1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ልማት ሽርክና ገባች

ረቡዕ፣ የካቲት 28 2010

ኢትዮጵያ፣ ሶማሌላንድ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ንብረት የሆነው ዱባይ የወደቦች አስተዳደር ኩባንያ ባለፈው ሳምንት የበርበራ ወደብን ለማልማት ሽርክና ገብተዋል። አብዛኛው የወጪ እና የገቢ ንግዷ በጅቡቲ ላይ ለተወሰነው ኢትዮጵያ ስምምነቱ መልካም ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2ttnI
Somaliland Reportage neuer Hafen in Berbera
ምስል DW/J. Jeffrey

ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ 19% ባለቤት ሆናለች

ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ 19 በመቶ ባለድርሻ ሆናለች። ባለፈው ሳምንት በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በተፈረመው ሥምምነት መሠረት ዱባይ ወርልድ የተባለው ዓለም አቀፍ የወደቦች አስተዳዳሪ ኩባንያ 51 በመቶ፤ የሶማሌላንድ መንግሥት ደግሞ ቀሪ 30 በመቶ ድርሻ ባለቤቶች ናቸው። በኢትዮጵያ በኩል በዱባይ ተገኝተው ውሉን የፈረሙት የትራንስፖርት ምኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ "አንድ አመት ከዘለቀ ድርድር በኋላ" ከሥምምነት መደረሱን ተናግረዋል። 

"ሥምምነቱ ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛቷ እና በኤኮኖሚዋ እያደገ ላለው የወጪ እና ገቢ ንግድ ተጨማሪ የማጓጓዣ በር እንድታገኝ ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪ በበርበራ ወደብና በአካባቢው ልማት ኢትዮጵያ የሚኖራት ተሳትፎ፤ የኤኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት እና ለሶማሌላንድ እና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ተጨማሪ ዕድል ለመፍጠር ይረዳል" ሲሉም ተናግረዋል። 

የአፍሪቃ ኅብረትን ጨምሮ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና ባታገኝም ነፃነቷን ባወጀችው ሶማሌላንድ የሚገኘው የበርበራ ወደብ በቂ መሠረተ-ልማቶች የሉትም። በምሕጻሩ ዲፒ ወርልድ ተብሎ የሚጠራው የዱባይ የወደቦች አስተዳዳሪ ኩባንያ የበርበራ ወደብን ለማልማት እና ለማስተዳደር ውል ከገባ ከአንድ ዓመት በላይ አልፎታል። ኩባንያው ከሶማሌላንድ መንግሥት ጋር ለ30 አመታት የሚዘልቅ ሥምምነት አለው። የወደቡን መሰረተ-ልማቶች ለመገንባት እና ለማስፋፋት እስከ  442 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ተመድቦለታል። ኢትዮጵያ በበኩሏ ወደቡን ለመጠቀም የሚያስፈልጉ መሰረተ-ልማቶችን ትገነባለች።

VAE Dubai Hafen in Dschabal Ali Container Schiff
ምስል AP

የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ምኒስትር ዶ/ር ሳድ አል-ሽሬ ውጥኑን አገራቸው "የገጠሟትን የሥራና የመዋዕለ-ንዋይ እጦት ችግሮች መፍታት የሚችል እጅግ ጠቃሚ ዕቅድ" ብለውታል። "በሶማሌላንድ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዲፒ ወርልድ መካከል ሥምምነት የፈረምንበት የዚህ ታሪካዊ ሁነት አካል በመሆኔ እጅግ ተደስቻለሁ። የበርበራ ወደብን አቅም በማሳደግ ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከአጠቃላይ ከቀጣናው አገራት እየጨመረ የመጣውን የመርከቦች ምልልስ ማስተናገድ እንዲችል እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሰራለን" ሲሉም አክለዋል። 

ስምምነቱ በተፈረመ ማግስት የሶማሌላንድን ሉዓላዊነት ከማትቀበለው ሶማሊያ ዘንድ የነበረው ምላሽ በዶ/ር ሳድ አል-ሽሬ ደስታ ላይ ውሐ የሚቸልስ ነበር። የሶማልያው ጠቅላይ ምኒስትር ሐሰን አሊኻይሬ በሰጡት መግለጫ ሶስትዮሹን ስምምነት "ጎዶሎ እና ጥቅም የለሽ" ብለውታል።

የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሒ አብዲ በበኩላቸው "ሥምምነቱ አዲስ አይደለም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።የፕሬዝዳንቱ ቢሮ ባወጣው መግለጫ የአሁኑ ሽርክና የሶማሊላንድ መንግሥት ከዱባይ የወደቦች አስተዳዳሪ ኩባንያ ጋር ከዚህ ቀደም የፈረመው እና በአገሪቱ ምክር ቤት የጸደቀው ሥምምነት ተቀጥላ መሆኑን በመግለፅ አገራቸው የቀረበባትን ወቀሳ ውድቅ አድርጓል።

ለሚቀጥሉት 30 አመታት የበርበራ ወደብን የሚያስተዳድረው ዲፒ ወርልድ ተጨማሪ የመርከብ መቆሚያዎች የመገንባት ውጥን እንዳለው አስታውቋል። የወደቡን አገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ ዘመናዊ መሳሪያዎች ለወደቡ ይዘጋጃሉ። የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሱልጣን ቢን ሱላዬም ሥምምነት በተፈጸመበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ከኢትዮጵያ ጋር የገቡበትን ሽርክና ደጋግመው አድንቀዋል። "ለኢትዮጵያ፣ ለሶማሌላንድ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬቶች እና ዲፒ ወርልድ ታሪካዊ ቀን ነው።" ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው "ኢትዮጵያ የውጥኑ አንድ አካል መሆኗ ደግሞ ብዙ አቅም እና ጥንካሬ ይሰጠናል።" ብለዋል። 

ሱልጣን ቢን ሱላዬም የሚመሩት ዲፒ ወርልድ ከ40 በላይ በሚሆኑ አገሮች ከ78 በላይ የባሕር እና ደረቅ ወደቦች የሚያስተዳድር ግዙፍ ኩባንያ ነው። ኩባንያው የበርበራ ወደብን ለ30 አመታት ለማስተዳደር ሲዋዋል በኢትዮጵያ ገበያ ላይ አተኩሮ ይመስላል። ዋና ሥራ አስፈፃሚው የኢትዮጵያን የሕዝብ ቁጥር እና የኤኮኖሚ እድገት እየጠቀሱ የወደቡን አስፈላጊነት ለማጉላት ተደጋጋሚ ጥረት አድርገዋል።

መቀመጫውን በዱባይ ያደረገው ኩባንያ በሶማሌላንድ ከበርበራ ወደብ አቅራቢያ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመመስረት ተጨማሪ ሥምምነት ፈርሟል። የንግድ እንቅስሴ እና መዋዕለ-ንዋይን ማበረታታት እንዲሁም ለአገሬው ሰው የሥራ እድል መፍጠር ዋንኛ ግቦቹ ናቸው።  

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