1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለለዉጡ ሰዎስት ቢሆኖች ሴናሪዮዎችን ያስቀምጣሉ

ሰኞ፣ የካቲት 19 2010

የካቲት 1929 አዲስ አበባ የግራዚያኒን ጭፍጨፋ አስተናግዳለች።የካቲት 1966 የረጅም ጊዜዉ ጠቅላይ ሚንስትር አክሊሉ ሐብተወልድ ሥልጣን በመልቀቃቸዉ ጨፍራለች።ሕዝባዊ ተቃዉሞ የዘመናት ያገዛዝ ሥርዓታቸዉን ያንገጫገጨባቸዉ አፄ ኃይለ ሥላሴ በአክሊሉ ምትክ እንዳልካቸዉ መኮንን ሲሾሙ አዲስ አበባ «ጉልቻ ቢቀያየር----» እያለች ጮኻለች---

https://p.dw.com/p/2tN3d
Äthiopien Tote bei Anti-Regierungs-Protesten in Bishoftu
ምስል DW/Y. Gegziabher

ኢትዮጵያ የየካቲት አዚም

እርግጥ አዲስ አበቦች በ1929ኙ አለያም በ1966ቱ የካቲት ሁነት ከመቆዘም አልፈዉ፤ በያሬድ ጥበቡ አገላለፅ ፊታቸዉን ፀሐይ «ለማስመታት» የፈቀዱ አይመስሉም።ከኦሮሚያ እስከ አማራ፤ ከስልጤ እስከ ኮንሶ ያለዉ ኢትዮጵያዊ ግን ሲሆንለት ባደባባይ፤ ሳይሆን በር ዘግቶ ለ«ለዉጥ» እንደ ጮኸ ሰወስተኛ የካቲትን አጋመሰ።ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለሕዝብ ጩኸት እና ጥሪ የሰጡት መልስ የአክሊሉ ሐብተወልድን እንጂ የማርሻል Rodolfo Grazianiን አለመሆኑ ለብዙዉ ኢትዮጵያዊ ስስ ግን ጥሩ ተስፋ- ደስታም ነዉ።የ2010ሩ የካቲት እንዳልካቸዉ መኮንን የሚያደርገዉን ፖለቲከኛ ማንነት አብይ፤ ለማ፤ ደመቀ እያለ ሲያማርጥ ሐይለማርያም የሚመሩት መንግሥት የጣለዉ ዳግማዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግን ወትሮም የሳሳዉን ተስፋ-ደስታ እንዳያጨናጉለዉ ማስጋቱ ነዉ ቀቢፀ ተስፋዉ።

                                  

ኢትዮጵያ መንግሥት ደጋግሞ የሚለዉ አለቅጥ የሚኩራራበት፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መገናኛ ዘዴዎች የሚያወድሱለት አንድ ጥሩ ዉጤት አለዉ።ልማት። ወይም የምጣኔ ሐብት እድገት።የምጣኔ ሐብት አዋቂ እና የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮ እንደሚሉት ግን ዕድገቱ  የሚባልለትን ዓይነት አይደለም።

                                   

አሁን ደግሞ እጅግ የተወራለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕዳ መከፍል የሚበቃ አቅም እንኳን አጥቷል።

                          

በሰብአዊዉ  እና በፖለቲካዉ መስክ ደግሞ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች «ድምፃችን ይሰማ» በማለት የጀመሩት የፍትሕ ጥያቄ አጉዞ አጉዞ ወደ ሕዝባዊ አመፅ እና ተቃዉሞ ከተቀየረ ወዲሕ ሺዎች ተገድለዋል፤ ብዙ ሺዎች ቆስለዋል። በገፍ ታፍሰዉ፤ ታስረዉ በግፍ ተፈርዶባቸዉ ተፈተዋል።መቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል።

