1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ፤ የአውሮፓ ሕብረት የንግድ መሰናክሎችና ዕድገቷ

ረቡዕ፣ ሰኔ 13 1999

የዓለም ንግድ ደምቦች መለዘብ ድሕነትን ለመታገል አንዱ ፍቱን መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል ብዙ ቢነገርም አሁንም ሰፍኖ የቀጠለው የዚህ ተጻራሪ ነው። እርግጥ የደቡቡን ዓለም ገበሬ ሕይወት ያከበደው የበለጸጉት መንግሥታት የእርሻ ድጎማ የፉክክር አቅሙን ማዳከሙ ብቻ አይደለም። ሌሎች ከባድ ተጽዕኖ የሚኖራችው ስውር መሰናክሎችም አሉ። ከነዚህም አንዱ በፔሩ እንደሚታየው የአውሮፓ ሕብረት በታዳጊ አገሮች ላይ የጫነው የምግብ ምርቶች ንግድ መርህ ነው።

https://p.dw.com/p/E0cq
ምስል Geraldo Hoffmann

የዓለምአቀፉ ነጻ ንግድ መስፋፋት ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረገው ትግል አንዱ ጠቃሚ መሣሪያ ሊሆን መቻሉ ብዙ የሚነገርለት ጉዳይ ነው። ግን ሃቁ በተለይ የዚሁ ድህነት ሰለባ የሆነው የታዳጊው ዓለም ገበሬ ብቁ ተፎካካሪ ሆኖ ምርቱን በነጻ ገበዮች ላይ በመሸጥ እንዳይጠቀም ግልጽና ስውር በሆኑ መሰናክሎች መወጠሩ ነው። ታዳጊዎቹ አገሮች የነጻውን ንግድ መሠረተ-ዓላማ ተቀብለው ገቢር እንዲያደርጉ የሚገፋፉት አውሮፓውያንና መሰል የበለጸጉ መንግሥታት የራሳቸውን የድጎማ ፖሊሲና ሌሎች መሰናክሎች ለማንሣት ብዙም ቅን ሆነው አይገኙም። የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር ዙር ንግግሮች ይህን በተደጋጋሚ አጉልተው አሣይተዋል።

እንደ ዕውነቱ ከሆነ የደቡቡ ዓለም ታዳጊ ሃገራት ለረሃብ፣ ለድህነትና ኋላ ቀርነት መጋለጣችው በደፈናው ሃብታም የሚያሰኛቸው የተፈጥሮ ጸጋ ወይም ሃብት አጥተው አይደለም። በውስጥ አስፈላጊው የልማት ይዞታ ጎድሎ፤ ከውጭም የዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ሥርዓት ተጽዕኖ አንቆ ይዟቸው እንጂ! እንደምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ድሃ ከሚባሉት፤ ሆኖም ግን በተፈጥሮ ጸጋ የካበቱ ከሆኑት የታዳጊው ዓለም አገሮች አንዷ ላቲን አሜሪካይቱ ፔሩ ናት። ለዚህ ቅራኔ የተዋሃደው ለሚመስለው የማጣትና ያለማጣት ባህርይ ዋናው ምክንያት የአገሪቱን ሃብት፣ ይሄው የሚሰጠውን ዕድል፤ ትምሕርት፣ ጤና ጥበቃና የኤኮኖሚ ሕይወት ብዙሃኑ ተካፋይ እንዳይሆኑ ያገለለ እጅግ የጠነከረ ብሄራዊ ሃብትን እኩል የማከፋፈል ሁኔታ መጓደሉ ነው።

የፔሩ ሃብት አገሪቱ ከአማዞን ሸለቆ አካባቢ በምታገኘው ነዳጅ ዘይት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ዓይነቱ እጅግ በርካታ የሆነው የተክሎች ጸጋዋም የመካበት ምልክቷ ነው። ግን ይህን ሁል-አቀፍ የተክል ሃብት ለኤኮኖሚ ዕድገቷ ልትጠቀምበት አልቻለችም። ምክንያቱ ደግሞ ሁል ጊዜ ቤት-በቀል፤ ውስጥዊ ብቻ አይደለም። ከችግሩ አንዱ ቀደም ሲል በፕሮግራማችን መግቢያ ላይ የጠቀስነው የአውሮፓ ሕብረት በታዳጊ አገሮች አንጻር ከአሥር ዓመታት በፊት ያሰፈነው የምግም ምርቶች ቁጥጥር ደምብ ነው። በፔሩ የጀርመን ቴክኒካዊ ተራድኦ ድርጅት የ GTZ የገጠር አካባቢ ልማት ተጠሪ ኡልሪሽ ሩትገር ደምቡ ያሳደረውን ተጽዕኖ በቅርብ ከሚያውቁት መካከል አንዱ ናቸው።

