1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያና የዓለም ንግድ ድርጅት

Merga Yonas Bulaረቡዕ፣ ታኅሣሥ 6 2008

የዛሬ 13 ዓመት ገደማ ነበር ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት «WTO» አባል ለመሆን ጥሪዋን ያቀረበችዉ። የንግድ ድርጅቱ አባል መሆን በንግድ ከዓለማቀፍ ገበያዎች ጋር ለመተሳሰር እና ለመገበያየት ይረዳታል በተባለዉ ላይ በአዉሮጵያኖቹ በ2007 ዓ,ም አባል ለመሆን የመግባባያ ሰነድ ፈርማለች።

https://p.dw.com/p/1HONz
Logo Welthandelsorganisation WTO

[No title]

ከዛ በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ,ም የዉጭ ንግድን በተመለከተ ለአባልንት ያቀረበቻቸው ሠነዶች እንዲዳሰሱ ተደርጎ ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ በንግድ ሚኒስቴር በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ልሳነወርቅ ዘርፉ ለጋዜጤኞች መግለጫ በሰጡበት ጊዜ ኢትዮጵያ በአዉሮጳዉያኖቹ 2015 ዓ,ም የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንደምትሆን ተናግረዉ ነበር። ከትላንት ማክሰኞ ታህሳስ 5 ጀምሮ እሰከ ነገ ወዲያ አርብ ታህሳስ 8 ድረስ በናይሮቢ፣ ኬንያ፣ በሚደረገዉ 10ኛዉ የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ፣ አቶ ልሳነወርቅ ዘርፉ ከሁለት ዓመት በፊት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን ትቀላቀል ይሆን?

Kenia WTO Treffen in Nairobi
ምስል picture-alliance/dpa/D. Irungu

አሁን ካሉት የ 161 የድርጅቱ አባል አገራት ዉስጥ 150ዎቹ ታዳጊ አገሮች ሲሆኑ ካዛክስታንና ላይቤርያ በድርጅቱ አባል በመሆን 162ኛና 163ኛ ደረጃ ላይ ተመዝገበዋል። በናይሮቢ በሚካሄደዉ በዚህ ስብሰባ ላይ አፍጋኒንስታን ከ11 ዓመት በኋላ አዲሲትዋና 164ኛዋ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንደምትሆን ይጠበቃል። ላለፉት 13 ዓመታት ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን እየተጓዘች ቢሆንም አሁን የድርጅቱ አንዷ አካል ትሆናለች ብሎ ደፍሮ ማዉራት እንደሚከብድ ባለሞያዎች ይናገራሉ። የዓለም የንግድ ድርጅትን ለማቀላቀል ከሚወስደዉ ረጅም ዓመታት እና አስፈላጊዉን ሠነዶች አሟላቶ አባል ለመሆን ለደሃ አገሮችን ከባድ ፈተና እንደሆነ በርሊን በሚገኘዉ የኢኮኖሚና የፖለትካ ተቋም ወይም በጀርመንኛ አጠራሩ Stiftung Wissenschaft und Politik ባለሙያ የሆኑት ዶከተር ሄርቤርት ዲትር ለዶቼ ቬሌ ስናገሩ፣ <<ለኔ የዓለም የንግድ ድርጅት «WTO» ከደኃና በማደግ ላይ ከሚገኙ አገሮች አኳያር ሆኜ ስመለከተዉ ትልቅ ትርጉም አለዉ። ትንንሽ አገራት ማለት ድሆች አገራት ለምሳሌ አፍሪቃ ዉስጥ በሚገኙት በትልቅ ፕሮዤ ላይ አይሳተፉም። በአዉሮጳና በዩኤስ አሜሪካ መካከል ሊደረግ የታቀደ የንግድና የማዕለንዋይ ፍሰት ስምምነት ላይ አይሳተፉም። ስለዚህ ነዉ የዓለም የንግድ ድርጅት «WTO» ለአፍሪቃ አገሮች ትልቅ ትርጉም የሚኖረዉ። እነዚህ አገራት ወደ ጫፍ ማለትም ወደ ዳር በመገፋት ጉዳት ይደርስባቸዋል። ድሃ አገሮች በዚህ እቅድ የመግባት አመቺ ሁኔታ ስለሌላቸዉ ወይም አቅም ስለሌላቸዉ የዓለም የንግድ ድርጅት ብቻ ነዉ በንግዱ ዘርፍ ዉስጥ እነሱን በማካተትና በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ቦታ እንዲያገኙ ሊረዳቸዉ የሚችለዉ።>>