ሁለት ዓመት ከመንፈቅ።ብዙ ጥፋት። ብዙ ኪሳራ።ትንሽ ዉጤት።በሕዝብ ድምፅ መቶ ከመቶ በሆነ ዉጤት «ተመርጥኩ» ያለዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሕዝባዊዉ ተቃዉሞ እና ጥያቄ ሕዝብን የሚያረካ መልስ ባለመስጠቱ የመቶ ሚሊዮኖቹ ሐገር ዛሬ፤  በመለወጥ እና አለመለወጥ መሐል ግራ ቀኝ ትላጋለች።ከኢሕአፓ አባልነት እስከ በነፍጥ ታጋይነት፤ ከኢሕዴን (የዛሬዉ ብአዴን) መስራች እና መሪነት እስከ ፖለቲካ ተንታኝነት የኢትዮጵያን ፖለቲካ የኖሩበት አቶ ያሬድ ጥበቡ «መስቀለኛ መንገድ» ይሉታል።

                              

Äthiopien Abiy Ahmed OPDO
ምስል Abdulbasit Abdulsemed

ተስፋቸዉ ኢትዮጵያ ወደ ተሸላ ፖለቲካዊ ስርዓት ትሸጋገራለች የሚል ነዉ።ትለወጣለች።ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮም ለወጥ አይቀርም ባይ ናቸዉ።የሕዝብ ጥያቄ ነዉና።

                      

ግን ምን አይነት ለዉጥ።የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ ለሕዝብ ጥያቄ መልስ ያለዉን ለዉጥ አድርጓል።ጥልቅ ተሐድሶ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የካቢኔ ሹም ሽር፤የኦሕዴድ እና  የሕወሐት መሪዎች ለዉጥ፤ እስረኞች መፍታት፤የካቲት ከባተ ወዲሕ ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን መልቀቅ እና ሁለተኛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ።

ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ እንደምንሰማዉ ከባሕርዳር እስከ ነቀምት፤ ከደምቢ ዶሎ እስከ ጎንደር የተደረጉ እና የሚደረጉ ተቃዉሞዎች ገዢዉ ፓርቲና መሪዎቹ «ለዉጥ» ያሉት ለዉጥ ሕዝብ የሚሻዉ ለዉጥ እንዳልሆነ መስካሪ ነዉ።ፕሮፌሰር መሐመድ እንደሚሉት ደግሞ ሕዝብ የሚሻዉ  የጥገና ለዉጥ አይደለም።የሥርዓት እንጂ።

                                        

አቶ ያሬድ ጥበቡም  ለዉጡ  አይቀሬ ነዉ ባይ ናቸዉ።ለለዉጡ ሰዎስት ቢሆኖች ሴናሪዮዎችን ያስቀምጣሉ።አንደኛዉ የዛሬ አርባ ዓመት ግድም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ያራምደዉ የነበረዉ አይነት ነዉ ይላሉ አቶ ያሬድ።ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት።ሁለተኛዉ የዛሬ 27 ዓመት ግድም ኢሕአዴግን ለስልጣን ያበቃዉ ዓይነት በአሜሪካኖች ግፊትና ተፅዕኖ የሚደረግ ለዉጥ ነዉ።

ሰወስተኛዉ  በኢሕአዴግ ዉስጥ ያሉ ግን የሕዝብ ጥያቄን የተቀበሉ ፖለቲከኞች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚኢደርጉት ለዉጥ ነዉ።የዚሕ ዓይነቱን ለዉጥ አቶ ያሬድ ሐገሪቱን ካደጋ ለማዳን ጠቃሚ ይሉታል።ይደግፉታልም።

                                            

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) መሪዎች በፌደራሉ መንግስት እና በሌሎች የኢአሐዴግ አባል ፓርቲዎች ላይ ያደርጉታል የሚባለዉ ግፊት ለአቶ ያሬድ እና ለመሰሎቻቸዉ  ተስፋ መሰረት ነዉ።የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፈዉ ሳምንት ያወጣዉ መግለጫ ግን ተስፋቸዉን ሳያመነምነዉ አልቀረም።

