1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኡርባኽ እና የ1/1/1994 ትውስታቸው

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 3 2003

የ 52 ዓመቱ ፍሪትስ ኡርባኽ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ናቸው። በራይን ዳርቻ በምትገኘው የኬል ከተማ የሚወለዱት ኡርባኽ ከ 1990 ዓም ወዲህ በጀርመን ብሄራዊ ጦር ውስጥ ያገለግላሉ።

https://p.dw.com/p/RcNm
ጀርመናዊው የጦር መኮንን ፍሪትስ ኡርባኽምስል DW

የመስከረም አንድ 1994 ዓም የአሸባሪዎች ጥቃት በተጣለበት ጊዜ ኮብለንስ ከተማ በሚገኘው ጦር ሰፈር ውስጥ ጥበቃ ላይ ነበሩ። ልክ እንደ ብዙው ሰው በቴሌቪዥን በቀጥታ ከኒው ዮርክ ይተላለፍ የነበረውን አሰቃቂ ጥቃት የተከታተሉት።
ኒው ዮርክ፣ ካቡል፣ ፋይዛባድ
«ሀቀኛ ስዕል ይሁን አይሁን እርግጠኛ አልነበርኩም። ገሀድ፡ እውን የማይመስል ነበር። ለማመን አዳግቶኝ ነበር። » ምንም እንኳን ባይመኙትም፡ ጥቃቱ በርሳቸው ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ኡርባኽ ወዲያውኑ ነበር የተገነዘቡት።
ምክንያቱም በኒው ዮርክ ጥንዶቹ የዓለም ንግድ ማዕከል ህንጻዎች በእሳት ይጋዩ በነበረበት ጊዜ ነበር የአሸባሪዎቹ ጥቃት በሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን፡ ኔቶ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አባል ሀገራቱ ለአጋራቸው ዩኤስ አሜሪካ የድጋፍ ትብብራቸውን ያሳዩት። የጀርመን ብሄራዊ ጦርም ከጥቂት ወራት በኋላ በፌዴራዊው ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት በሂንዱኩሽ የምትገኘዋን ሀገር ጸጥታ በማረጋጋቱ ዓለም አቀፉ የአፍጋኒስታን ተልዕኮ የተሳተፈው። ፍሪትስ ኡርባኽ በዚያን ጊዜ በጦር ቡድኑ ስምሪት ዕቀዳ ላይ ሰርተዋል። ወደ አፍጋኒስታን መዲና ካቡል የተላከው የመጀመሪያው የጀርመናውያኑ ጦር ቡድን መደራጀት እና መሰልጠን ነበረበት።
የቶራ ቦራ ተልዕኮ
ኡርባኽ በ 1994 ዓም መጨረሻ በቱርክ በተካሄደ አንድ የኔቶ ልምምድ ላይ ተሳታፊ ነበሩ። የአፍጋኒስታኑ ተልዕኮ በአባል ሀገራቱ መካከል ዋነኛ የመወያያ ነጥብ ነበር። ቶራ ቦራን ለመደብደብ ወደ አፍጋኒስታን ይበሩ የነበሩ የ B-52 ተዋጊ አይሮፕላኖች በሰማዩ ላይ ትተውት ያለፉት ጢስ ማየታቸውን ኡርባኽ ያስታውሳሉ። ያኔ ነበር በርግጥም የተልዕኮው አካል መሆናቸው በግልጽ የተሰማቸው።
ለፍሪትስ ኡርባኽ ከቤተሰባቸው ለረጅም ጊዜ የሚለዩበት ገሀድ ከዚያ በኋላ የተለመደ ሆነ። የጦር መኮንኑ ኡርባኽ ከዚያ በቀጠሉት ዓመታት በተደጋጋሚ ወደ አፍጋኒስታን ተልከዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍጋኒስታን የሄዱት በ 1996 ዓም በመጸው ወራት ነበር። «ልጆቼ ህጻናት ነበሩ፤ ባልተቤቴ ዘገየም ፈጠነ አንድ ቀን ወደ ውጭ ሀገር እንደምላክ ታውቅ ነበር። » ኡርባኽ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሚገባ ይወጡ ዘንድከቤተሰባቸው ሙሉ ድጋፍ አግኝተዋል። « ባልተቤቴ ከወታደር ቤተሰብ በመምጣትዋ፡ የአንድ ወታደር ህይወት ምን መሆኑን እና የሚከፈለውንም ዋጋ ታውቃለች። »

