1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ የቀድሞዉና የወደፊቱ መሪዎቿ

ሰኞ፣ ነሐሴ 21 2004

የአድዋዉ ወጣት አዲስ አበባን ትምሕርቱንም ጥሎ ዱር ቤቴ ሲል የወላይታዉ ሕፃን የአስር ዓመት ታላቁን ትግል ገድል ቀርቶ አካባቢዉንም በቅጡ አያዉቅም ነበር።ሰዉዬዉ ግን የሚገመት፥ የሚመስለዉን እያከሸፉ-የማይገመት፥ የማይመስለዉን የማድረግ አባዜ ያኔ ተጠናወታቸዉ እንበል ይሆን?

https://p.dw.com/p/15xcK
Ethiopian Prime Minister Meles Zeinawi speaks to reporters after a meeting with Egyptian Prime Minister Essam Sharaf, not pictured, in Cairo, Egypt, Saturday, Sept. 17, 2011. Egypt's prime minister says Ethiopia's planned Nile River dams "could be a source of benefit" _ a significant change in tone by Egypt's new rulers on the highly contentious issue. Essam Sharaf's remarks came after talks in Cairo with Ethiopian Prime Minister Meles Zenawi on Saturday. It's the first visit by an Ethiopian official since Hosni Mubarak was ousted by a popular uprising in February.(Foto:Khalid El-Fiqi, Pool/AP/dapd)
አቶ መለስምስል AP


የአንድ ሐገር ግን የሰሜን-ደቡብ ተቃራኒ መንደሮች ዉልዶች፣ የሩቅ ለሩቅ ማሕበረሰብ ግኝቶች፣ ናቸዉ።የአንድ ተቋም ተማሪዎች ግን ሐኪምና መሐዲስ የመሆን ፍላጎት ያለያያቸዉ፣ በጅምር ማቋረጥና ማጠናቀቅ የሚያቃርናቸዉ፣ እድሜ በአስር አመት ያራራቃቸዉ ወጣቶች።ሰሜን ተወልደዉ፣ ሰሜን ያደጉት፣ ሰሜን ታግለዉ ለመሪነት የበቁት ፖለቲከኛ የሚከተሉት መርሕ ደቡብ ተወልደዉ፣ ደቡብ አድገዉ ደቡብ የሚስተምሩትን መሐንዲስ ልብ አማልሎ ከፖለቲካዉ መዶሉ የሁለቱን ደንዳና ልዩነት እያሰለ፣ ሰስ አድነታቸዉን ማደንደኑ በርግጥ አላጠያየቅም።አዲሱ ፖለቲከኛ ምክትል መሪ፣ አለቃቸዉ ሲሞቱ ደግሞ አልጋወራሽ ይሆናሉ ብሎ ያሰበ-የገመተም ከነበረ እሱ በርግጥ መሲሕ ብጤ ነዉ።ግን ሆነ።የሆነዉ የሆነበትን ግርድፍ ምክንያት፣ የሿሚ፣ ተሿሚዉ ያዉራሽ ወራሹ ፖለቲካዊ ስብዕና ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ። አብራሁኝ ቆዩ።


ዘመኑ በርግጥ ሩቅ ነዉ።1960ዎቹ አጋማሽ።ያኔ የታተመችዉ አንዲት የሕክምና ፋኩሉቲ መፅሔት ከለጠፈቻቸዉ ፎቶ ግራፎች ባንዱ፥ በመደዳ የተደረደሩት ወጣቶች ለዚያ ትምሕርት ቤት አዲሶች ነበሩ።የዘመኑ ርቀት፥ የመፅሔቷ መጎሳቆል፥ የፎቶዉ ጥቁርና ነጭነት-የባለፎቶ ግራፎቹን ማንነት መለየቱ ግር ያሰኝ ይሆናል።ግን ካገኙት ይዩት።ከፊተኛዉ ዕረድፍ፥ ከግራ ጥግ የቆመዉን ወጣት ደግሞ ያስተዉሉ።