Äthiopien Regierungsvertreter
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

                              

የብአዴን መሪዎች አንድም ሆኑ ብዙ የአማራ መስተዳድር ነዋሪ ከኦሮሚያ ቀጥሎ ለለዉጥ ከፍተኛ ግፊት ማድረጉን አላቋረጠም።ከዉስጥ ይደረጋል ለሚባለዉም ሆነ ከዉጪ ይመጣል ተብሎ ለሚታሰበዉ ለዉጥ የገዢዉ ፓርቲ መስራች እና ዋና ዘዋሪ ሕወሐት ለዉጡን ለማስተናገድ መዘጋጀቱ ዛሬም እንዳጠያየቀ ነዉ።ፕሮፌሰር መሐመድ እንደሚሉት የሕወሐት መሪዎች ለለዉጥ አልተዘጋጁም።አሳሳቢ ይሉታል-ፕሮፌሰሩ።

                             

የአቶ ያሬድ አስተያየት ስጋት እና ተስፋም ከፕሮፌሰር መሐመድ ብዙ አይለይም።

                    

የካቲት 1929 አዲስ አበባ የግራዚያኒን ጭፍጨፋ አስተናግዳለች።የካቲት 1966 የረጅም ጊዜዉ ጠቅላይ ሚንስትር አክሊሉ ሐብተወልድ ሥልጣን በመልቀቃቸዉ ጨፍራለች።ሕዝባዊ ተቃዉሞ የዘመናት ያገዛዝ ሥርዓታቸዉን ያንገጫገጨባቸዉ አፄ ኃይለ ሥላሴ በአክሊሉ ምትክ እንዳልካቸዉ መኮንን ሲሾሙ አዲስ አበባ «ጉልቻ ቢቀያየር----» እያለች ጮኻለች።ዛሬ ኢሕአዴግን ከሚዘዉሩት አንጋፋዎቹ የያኔ ተማሪ፤ የንጉሱ እርምጃ ቃዋሚዎችም ነበሩ።

Äthiopien Ministerpräsident Hailemariam Desalegn kündigt Rücktritt an
ምስል picture-alliance/AP Photo

ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ የተመሰረተበት 43ኛ ዓመት  ዘንድሮ  ሲከበር የካቲት፤ የኢአሕዴጉ  ጠቅላይ ሚንስትር ሥልጣን ለቀቁ።ሐይለማርያምን የሚተካዉ ፖለቲከኛ ማንነት እስካሁን በግልፅ አልታወቀም።ይሁንና ኦሕደዴ የቀድሞ ሊቀመንበሩን አቶ ለማ መገርሳን  ወደ ምክትልነት ዝቅ፤ የፅሕፈት ቤት ኃላፊዉን ዶክተር ዓብይ አሕመድን ወደ ሊቀመንበርነት ከፍ ማድረጉ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን የመያዝ ዝግጅት ነዉ ባዮች አሉ።

ሌሎች ደግሞ ያሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን የጠቅላይ ሚንስትርነቱን፤ አቶ ዓብይ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነቱን መያዛቸዉ አይቀርም ይላሉ።አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለሕዝብ ያወጁትን ሥልጣን የመልቀቅ ዉሳኔ ሽረዉ በያዙት ሥልጣን ይቀጥላሉ የሚሉም አሉ።ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል እንደሚሉት ግን ጠቅላይ ሚንስሩ ማንም ሆነ ማን ከፖለቲካዊ «ሞት» መጠንቀቅ አለበት።የቀጣዩ ጠቅላይ ሚንስትር ማንነት ምናልባት በያዝነዉ ሳምንት ማብቂያ ይታወቅ ይሆናል።ቀጣዩ ጠቅላይ ሚንስትር እንዳልካቸዉ መኮንን መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ግን በርግጥ እሳቸዉ ይሉት እንደነበረዉ «ፋታ»  ያስፈልጋል እንበል ይሆን ወይስ ጊዜ። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ተስፋአለም ወልደየስ