ሞት በፋዛባድ

ለዚሁ ተልዕኮ የሚከፈለው ዋጋ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን ፍሪትስ ኡርባኽ በቀጠሉት ዓመታት በተደጋጋሚ ሊገነዘቡት ችለዋል። በሰሜናዊ አፍጋኒስታን በፋይዛባድ ከተማ የተጀመረው የመልሶ ግንባታ ቡድን መሪ ኡርባኽ ሚያዝያ 2002 ዓም ሶስት ወታደሮቻቸው በአንድ አደገኛ ስራ ላይ እንዳሉ ህይወታቸው አልፋለች። ኡርባኽ የሟቾቹን ቤተሰብ ስለልጆቻቸው ሞት ማሳወቅ እና በዚሁ አዳጋች ጊዜ ከቤተሰቡ ጎን የመቆም ኃላፊነታቸውን ቢወጡም፡ ከቡድናቸው አባላት አእዱን ማጣት ምን ያህል ከባድ መሆኑን ያስታውሳሉ።
ወታደሮቹ በተከተሉት ዓመታት የተደቀነባቸውን ስጋት ምን ያህል ከፍ ያለ መሆኑን ኡርባኽ በቅርብ ነበር የተከታተሉት። በ 1994 ዓም ተልዕኮዋችንን ስንጀምር የጸጥታው ሁኔታ የተረጋጋ እና አስተማማኝ ነበር። ቀስ በቀስ ግን፡ ሁኔታዎች እየተቀየሩና አደገኛ እየሆኑ መምጣታቸውን መገንዘባቸውን ገልጸዋል። የመስከረም አንድ፡ 1994 ዓም ጥቃት የሚያስታውሱ ዓይነት ጥቃቶች በየጊዜው ተከስተዋል።

የእስልምና ገጽታ

በ 2010 ዓም ዩኤስ አሜሪካ ውስጥ ቅዱሱ መጽሀፍ ቆርአን በይፋ በተቃጠለበት ጊዜ ፋዛባድ በሚገኘው የጀርመናውያኑ ሰፈር ደጃፍ የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጎ፡ ጀርመናውያኑ ወታደሮች በድእጊያ ናዳ እንደወረደባቸው እና የተቃዋሚዎቹን ቁጣ እንዲያበርድ የተላከው የአፍጋኒስታን ፖሊስ ኃይል የማስጠንቀቂያ ተኩስ ከፍቶ እንደነበር ኡርባኽ ዛሬም ያስታውሳሉ። ኡርባኽ ነገሮችን ለማብረድ ከተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ጋ ባደረጉት ውይይት ላይ የተሳተፉት ተወካዮች የመስከረም አእድ ጥቃት የጣሉትን ሰዎች እንዳስታወሱዋቸው፡ ማለትም፡ ሁሉም በተመሳሳይ የእድሜ ክልል የሚገኙ፡ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸውና ግትር እና ማድመጥ የማይፈልጉ አክራሪ ጽንፈኞች እንደነበሩ አስታውቀዋል።
በፖለቲካ አስተሳሰብ የታነጹት ኡርባኽ ከረጅሙ የአፍጋኒስታን ተሞክሮዋቸው የተማሩት ነገር ቢኖር የተቀመጠ ዓላማ ሁሉ ግቡን ይመታል ብሎ መጠበቅ እንደማይቻል ማወቅን ነው። ይህ የዓለም አቀፉ የሂንዱኩሽ የጦር ተልዕኮ ዓላማን ይመለከታል። በ 1994 ዓም መጀመሪያ ላይ ይዘነው የተነሳነው ዓላማ የሰብዓዊ እና የሴቶች የእኩልነት መብት የሚከበርባት ዴሞክራሲያዊት አፍጋኒስታን የምትመሰረትበትን ዓላማ ገሀድ ለማድረግ መርዳት የሚሰኝ ነበር። ግን ካገኙት ተሞክሮ እንደሚታየው ከዚሁ ዓላማችን መሰናበት እንዳለብን ነው። ያም ሆኖ የአፍጋኒስታን ህዝብ በቅርብ ጊዜ የራሱን ጸጥታ ራሱ ማስጠበቅ እንደሚችል ኮሎኔል ኡርባኽ ያምናሉ። የመስከረም አንድ 1994 ዓም ዓይነት አሸባሪዎች በአፍጋኒስታን መንቀሳቀሻ ቦታ እንደያገኙ ማድረግ ከቻልን ያኔ ከአፍጋኒስታን ቀስ በቀስ ለቀን ልንወጣ እንችላለን።

ዳንየል ሸሸኬቪትስ

አርያም ተክሌ