የዓለም የንግድ ድርጅትን በቅድምያ ማሟላት ያለበት ነጥብ፤ ድርጅቱ የትኛዉንም አገር በንግድ ሂደቱ ዉስጥ ለይቶ መጥቀም ወይም ደግሞ መጉዳት እንደሌሌቤት በመርህ ደረጃ ተቀምጧል። በኢትዮጵያ ወይም የየትኛዉም አገር ንግድ ዉስጥ የተሳተፉት የዉጭም ሆነ የአገር ዉስጥ ኩባንያዎች አገሮቹን በአንድ ዓይን ማየት እንዳለባቸዉ የዓለም የንግድ ድርጅት እንደ መርህ እና አንድ አገር አባል ለመሆን ከተፈለገ ማሟላት ያለበት ነጥብ ነዉ ሲል ያሳስባል። በአዲስ አበባ ዩንቬርስቲ በኤኮኖሚክስ ክፍል ትምህርት የማይክሮ ኤኮኖሚክስ እና የእድገት ፖሊሲ ምሁሩ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ እሄን ጉዳይ አስመልክቶ በምሳሌነት ስያስረዱ፣ <<ምን ማለት ነዉ፣ ለምሳሌ ባርክሌይስ ባንክ የሚባለዉ የእንግሊዝ ባንክ ወደ ኢትዮጲያ ቢመጣ፣ አይ ባርክሌይስ ከባድ ነህ፣ ካንተ ጋር ዉድድር አንችልም ብለህ እሱ ላይ እንቅፋት መሆንና ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነገሮችን ማቃናት እትችልም ማለት ነዉ። በእኩል አይን ልታያቸዉ ይገባል ማለት ነዉ።>>

በላይ ከተጠቀሰዉ መርህ ጎን ለጎን የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን አገራት ለንግድ የሚቃርቡትን፣ ማለትም በግብርና ምርቶች፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ያሉትን፣ ለዉጭ ኩባኒያዎች ነፃ እንድያደርጉ የሚያስገድዳቸዉ ማዕቀፎች በስምምነቶቹ ዉስጥ ትልቅ ቦታን ይዘዉ ይገኛል። ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን ጉዞዉን ያስረዘመባት በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ያሉትን በተለይም በፋይናንስና በቴሌኮሙኒኬሼን ዘርፎች ለዉጭ የንግድ ተቋማት መክፈት አለመፈለጓ መሆኑን የተለያዩ ዘገባዎች ያትታሉ። ከሦስት ወይም ከአራት ዓመት በፊት በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ የዉጭ ኩባንያዎች ቢገቡ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚል ጥናት አድርገዉ እንደነበር የሚናገሩት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ የኢትጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ የንግድ ባንክ እና ከኢንዱስትሪዉም እንደ ናሙና ወስደዉ እንዳጠኑ ገልፀዋል። ይሁን እንጅ የጥናቱ ማጠቃልያ የነበረዉ ይለሉ ፕሮፌሴሩ፣ <<የመጣንበት ማጠቃልያ፣ የኢትዮጲያን አየር መንገድ መወዳደር ይችላል፣ የባንክ እና ፋይናንስ ሴክቴሩ ግን መወዳደር አይችልም፣ የኢንዱስትሪ ሴክቴሩም መወዳደር አይችልም፣ ስለዚህ በእኛ ግምት አሁን ባለበት ደረጃ WTO ብትገባ አገሪትዋ በእነዚህ የኤኮኖሚ መስኮች ላይ ተወዳዳሪ ሆና ብቁ መሆን አትችልም ብለን ነዉ ያጠቃለልነዉ። ይሄ እንግዲህ አንድ አራት ዓመት ሆኖታል።>>