ሉጫ ጠጉሩ ግንባሩ ላይ ተከብሏል። ፊቱና ልብስ ያልሸፈነዉ እጁ ደማቅ ነጭ ነዉ።ወጣቱ ብስል ቀይ ነዉ ማለት ነዉ።ከብዙዎቹ አጭር ነዉ።ቀጭን።ምናልባት በዕድሜ ትንሹ ሊሆን ይችላል።እርገጠኛነኝ በማንነቱ ተስማምተናል።እሱ ለገሰ ነዉ።ለገሰ ዜናዊ አስረስ።

«ሊቀ ደቂቃን» ይላል የፎቶ ግራፉ የግርጌ መግለጫ።ያ ለስላሳ የሚመስል እጅ፥ እስኪሪብቶ-ደብተሩን ጥሎ ጠመንጃ-ቦምብ የመጨበጥ ብርታት ይኖረዋል ብሎ ማሰብ፥ ያ-ቀጭን ለንቋሳ፥ ወጣት፥ ደቂቅ ግን ሊቅ ያሰኘዉን ትምሕርት አቋርጦ ዱር-ጫቃ ይገባል ብሎ መገመት ሲበዛ ከባድ ነበር።ወጣቱ ግን ያልተገመተዉን አደረገ።ተማሪነቱን ትቶ ተጋዳላይ።ለገሰነቱን ለዉጦ መለስ ሆነ።1967

እንደተጋይ ከዛሬዉ ዶክተር ከያኔዉ ታጋይ አረጋዊ በርሔ ጋር በቅርብ ተዋወቁ።


የአድዋዉ ወጣት አዲስ አበባን ትምሕርቱንም ጥሎ ዱር ቤቴ-ሲል የወላይታዉ ሕፃን የአስር ዓመት ታላቁን ትግል ገድል ቀርቶ አካባቢዉንም በቅጡ አያዉቅም ነበር።ቦሎሶ ሶሬ ላይ ገና ሀሁን ማገበዳዱ ነበር።

ሰዉዬዉ ግን የሚገመት፥ የሚሆን፥ የሚመስለዉን እያከሸፉ-የማይገመት፥ የማይመስለዉን የማድረግ አባዜ ገና ያኔ ተጠናወታቸዉ እንበል ይሆን?

ግንቦት 1983 አሁን የያኔዉ ደቂቅ-ሰላሳዎቹን የድሜ ክልል ያገባደደ።ያ የትምሕርት ሊቅ፥ በፖለቲካዉ የተካነ፥ በስልጣንም፥ በእድሜም፥ በእዉቀትም ክብርን የደረበ።አንቱ ናቸዉ።እንደተማሪ ጥለዋት የሔዷትን አዲስ አበባን እንደ መሪ በድል አድራጊነት ተቆጣጠሩ።

በ1967 ለገሰ-መለስ ሆኖ ጫካ ሲገባ ቦሎሶ ሶሬ ላይ ረጅሙን የትምሕርት ጎዳና አንድ ሁለት ማለት የጀመረዉ ሕፃን አዲስ አበባን እንደተማሪ ኖሮ፥ ዩኒቨርስቲዋን በምሕድስና ተመርቆባት አርባ ምጭ ከገባ ሰወስተኛ አመቱ ነበር።ሰኔ 1983።

መለስ እንደ አዲስ መሪ የጥታዊቷን ሐገር ታሪክ ባዲስ መንገድ እየተነተኑ «የአክሱም ሐዉልት ለደቡቡ--- ለወላይታዉ ምኑ እያሉ» ሲጠይቁ የአርባምንጩ የዉሐ ቴክኖሎጂ ኮሌጅ (ኋላ ዩኒቨርስቲ) አዲስ መምሕር እንደ አብዛኛዉ ኢትዮጵያ ከሩቅ ተከታትለዉ፥ ምናልባትም ባዲሱ ትንታኔ ቀልባቸዉን ወደ ፖለቲካዉ ሠርቆት ይሆናል።ግን ትምሕርቱን አስቀደሙ። ለሁለተኛ ዲግሪ ወደ ፊላንድ አቀኑ።

