1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

እቅዱ በአምስት ዓመታት ወደ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል

ረቡዕ፣ ኅዳር 20 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት "ብርሃን ለሁሉም" የተባለውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማስፋፊያ እቅድ አዲስ አበባ ላይ ይፋ አድርጓል። እቅዱ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች "በቂ፣ አስተማማኝ እና አቅምን ያገናዘበ ጥራት ያለው" የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማቅረብ ያለመ ነው። 

https://p.dw.com/p/2oO7U
Ukraine Elektrizität - Umspannwerk bei Kiew
ምስል picture-alliance/dpa/D. Karmann

"ብርሃን ለሁሉም"-እንዴት?

350,000 ኢትዮጵያውያን የኤሌክሪክ ኃይል አገልግሎት ፍለጋ ተመዝግበው ላለፉት በርካታ አመታት ተጠባብቀዋል። ከእነዚህ መካከል 50,000ዎቹ ከመመዝገብ ባሻገር የሚጠበቅባቸውን ቅድመ-ክፍያ አጠናቀው ነበር። በዓለም ባንክ የኃይል ከፍተኛ ባለሙያው ራሑል ኪትችሉ እንደሚሉት አገሪቱ የኤሌክትሪክ ደንበኞቿን ከኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጋር በማገናኘቱ ረገድ እምብዛም አልተሳካላትም። 

"ኢትዮጵያ በርካታ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት መዋዕለ ንዋይ አላት። የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እና የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ አውታሮች ግንባታን መውሰድ ይቻላል። የጎደለው የአገልግሎት አቅርቦት የምንለው የመጨረሻው ግንኙነት ነው። የተጠቃሚዎችን እና የመሳሰሉትን የማገናኘቱ ሥራ። በከፍተኛነቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም እና ወደ 60 በመቶ የሚሆኑትን ከተሞች እና መንደሮች የሚሸፍን የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ በአገሪቱ ይገኛል። ችግሩ ትክክለኛ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ምጣኔው በጣም ትንሽ ነው።" 

ራሑል ኪትችሉ እንደሚሉት የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙት ኢትዮጵያውያን 30 በመቶ ብቻ ናቸው። ከእነዚህ መካከል 20 በመቶው ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት ቀሪ 10 በመቶ ደግሞ ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት ውጪ አገልግሎቱን ያገኛሉ። 

Nil Dammbau in Äthiopien Archiv 28.05.2013
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ፈላጊ ዜጎቹን ከአገልግሎቱ ለማገናኘት ያቀደ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል። ለሰባት አመታት ተግባራዊ የሚሆነው እቅድ የዓለም ባንክ ለአገሪቱ በሰጠው ብድር የሚሰራ ሲሆን «ብርሃን ለሁሉም» የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል። አቶ ብዙነህ ቶልቻ እቅዱን ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለበት የኢትዮጵያ ውኃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒሥቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው።

"ብርሃን ለሁሉም በኢትዮጵያ ብሔራዊ የኤሌክትሪክፍኬሽን አቅርቦት ፕሮግራም ነው። የዚህ ፕሮግራም አላማ ሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በቂ፣ አስተማማኝ አቅምን ያገናዘበ ጥራት ያለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት እንዲኖረው ለማድረግ ተብሎ የተነደፈ ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙ በመላ አገሪቱ የሚገኙትን ሁሉንም ዜጎች ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት እና ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት ውጪ ያሉትን የሕብረተሰብ ክፍሎች ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።"

የዓለም ባንክ ባለሙያው እንደሚሉት በኃይል ማመንጫ መሰረተ-ልማቶች ላይ ብቻ አተኩሮ የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት አዲሱ እቅድ የትኩረት ለውጥ ያደረገበት ነው። በተለይም በኤሌክትሪክ ቋት እና በደንበኞች መካከል ያለውን ክፍተት ማጥበብ ቀዳሚው ትኩረት ነው ያሉት ራሑል ኪትችሉ እቅዱ በአምስት ዓመታት ወደ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል ብለዋል።

"በመጀመሪያው አምስት አመት ወደ 1.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ይገመታል። በአሁኑ ወቅት በየአመቱ ከብሔራዊው የኤሌክትሪክ ቋት ጋር ግንኙነት የሚፈጠርላቸው ሰዎች 52,000 ናቸው። ይኸንን ቁጥር በሚቀጥሉት አምስት አመታት ወደ ግማሽ ሚሊዮን እና አንድ ሚሊዮን ማሳደግ ይፈልጋሉ። ስለዚህ ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ብቻ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። ከዚህ መካከል የዓለም ባንክ 375 ሚሊዮን ዶላር ለማቅረብ ተደራድሯል። የቀረው ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከተጠቃሚዎች የግንኙነት ክፍያ ይፈጸማል። ስለዚህ ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ከሚያስፈልገው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወደ 50 በመቶ ገደማ የሚሆነው ቃል ተገብቷል።"

በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የተጀመረው ፓወር አፍሪቃ እቅድ ያዘጋጀው መረጃ እንደሚጠቁመው 2,261 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በምታመነጨው አገር የአገልግሎት ግንኙነት ያላቸው ዜጎች 23 በመቶ ብቻ ናቸው። በገጠር አካባቢ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል 8 በመቶ ብቻ ይኸንንው አገልግሎት ያገኛሉ። አቶ ብዙነህ እንደሚሉት በዚህ እቅድ 65 በመቶ ኢትዮጵያውያንን ከብሔራዊው የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት ጋር የማገናኘት እቅድ ተወጥኗል። 

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