Äthiopien Textilindustrie Fabrik Näherinnen
ምስል Jeroen van Loon

በፈረንጆቹ 2001 ዓ,ም ላይ የባንክ እና የቴሌኮሙኒኬሼን ጥናት አድርገዉ እንደነበር የሚናገሩት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ በዚህ ዘርፍ የዉጭ ኩባኒያዎች ቢመጡም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንኳን የፋይናንስ ዘርፉን የመቆጣጠርና የማስተዳደር አቅም እንደሌላቸዉ ጬምረዉ ተናግረዋል። ከ15 ዓመት በኋልም ቢሆን ይላሉ ፕሮፌሰር አለማየሁ፤ እነዚህ ዘርፎች እያደጉ አይደሉም፤ የመወዳደርም አቅምም የላቸዉም። እስከ መጨረሻዉ በዚህ መቀጠል ስለማይችሉ መፍትሄ ሊሆን የምችለዉ ይላሉ ፕሮፌሰሩ በመቀጠል፤ «ሁልጊዜ ጠብቀኻቸዉ አትችልም፣ ስለዚህ ለምን ሊሰሩ ከሚችሉ የውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና አድርገዉ ለምን ሊብራላይዝ አይደረግም። ለምሳሌ የባንኮቹን አስተዳደር ብትሰጥ፣ ቴሌኮሙ ጥሩ ከሆኑ የዉጭ ድርጅቶች ጋር ተወዳድሮ ከሆነ ጋር በሽርክና ለምን አትሰራም። ለዚህ ደግሞ ምሳሌ ከፈለገን ኬኒያ አለ። ኬንያ ዉስጥ አሁን ሳፋር ኮም የሚባል ኩባኒያ አለ። ግማሹ የእንጊሊዝ ነዉ። ቮዳፎን የሚባል ኩባንያ አለ። አብዛኛዉን እጅ ግን የያዘዉ የኬንያ መንግስት ነዉ። ሳፋር ኮም የሚሰጣቸዉ አገልግሎቶች፣ በቴሌኮም፣ በአፍሪቃ ደረጃ አንደኛ የሚባሉ ናቸዉ። በተለይ በሞባይል ባንኪንግ፣ ከዓለም አንደኛ ናት።»