ጥቅምት 1988 ዋሽግተን ዲሲ።ባለራዕዩ መሪ።

Ethiopian state television announced on August 21, 2012 that Hailemariam Desalegn will be acting prime minister, after the death of Ethiopian Prime Minister Meles Zenawi.
አቶ ሐይለ ማርያም ደሳለኝምስል CC-BY-SA- World Economic Forum

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን መለስን «የዳግም ትንሳኤ መሪ» በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ያወደሷቸዉም ያኔ ነበር።መለስ በሕይወት እያሉም ሆነ አሁን ካለፉ በሕዋላ በተደጋጋሚ እንደሚሰማዉ ለፕሬዝዳት ቢል ክሊተን፥ ለጆርጅ ደብሊዉ ቡሽም ሆነ ለባራክ ኦባማ፣ ለጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር፥ ለጎርደን ብራዉን ይሁን ለዴቪድ ካሜሩን፣ ለፕሬዝዳት ፍራንሷ ሚትሯ፥ ለዣክ ሺራክ ለኒኮላይ ሳርኮዚ፥ ይሁን ለሌሎች ምዕራባዉያን መሪዎች አርቆ አሳቢ፣ ከሐገራቸዉ አልፎ ለአፍሪቃ ሠላም፣ ልማትና እድገት የሚጥሩ መሪ ነበሩ።

የመለስ ራዕይ ከዋሽግተን ሲሰማ፥ የመለስ አመራር በዋሽንግተንና በተባባሪዎቻቸዉ ሲወደስ፥ ሲደነቅ ወጣቱ መሐንዲስ፥ የኮሌጅ መምሕር ሁለተኛ ዲግሪዉን ከታምፔር ዩኒቨርስቲ-ፊላንድ ተቀብሎ፥ የአርባ ምንጭ የዩኒቨርስቲዉ ዲን ሆኖ ነበር።ሐይለ ማርያም ደሳለኝ።እና አንቱም።የቀድሞዉ የደቡብ መስተዳድር የአደጋ መከላከያና ዝግጁነት ቢሮ ሐላፊ፥ የኋላዉ የቅንጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አየለ አንጌሎ ተዋወቋቸዉ።


ከምዕራብ ሐገራት መሪዎችና ፖለቲከኞች ለመለስና ለተከታዮቻቸዉ የወረደና የሚወርድላቸዉ ሙገሳ፣ ዶክተር አረጋዊ ሥለ መለስ፥ አቶ አየለ ሥለ ሐይለማርያም ከሰጡና ከሚሰጡት አስተያየት ጋር መቃረኑ ወትሮም መለስና ተባባሪዎቻቸዉ ከስልጣንም ከፓርቲም ካበረሯቸዉ፥ መለስ፥ ሐይለ ማርያምና ተባባሪዎቻቸዉ ከሥልጣን፥ ከሐገርም ካሰደዷቸዉ ፖለቲከኞች ምን ይጠበቃል ያሰኝ ይሆናል።ግን ዶክተር አረጋዊና አቶ አየለ ብቻቸዉን አልነበሩም።አይደሉም።

ጊዜዉ ግን ይሮጣል።ወይም ሰዉ ይንቀረፈፋል።መለስ ዋሽንግተን ላይ ያሉትን ያሉበት አስር አመት ዞሩ ሊገጥም ወራት ቀሩት።1997።ግንቦት ምርጫ ነዉ።መለስ ድምፅ ሰጡ።አሉም።

«የተዋጋሁት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎታቸዉን የመወሰን መብት እንዲኖራቸዉ ነበር።አሁን ይሕንን መብት ከሌሌላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ገቢር እያደረግሁ ነዉ።ከዚሕ በመድረሳችን እኮራለሁ።»

