1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ወዴት?

እሑድ፣ የካቲት 18 2010

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እለቃለሁ ካሉ በኋላ የሰው ሳይሆን የስርዓት ለውጥ ነው የምንፈልገው የሚሉ የሽግግር መንግሥት ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው። መንግሥት ደግሞ ይህን ተቃውሟል። እነዚህ ሃሳቦች እንዴት ይታረቃሉ? ኢትዮጵያስ ወዴት እየሄደች ነው?

https://p.dw.com/p/2tEfY
Äthiopien Unruhen
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

ውይይት፦ ኢትዮጵያ ወዴት?

ኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ  በፍጥነት የሚለዋወጡ ክስተቶችን እያስተናገደች ነው። በነዚህ ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎችም የዜጎችን ልብ እያንጠለጠሉ እና ብዙ ጥያቄዎችን እያስነሱ ነው። ለዓመታት ከተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ በኋላ ካለፈው ሳምንት አንስቶ ታዋቂ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በይቅርታ እና ክሳቸው እየተቋረጠ በመለቀቅ ላይ ናቸው።

በዚህ ሂደት መሀል ከ10 ቀናት በፊት የሀገሪቱ  ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው የተጠበቀ ነበር የሚሉ ቢኖሩም ማነጋገሩ ቀጥሏል። ማን ይተካቸዋል የሚለውም ከመላ ምት በስተቀር እስካሁን ቁርጥ ያለ መልስ አላገኘም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳይ አነጋግሮ ሳያበቃ በማግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ሌላው ካለፈው ሳምንት አንስቶ የሚያጠያይቅ ዐብይ ክስተት ሆኖ ዘልቋል። መንግሥት አዋጁ ሀገሪቱን ለማረጋጋት አስፈላጊ ነው ቢልም የህዝቡን ልዩ ልዩ መብቶች ያፍናል ሀገሪቱንም ለባሰ አደጋ ያጋልጣል የሚሉ ተቃውሞዎች እና ትችቶች እየተሰነዘሩበት ነው። አዋጁ ከተደነገገ በኋላም ህብረተሰቡ ሌሎች ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ በመጠየቅ አድማ ማካሄዱን ቀጥሎ ነበር የሰነበተው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እለቃለሁ ካሉ በኋላ የሰው ሳይሆን የስርዓት ለውጥ ነው የምንፈልገው የሚሉ የሽግግር መንግሥት ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው። መንግሥት ደግሞ ይህን ተቃውሟል። እነዚህ  ሃሳቦች እንዴት ይታረቃሉ? ኢትዮጵያስ ወዴት እየሄደች ነው? የዛሬው እንወያይ የሚያተኩርባቸው ነጥቦች ናቸው።

በዚህ ውይይት ላይ የሚሳተፉ አራት እንግዶችን ጋብዘናል። እነርሱም ከ6 ዓመታት እሥር በኋላ ባለፈው ሳምንት የተፈታው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ሙላቱ ገመቹ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በምህጻሩ ኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር፣ አቶ ስዩም ተሾመ የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የድረ ገጽ ፀሀፊ አቶ ቻላቸው ታደሰ የፖለቲካ ተንታኝ ናቸው። ሙሉውን ውይይት የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያዳምጡ።

ኂሩት መለሰ