1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጁባ ስብሰባ አድርገዋል

ረቡዕ፣ ሐምሌ 19 2009

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች የደቡብ ሱዳን ጦርነት ሠላማዊ መፍትሔ በሚያገኝበት ሥልት ላይ ጁባ ዉስጥ ባለፈው እሁድ እና ሰኞ ተነጋግረዋል፡፡ የኡጋንዳ በፕሬዝዳንት በበኩላቸው የደቡብ ሱዳን መንግስትን እና የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ የቀድሞ አባላትን ለማስማማት እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡

https://p.dw.com/p/2h9x7
Südsudans Präsident Kiir und Ugandas Präsident Museveni
ምስል Samir Bol/AFP/Getty Images

የኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጁባ ስብሰባ አድርገዋል

ደቡብ ሱዳን በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ መንገታገት ይዛለች፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ረሃብ፣ ወዲህ ደግሞ የኮሌራ ወረረሽኝ ለበርካታ የሀገሪቱ ህዝብ ሞትና ስደት ምክንያት ሆኗል፡፡ ለችግሮቹ ዋነኛ መንስኤ የሆነውን በሀገሪቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ያለውን የፖለቲካ ቁርሾ ለመፍታት ሁሉም ላይ ታች ማለት ከጀመረ ሰነባበተ፡፡

በደቡብ ሱዳን ላይ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ፍላጎት ያላት ኡጋንዳ የችግሩ አስኳል በሆነው በገዢው ፓርቲ የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ንቅናቄ (SPLM) ክፍፍል ላይ አተኩራለች፡፡ ፕሬዝዳንቷ ዩዌሪ ሙሴቬኒ የፓርቲው የአሁን አመራሮች እና ከመሪዎቹ ጋር ተጋጭተው የወጡትን በማግባባት የንቅናቄው ተቀናቃኝ አንጃዎች እንዲዋሃዱ የማድረግ ውጥን አላቸው፡፡

ሙሴቬኒ ባለፈዉ ሳምንት ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን እና ሶስት የደቡብ ሱዳን ሚኒስትሮችን ኢንቴቤ በሚገኘው ቤተመንግስታቸው አነጋግረዉ ነበር፡፡ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት የደቡብ ሱዳን  መስራች የሚባሉት እና ህይወታቸውን በሄሊኮፕተር አደጋ ያጡትን የጆን ጋራንግ ባለቤትን ወይዘሮ ሬቢካ የእዚሁ ስብሰባ ተሳታፊ አድርገዋቸዋል፡፡ በዚሁ ስብሰባ በተደረሰበት ስምምነት መሰረት ኡጋንዳ የደቡብ ሱዳን መንግስትን እና ታስረው የተፈቱ የንቅናቄ አባላትን ለማፈራረም ለነገ ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀጠሮ መያዟ ተነግሯል፡፡

በጁባ ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚ ጥናቶች ኮሌጅ ዲን የሆኑት ማሪያል አዎ ዬል የሙሲቬኒ ሙከራ ከዚህ ቀደም በSPLM አንጃዎች መካከል ተደርሶ የነበረውን ስምምነት ማደስ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

“ይሄኛው እርምጃ ቀደም በሶስቱ የSPLM አንጃዎች መካከል በአሩሻ ተፈርሞ የነበረን ስምምነት እንደገና ማንቀሳቀስ ነው፡፡ ዩዌሪ ሙሴቬኒ ነፍስ ሊዘሩበት እየሞከሩ ነው፡፡ እነዚህ ግጭቱን ለመፍታት ያለሙ ሙከራዎች ናቸው፡፡ ሆኖም እቅዶቹ ሰላምን ሊያመጡ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ሬየክ ማቻርን እና ቡድናቸዉን ካላካተቱ ሰላም የመስፈን ዕድሉ የለም” ይላሉ ፕሮፌሰር ማሪያል፡፡     

Äthiopien Meles Alem Sprecher Außenministerium
ምስል DW/G. Tedla

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በኩልም ሆነ በግሏ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን የሚያስታውሱ ታዛቢዎች ኡጋንዳ እና ኢትዮጵያ “የአደራዳሪነት ሽኩቻ” ውስጥ መግባታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ አቶ መለስ አለም ግን ትዝብቱ “ብዙም ውኃ የሚይዝ አይደለም” ሲሉ አጣጥለውታል ፡፡ 

“ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ የደቡብ ሱዳን የሰላም ጥረት የተሳካ እንዲሆን በጋራ ይሰራሉ፡፡ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ እና የኢፌዲሪው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚህ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም ነው ያላቸው፡፡ አዲስ አበባ ላይ የኢጋድ አባል ሀገራት የመሪዎች ስብሰባ ላ በተካሄደበት ወቅት በግልጽ እንደተቀመጠው የአዲስ አበባው ስምምነት ብቸኛው የሰላም አማጭ ስምምነት ነው በሚለው ላይ የጋራ አቋም ነው ያለው፡፡ ሁለተኛ ደቡብ ሱዳን ውስት የተጀመረው የብሔራዊ ምክክር (national dialogue) ሁሉንም አካታች እንዲሆን በሚለው አቋም ላይ ኢትዮጵያም ኡጋንዳም ተመሳሳይ አቋም ነው ያላቸው” ሲሉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሽኩቻ እንደሌለ ያስምሩበታል፡፡ 

የኢጋድ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው እሁድ እና ሰኞ በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ ባደረጉት ስብሰባ የፕሬዝዳንት ሙሴቬኒን ጥረት እንደሚቀበሉት አሳውቀዋል፡፡ ሚኒስትሮቹ ካወጡት ባለ 19 ነጥብ የአቋም መግለጫ አንዱ ለዩጋንዳ ጥረት እውቅና የሚሰጥ ነው፡፡

በኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የተመራው ይህ ስብሰባ በደቡብ ሱዳን የወቅቱ ሁኔታ ላይ ምን ውሳኔዎች አሳለፈ? ምንስ አስገኘ? አቶ መለስ አለም ምላሽ አላቸው፡፡

“ጁባ አንጻራዊ ሰላም አግኝታ 58ኛውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ማስተናዷ በራሱ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ሁለተኛ የአዲስ አበባውን የሰላም ስምምነት በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ የማድረግ ዕቅድ በተመለከተ ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች ነበሩ፡፡ ይሄ የከፍተኛ ደረጃ የሰላም ስምምነት ትግበራ መድረክ የራሱን የመራሔ መንገድ እና የማስፈጸሚያ ጊዜ ሰሌዳ እንደአዲስ ማውጣቱ ስኬት ነው፡፡ ይሄ መራሄ መንገድ (roadmap) ወጥቶ የሰላም ስምምነቱ ትግበራ የተጓተተ ከመሆኑ አንጻር እንዴት ነው በተቻለ ፍጥነት ወደ ስራ መግባት ያለብን በሚለው ጉዳይ ላይ የደቡብ ሱዳን መንግስት ከኢጋድ አባል ሀገራት እና ከጋራ የክትትል ኮሚሽን (JEMC) ጋር ተባብሮ ለመስራት ውሳኔ ላይ ደርሷል” ብለዋል ቃል አቃባዩ፡፡

በስብሰባው ወቅት ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በዶ/ር ወርቅነህ የተመሩትን የኢጋድ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን አነጋግረዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