ወዲያዉ ግን ኢትዮጵያ በምርጫ ዉጤት፥ ቁርቁስ እንደታበጠጭ፥ ከረምቱን ተሰናብታ፥ አዲስ አመት አለች።መለስ ከአስር ዓመት በፊት በእሳቸዉ አመራር የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢያንስ በቀን ሰወስት ጊዜ መብላት እንደሚችል ተስፋ አድርገዉ፥ ለዚያ እንደሚጥሩም ቃል ገብተዉ ነበር።

ግን የሚገመት፥ የሚጠበቀዉ፥ ተስፋ፥ በአስረኛ ዓመቱ የወለፊንድ ባረቀ።ሰኔ የጀመረዉ የምርጫ ዉዝግብ፥ ቁርቁስ አዲስ አበባን በደም አጨቀየ፥ ድፍን ኢትዮጵያ ተንቀረቀበች። ጥቅምት 1998 ። አዲስ አበባ ብቻ ከሁለት መቶ በላይ ተገደሉ።

የተቃዋሚ መሪዎች፥ የተቃዋሚ ደጋፊ ናቸዉ ተብለዉ የተጠረጠሩ ሰዎች፥ ጋዜጠኞች፥ የሲቢክ ማሕበረሰብ አባላት፥ በጥቅሉ፥ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ግምት ከሐምሳ-እስከ ስልሳ ሺሕ የሚገመት ሕዝብ ተለቃቅመዉ ወሕኒ ተወረረ።በዚያዉ ወር መለስ እዚሕ-ቦን ነበሩ።ጥቅምት።


«የምርጫዉ ዘመቻዉ በሁሉም ዘገቦች፥ በሁሉም ዘገቦች ለክፍለ-ዓለሚቱ ምሳሌያዊ ነበር።የድምፅ መስጪያዉ ዕለትም ለክፍለ ዓለሚቱ አብነታዊ ነበር።ምክንያቱም መምረጥ ከሚችለዉ ከዘጠና ከመቶ የሚበልጠዉ ሕዝብ ድምፁን ሰጥቷልና።» አሉ።ታዲያ ግድያ፥ እስራቱን ምን አመጣዉ? ከመለስ፥ መልስ በርግጥ በሽ ነዉ።

«አምስት የእጅ ቦምቦች በፖሊሶች ላይ ተወርዉረዉ የተወሰኑ ፖሊሶችን ተገድለዋል፥፡ሌሎች ቆስለዋል።እነዚሕ ሥራ ፈት ወጣቶች ከፖሊስ ሁለት ጠመንጃ ቀምተዉም ነበር።»


አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት፥የሙያ ነፃነት ተሟጋቾች፥ ሁሉም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመለስን አምባገነነት በተመሳሳይ ድምፅ አፀደቁ።አወገዙም።

በኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ማግስት፥ የሕዋሐት ለሁለት መከፈል-ለአቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ሳይደግስ አይጣላም አይነት ነበር።መለስ የሚመሩት ቡድን ከክፍሉን ባሸናፊነት እንዳጠናቀቀ፥ (ለተሸናፊዎቹ) ለተባራሪዎቹ ያዳላሉ የሚባሉትን የእስከያኔዉ የደቡብ መስተዳድር መሪ አቶ አባተ ኪሾን በሙስና ሰበብ ላጭር ጊዜ ወሕኒ ዶሎ የርዕሠ-መንበርነቱን ሥልጣን ለአቶ ሐይለማርያም አስረከበ።

የምርጫዉ ዉጤት ዉዝግብ ደም ባፋሰሰ ድቀት ማሳረጉ ብዙ የፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚሉት ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን ሙሉ በሙሉ ከምዕራቦች እቅፍ ሲወሽቅ፥ አቶ ሐለማርያምን ደግሞ መለስ «ሲጠሯቸዉ አቤት፥ ሲልኳቸዉ ወዴት» የሚሉ አይነት ፖለቲከኛ አደረጋቸዉ።