Äthiopien Textilindustrie Fabrik H&M Produktion
ምስል Jeroen van Loon

እነዚህ ዘርፎች ላይ የዉጭ ባለሃብቶች እንድሳተፉበት በኢትዮጵያ መንግሥት በኩልም ቢሆን እቅድ እንደሌለ ይጠቀሳል። ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት እነዝህን የንግድ ዘርፎች ለዉጭ ኩባንያዎች ለመክፈት ተባ ያለበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? የቀድሞዉ የንግድና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ ኢትዮጵያ ለሎችን ለማስደሰት እነዚህን ዘርፎች ለዉጭ ድርጅቶች መክፈት እንደማትፈልግ ተናግረዉ ነበር። እንደ አቶ ግርማ ብሩ የአገሪቱን ኤኮኖሚ በሚረዳበት አኳኋን ለተወሰኑ ዘርፎች በሯን እንደምትከፍት ግን የንግድና የልማት ግቦቿን የማያሳካ ከሆነ ለዉጭ ተቋማት እንደማትሰጥ ተናግረዉ ነበር። ሌሎችም ባለስልጣናት ቢሆኑ ኢትዮጲያ በሯን እንድትከፍት ስትጠየቅ መልሳቸዉ የሚሆነዉ ዘርፉ የአገሪቷን ብሔራዊ ጥቅም በጣም ሊጎዳ የሚችል ቦታ ስለሆነ በሯን እንደማትከፍት ነዉ የሚናገሩት። ይሁን እንጅ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ባንኩን በተመለከተ ኢትዮጵያ ተባ ያለችበት ምክንያት የመወዳደር አቅም ማጣት ጉዳይ ሲሆን ፣ ማለትም የኢትዮጵያ የንግድ ባንክ አጠቃላይ ሃብቱ ከ 5 ቢሊዮን ዶላር የማይበልጥ ሆኖ የብሪታንያን ቤርክሌይ 2,2 ትርልዬን ዶላር ይዞ መወዳደር አይችልም ሲሉ አስረድተዋል። ቴሌኮምንኬሼንን በተመለከተ ደግሞ የመወዳደር አቅም ማጣት እና የፖለቲካ ቁጥጥር እንዲኖርበት ስለተፈለገ ነዉ ይላሉ። እንደ ፕሮፌሴሩ ገለፃ፣ ምክንያቱ ኮሙኒኬሼንን መቆጣጠር ማለት ሁሉንም የፖለቲካ ስርዓቱን መቆጣጠር ስለሆነ ነዉ። ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ሊሆኑ የሚችሉት የሰዉ አቅም ማጣት እና አገሪቷ በቴክኖሎጂ ኋላ ቀር መሆኗንም ሳይጠቅሱ አለለፉም።


ኢትዮጵያ ይሄን ሳታሟላ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን ትችል ይሆን? ከቅርብ ግዜያት ወዲህ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን ቅድመ ሁኔታዎችን እያላላ የመጣበት ሁኔታ እንደሚታይ ዘገባዎች ያሳያሉ። ይህም እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ደኃ አገሮች አዲስ የአባልነት መስፈርት እንድሰጣቸዉ ስሆን አገራቶቹ ኤኮኖሚ እያደገ በሄደ ቁጥር የተወሰኑትን ዘርፎችን ቀስ በቀስ ለዉጭ ኩባኒያዎች እየከፈቱ እንዲሄዱ ያስገድዳቸዋል። ይሁን እንጅ በንግድ ሚኒስቴር በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ክፍል ኃላፊ «Multilateral Trade Relations » አቶ ልሳነወርቅ ዘርፉ ከ2 ዓመት በፊት በጋዜጣዊ መግለጫቸዉ እንዳታቱት ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን በዚህ ዓመት ትቀላቀል ይሆን? ይህን ጉዳይ በተመለከተ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ በመቀጠል፣ <<እኔ ብዙ አልጠብቅም። ለምን ካልከኝ WTO ራሱ የችሮታ ጊዜ አለዉ። ቅድመ ሁኔታዎች ቢኖሩም እንዲህ እንዲህ አርግ የሚባሉ አስገዳጅ ሁኔታዎች ብኖሩም ላደጉ አገሮች የሚሰጠዉ የችሮታ ግዜ አለ። በአንድ ግዜ ክፈተዉ አይሉም፣ በአንድ ግዜ ሁሉንም ፈፅም አይልም። በመሰረታዊ ኃሳብ ደረጃ ማለት ነዉ። ግን እንዳልኩት የባንክ ዘርፋችንን ሳየዉ፣ የፋይናንስ ዘርፋችንን ሳየዉ፣ የብሔራዊ ባንክን የመቆጣጠር አቅም ሳየዉ፣ የቴሌኮሙኒኬሼን ዘርፉ ድክመቱን ሳየዉ እናም መንግስት ደግሞ የቴሌኮሙኒኬሽን የመቆጣጠር ፍላጎቱን ሳየዉ እኔ ብዙ አልጠብቅም።>>

መርጋ ዮናስ
አዜብ ታደሰ

Äthiopien Textilindustrie Fabrik Näherin
ምስል Jeroen van Loon