዉ ያመይሳዉ ካሳ ጀግናዉ አባ ታጠቅ፤ ያ መይሳዉ ካሳ ጀግናዉ አባታጠቅ ፤ ያዉቅበት ነበረ ሱሪዉን ማስታጠቅ ኸረ ጎራዉ ጎራዉ ጎራዉ ፤
ይህን ስራ ስጀምር ሩቅ ደርሳለሁ ብዬ አልነበረም። በሃገራችን የየካቲት አስራ ሁለት 75 ኛ ዓመት ክብረ በዓል ዝግጅት ሲደረግ ነዉ። በኢትዮጵያ የሚገኙት ጥንታዊ አርበኞችና የዩንቨርስቲ ምሁራን በዝግጅቱ ላይ የሆነ ነገር እንዳቀርብ ጋበዙኝ። እኔ የምችለዉን ሁለት ፉከራ አቀርብኩ፤ ከዝያ ነዉ አንድ ስራ ካልሰራሽ ብለዉ ለዚህ ያበቁኝ። »
ጋብርኤላ ጋርማንዲ ዝክር ለአጼ ቴዮድሮስ የሚለዉ ሚዚቃዋ በዓለም የሙዚቃ ሽልማትን እንዲያሸንፍ ሙዚቃዋን በመግዛት ትብብር እንዲደረግላት ጠይቃለች፤ ከያኒ ጋብሪላ ጋርማንዲን ለሰጠችን ቃለ-ምልልስ በማመስገን ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫዉን ማዕቀፍ በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

Gabriella Ghermandi Schrifstellerin
ምስል Gabriella Ghermandi
Gabriella Ghermandi Schrifstellerin
ምስል Gabriella Ghermandi
Gabriella Ghermandi Schrifstellerin
ምስል Gabriella Ghermandi
Gabriella Ghermandi Schrifstellerin
ምስል Gabriella Ghermandi