የሰዉዬዉን ፖለቲካዊ ሥልት-ምግባር አስቀድሞ በተንበይ ይቻል ይሆናል።ግን ለሩቁ ቀርቶ ለቅርቡም ሲበዛ ከባድ ነዉ።በ1997 የኢሐዲግን የመንግሥትነት ሥልጣን ከፍፃሜዉ አፋፍ ላይ ያደረሰዉን የቅንጅት ለአንድነት፥ ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መሪዎችን ከአመት ከመንፈቅ እስራት በሕላ በምሕረት በለቀቁ ማግስት አዲሱ አመአት ሲብት አዲስ ተስፋ ይዘዉ ከች አሉ።

በ2002ቱ ምርጫ ኢሐዴግ በ99.9 በመቶ ድምፅ ማሸነፉ ሲታወጅ በአዲሱ አመአት መለስ የሰጡት አዲስ ተስፋ-ቃል ከንቱ-የከንቱ ከንቱ መቅረቱ ተረጋገጠ። አዲሱ አመዓትም ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ካሮጌዉ የባሳ እንጂ የተለየ እንዳልሆነ ግልፅ ሆነ።

ለሐይለማርያም ግን ሌላ ድል የሌላ ሹመት እርጥባን ነበር።በምርጫዉ ማግስት ነባሩን የብኤደን ታጋይ አዲሱ ለገሰን እና አንጋፋዉን የሕወሐት ፖለቲከኛ ስዩም መስፍንን ተክተዉ ባንዴ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነቱንም ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነቱንም ያዙ።«መተካካት» ይሉት ነበር መለስ።

የኒዮርክ ታይምሱ ጋዜጠኛ ጀፍሬይ ጀንትልማን እንደዘገበዉ የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ መንግሥት ከአንዲት ዩናትድ ስቴትስ ብቻ በየአመቱ ስምንት መቶ ሚሊዮን ዶላር ይቆረጥለታል። የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ፥ ዶቸ ቬለም ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዳይሰሙ ይታፈናሉ።

መለስ አሸባሪዎችን በመዋጋት፥ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት በማሳደግ፥ ለአፍሪቃ ሠላምና ብልፅግና በመጣር የማያደንቃቸዉ የምዕራብ መሪ ጥቂት ነዉ።ግን ደግሞ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ በማድረግ ይወቀሳሉ።ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፥ ጋዜጠኞችን፥ የነፃ የሙያ ማሕበራት መሪዎችን በማሰር፥ በማሰደድ፥ በማፈን ከአፍሪቃ የሚወዳደራቸዉ የለም እየተባሉ ይወገዛሉ።ለሁሉም ሞት ቀደማቸዉ።

አሉ አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ።የአርባ ሰባት አመት ጎልማሳ ናቸዉ።ልክ እንደመለስ የሰወስት ልጆች አባት።ባለቤታቸዉ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ግን እንደ ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን ከለየለት ፖለቲከኛነቱ ይልቅ ወደ ሰብአዊ መብቱ የሚያዳሉ ናቸዉ ይባላሉ።አንንዳድ ዘገቦች እንደጠቆሙት ወይዘሮ ሮማን በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የክፍል ሐላፊ ናቸዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Ethiopian students demonstrate outside Addis Ababa Tegbareed Industrial College in the capital's Mexico area., Tuesday, June 7, 2005. Police raided a technical college in Ethiopia's capital Tuesday, beating up students and firing rubber bullets on the second day of defiance of a government ban on demonstrations, witnesses said. Clashes between police and student demonstrators on Monday left a girl dead, seven people injured and hundreds arrested in protests against disputed election results that left parliament in the hands of the ruling party. (AP Photo)
ተቃዉሞ በ1997ቱ ምርጫ ማግስትምስል AP
Wahlen in Äthiopien Ethiopia's Prime Minister Meles Zenawi (L) shakes hands with an old man wearing traditional clothes just after casting his vote in his native village of Adwa, Tigray Province, on Sunday 15 May 2005. Hundreds of thousands of Ethiopians are due to vote today in the third time of democratic elections in the history of their country. EPA/STRINGER +++(c) dpa - Bildfunk+++
አቶ መለስ ከድጋፊዎቻቸዉ ጋርምስል dpa

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ





































ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