በርሳቸው አነጋገር “የሕብረቱ የምግብ ምርቶች መቆጣጠሪያ ደምብ በአንድ በኩል በጂን የተመረቱ ተክሎች ገበዮቹ እንዳይገቡ አድርጓል። ግን ደምቡ ጎጂ ገጽታም አለው። በሰፈነበት ወቅት በጂን የተለወጡ ተክሎችንና አዳዲስ ምርቶችን ለያይቶ መመልከት የሚቻል አልነበረም። ሩትገርስ ፔሩ ውስጥ ለጀርመኑ ቴክኒካዊ ተራድኦ ድርጅት ሲሰሩ አርባ ዓመታት ያሳለፉ ሲሆን የሚሉትን በሚገባ ያውቃሉ። የአገሪቱን የእርሻ ምርቶች የማንጎ፣ የቡና፣ የኮኮ ልማትና የገበያ አቅርቦት በተሣካ ሁኔታ ሲያራምዱ ቆይተዋል። ባለሙያው እንደሚሉት በዓለም ኤኮኖሚ ትስስር በግሎባላይዜሺን ሳቢያ የፔሩ የእርሻ ምርቶች በውጩ ንግድ ይበልጥ ተፈላጊ እየሆኑ መሄዳቸው አልቀረም። ይህም የምርቱን መጠን ከፍ ማድረግ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።

በመሆኑም “በጉዳዩ ውይይት ውስጥ በመግባት ፔሩ ከምትለግሣቸው በርካታ ምርቶች ዝርዝር ውስጥ አምሥቱን መረጥን። እነዚህ ምርቶች በጀርመንና መሰል አገሮች ብዙም የማይታወቁ ናቸው። ካሙ-ካሙ፣ ሣቻ-ኢንቺ፣ ታራ፣ ያኮንና ማካ ይባላሉ። በቆላም በደጋ አካቢዎች የሚበቅሉ ናቸው። ምርቶቹ በውስጥና በዓለምአቀፍ ገበዮችም ተቀባይነት የማግኘት ዕድል አላቸው” ሲሉ አስርተዋል። ሃሣቡ ግሩም ነበር። ገቢር ማድረጉ ግን ከባድና የማይቻል መሆኑን ለመለየት ብዙ ጊዜ አይወስድም። ምክንያቱም እነዚህ ፍራፍሬዎች’ በአውሮፓ የምግብ ቁጥጥር ደምብ ሥር በመሆናቸው በቀላሉ ወደ ሕብረቱ ገበዮች ሊገቡ አለመቻላቸው ነው። በአውሮፓ የዕርሻ ምርት ቁጥጥር መርህ መሠረት እስከ 1997 ዓ.ም. በገበዮቹ ያልዋሉ አዳዲስ የምግብ ምርቶች የሕብረቱን ፈቃድ ለማግኘት ረጅም ጊዜ ማለፍ ይኖርባቸዋል።

ለምሳሌ ያህል ምርቶቹ በረጅም ጊዜ በሰው ላይ መራዥነት እንዳላቸው ለመለየት የቶክሢኮሎጂ ምርመራ መካሄዱ መሟላት ያለበት ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ በያንዳንዱ ምርት ከ 250 እስከ 500 ሺህ ኤውሮ ወጪን ይጠይቃል። በኡልሪሽ ሩትገር አባባል በአጠቃላይ ምርቱ በአውሮፓ ገበዮች እንዲሸጥ ፈቃድ ያገኝ ዘንድ ምርመራው እስከ አንድ ሚሊዮን ኤውሮ የሚጠይቅ ነው። የአውሮፓ ሕብረት አዳዲሶቹን የፔሩ ፍራፍሬ ምርቶች ለማስገባት ፈቃደኛ ባለመሆኑ አገሪቱ ባለፉት አምሥት ዓመታት 110 ሚሊዮን ኤውሮ ማጣቱ ግድ ሆኖባታል። በሌላ በኩል የፔሩ ሕዝብ እነዚህን ምርቶች ለአያሌ ዘመን ሲጠቀምባቸውና ሲመገባቸው ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል የዘይት ይዘት ያለው ተክል ሣቻ-ኢንቺ በአውሮፓ ገበዮች በሰፊው የመሸጥ ጥሩ ዕድል ባገኘ ነበር።

የተክሉ ፍሬዎች ከፍተኛ ጥራት ያለው ዘይት አላቸው። የአሣ ዘይትን ያህል፤ እዚህ በየመድሃኒት ቤቱ እንደሚገኘው ሁሉ፤ ብዙ ኦሜጋ-3 ቅባትን የያዙ ናቸው። በሰውነት ውስጥ የኮሌስተሪን መጠንን ለመቀነስ ሊጠቅሙም ይችላሉ። ሌላው እንዲሁ ከአማዞን አካባቢ የሚገኘው ፍሬ ካሙ-ካሙ ወደ ጃፓንና ወደ ቻይና በሰፊው ይሸጣል። የአውሮፓ ተጠቃሚዎች ግን ይህን ግሩም ጣዕምና ከሁሉም በላይ ደግሞ በቪታሚን ሢ. የካበተውን ፍራፍሬ ለጊዜው ለመቅመስ አልቻሉም። ሆኖም ሩትገርስ “እነዚህ ምርቶች በጣም እንደሚፈለጉ በንግድ ትዕይንቶች ላይ አረጋግጠናል። ግን ገና ለገበያ ልናቀርባቸው አንችልም። አስገቢ ነጋዴዎችም እነዚህ ተክሎች በአውሮፓው የምርቶች ቁጥጥር ደምብ ባለመደገፋቸው ንግዱን መተዉን ነው የሚመርጡት” ሲሉ አስረድተዋል።

