1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ የድርቅ እርዳታ እንዳጠራት አሳሰበች

ቅዳሜ፣ ሰኔ 3 2009

ኢትዮጵያ ከሚመጣው ወር አንስቶ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎቿ የሚከፋፈል የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ላይኖራት እንደሚችል አስታወቀች፡፡ የእርዳታ ፈላጊዎች ኢትዮጵያውያን ቁጥር 7.8 ሚሊዮን ደርሷል፡፡

https://p.dw.com/p/2eSd4
Äthiopien Gode - Dürre-Krise
ምስል DW/J. Jeffrey

 
የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለአሶሴትድ ፕሬስ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚሆን አንድ ቢሊዮን ዶላር ትሻለች፡፡ አቶ ምትኩ በከፍተኛ የምግብ እጥረቱ ምክንያት ቀውስ የመከሰቱ አዝማሚያ “በጣም ከፍተኛ” እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ወቅት ጠብቆ ይመጣ የነበረው ዝናብ በመቅረቱ ከብቶች እየሞቱ እንደሆነ አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ባለፈው አራት ወር ብቻ የድርቅ ተጎጂዎች ቁጥር በሁለት ሚሊዮን መጨመሩንም አስታውሷል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በድርቅ የተጠቁ ሶስት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ለመጎብኘት ወደ አካባቢው የተንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ጉዳዮች ልዑካን ቡድን ትላንት በሶማሌ ክልል ዋርዴር ዞን ያሉ ቦታዎችን ጎብኝቷል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ልዑካኑን ለመቀበል ተሰልፈው እንደነበር የገለጸው የአሶሴትድ ፕሬስ ዘጋቢ በአቅራቢያው ክፉኛ የከሱ ግመሎችን እና ፍየሎችን አስተውሏል፡፡ በየቦታው የወዳደቁ የከብት አጽሞችንም ተመልክቷል፡፡ የልዑካን ቡድኑን የመሩት የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ የሰብዓዊ ጉዳዮች መልዕክተኛ አህመድ ኤልማራኪ “ዋና ጉዳያችን ሊሆን የሚገባው በኢትዮጵያ ያለው ድርቅ ወደ ጠኔ እንዳያሽቆለቁል ነው” ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡ 
በአፍሪቃ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የጀርመን የልማት ሚኒስትር ጌርት ሙለር ዛሬ እንዳሳሰቡት የተባበሩት መንግሥታት ለእንደዚህ አይነት የአደጋ ጊዜ የሚሆን 10 ቢሊዮን ዩሮ መጠባበቂያ ሁሌ ሊኖረው ይገባል። በግጭት እና በድርቅ የተነሳ በአሁኑ ወቅት ከ 20 ሚሊዮን በላይ አፍሪቃውያን የምግብ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

Äthiopien Ein unterernährtes Kind wartet mit seiner Mutter im Krankenhaus
ምስል picture-alliance/dpa/S. Morison

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