የሆነው ሆኖ ፔሩ፣ ቦሊቪያ፣ ኤኩዋዶርና ኮሉምቢያ በ GTZ አማካይነት የአውሮፓ ሕብረት ደምቡን በአዲስ መልክ እንዲያቀናጅ ጠይቀዋል። የዘልማድ አጠቃቀማቸው ዕውቅና ምርቱ በአውሮፓው ሕብረት ገበዮች ይፈቀድ-አይፈቀድ ለሚደረገው ውሣኔ መሠረት ሊሆን ይገባዋል ባይ ናቸው። እስካሁን የተጠቀሱት የፔሩ አዳድስ ምርቶች ለጊዜው ገና ብዙም ገንዘብ አያስገኙም። በተናጠል ሲታይ በያመቱ ቢበዛ ግማሽ ሚሊዮን ዶላርና ከዚያም ያነሰ ገቢ ቢገኝ ነው። በመሆኑም ወደ አውሮፓው ገበያ መዝለቅ መቻሉ በነዚህ መርቶች የወደፊት ዕጣ ላይ ወሣኝ ሚና ይኖረዋል። በታዳጊ አገሮች አዳዲስ ምርቶችን ማዳበሩና ለዓለም ገበያ ተቀባይነት ማብቃቱ በረጅም ጊዜ ድህነትን በመታገሉ ረገድ ጠቃሚ መሣሪያነት ይኖረዋል። ገበዮቹ ካልተከፈቱ ግን የልማት ዕርዳታ በአንድ አቅጣጫ የሚያመራ ጎዳና ሆኖ ነው የሚቀጥለው። በአንዳንድ ሁኔታዎችም መውጫ ቀዳዳ ሊያሳጣ ይችላል።

በአፍሪቃ የልማት ችግሮች ላይ ያተኮረው 17ኛው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ ባለፈው ሣምንት የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚደንት ታቦ እምቤኪ የሥልጣን መሰሎቻቸው ለበለጠ የአካባቢ ትስስር እንዲጥሩ ባደረጉት ጥሪ ተከናውኗል። በወቅቱ በአማካይ 5 ከመቶ ገደማ ዓመታዊ ዕድገት የሚታይባት አፍሪቃ በብዙዎች አፍ በወደፊት ዕርምጃ ላይ ነው የምትገኘው። የአፍሪቃ የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ሊቀ-መንበር ሃይኮ አልፍሬድ እንደሚሉት ሂደቱ ወደፊት በመቀጠሉና ሕዝቡ በቅርብ ጊዜ ከዕርምጃው ተጠቃሚ በመሆኑ ረገድ ግን መሰናክሎቹ ብዙዎች ናቸው።“በቅድሚያ የአስተዳደር ዘይቤን መጥቀስ ይቻላል። ይህም ተጽዕኖው ብዙ ነው። ደካማ ተቋማት፣ መጥፎ መርህና የአወሳሰን ድክመት! ምንም እንኳ አፍሪቃን እንደዛሬው ሰላማዊ ሆና አይተን ባናውቅም ውዝግቦችና ጦርነት አሁንም ዓቢይ ሚና አላቸው። ሌሎቹ ዕድገትን አንቀው የያዙት ችግሮች ደግሞ የመዋቅርና የአካባቢ ትስስር ጉድለቶች ናቸው”

ይህም ሆኖ የአካባቢው ትብብር ደጋፊ ፕሬዚደንት ታቦ እምቤኪ አፍሪቃ ሃሣቡን ገቢር ልታደርግ እንደምትችል አይጠራጠሩም። ለነገሩ ከአሁኑ የቀረጥ ነጻነትን፣ የግብር ማቃለያና አንድ ወጥ ደምቦችን የሚከተሉ የአካባቢ ማሕበራት አሉ። ግን እነዚሁ የደቡባዊው አፍሪቃ የልማት ማሕበር SADC ኮሜሣና ኤኮዋስ የሚገባውን ያህል ፍቱንነት አላቸው ለማለት አይቻልም። ለማንኛውም አፍሪቃ ወደፊት የዕድገትና የመዋዕለ-ነዋይ መስፋፋት ዕድል በመፍጠር የምርት ማራገፊያ ብቻ ሣይሆን የውጭ ንግድ ምርት የሚመረትባቸው ፋብሪካዎች መሥፈሪም ልትሆን እንደምትችል የብዙዎች ኩባንያዎች ዕምነት ነው። እርግጥ ይህ እንዲሆን ቀደም ሲል የተጠቀሱት መሰናክሎች መነሣት ይኖርባቸዋል። ከሆነ ተጠቃሚዎቹ በክፍለ-ዓለሚቱ የተፈጥሮ ሃብት ላይ ያተኮሩት የበለጸጉ መንግሥታት ብቻ ሣይሆን በከፋ ድህነት የሚኖሩት 250 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጉት አፍሪቃውያን ጭምር ናቸው።