1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ መጪዋ ነብር?

ረቡዕ፣ መስከረም 9 2005

የአፍሪቃ ኤኮኖሚ እያበበ በመሄድ ላይ መሆኑ በየጊዜው ሲነገር የቆየ ጉዳይ ነው። ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙት ሃገራት ኤኮኖሚ በያመቱ ከአምሥት በመቶ በላይ ዕድገት እያሳየ መሆኑን የአፍሪቃ ልማት ባንክ ያመለክታል።

https://p.dw.com/p/16B5G
ምስል picture-alliance/dpa

የአፍሪቃ ኤኮኖሚ እያበበ በመሄድ ላይ መሆኑ በየጊዜው ሲነገር የቆየ ጉዳይ ነው። ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙት ሃገራት ኤኮኖሚ በያመቱ ከአምሥት በመቶ በላይ ዕድገት እያሳየ መሆኑን የአፍሪቃ ልማት ባንክ ያመለክታል። እንደ እህጉራዊው የልማት ባንክ ከሆነ ዕድገቱ በመጪዎቹ ዓመታትም ቀጣይነት የሚኖረው ነው። የባንኩ አስተዳዳሪ እምቱሊ እንኩቤ እንደሚሉት ሌላው ቀርቶ ደካሞቹ የአፍሪቃ ሃገራት እንኳ ከአውሮፓ ሲነጻጸር የጠነከረ ዕድገት ማድረጋቸው ነው የሚጠበቀው። ተያይዞ እንደተጠቀሰው ከሆነ በዚህ ዓመት ለምሳሌ ዕድገት የማያስመዘግብ አንድም የአፍሪቃ አገር አይኖርም።

ይሁን እንጂ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ንብረትን አፍሪቃ ውስጥ በስራ ላይ በማዋሉ ረገድ አሁንም ቁጥብነት ማሳየታቸውን አልተውም። ለዚህም ምክንያቱ እንደተለመደው የአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት የፖለቲካ ሁኔታ የተረጋጋ አለመሆንና የመዋቅራዊው ይዞታ ኋላ ቀርነት ነው። በዚህ በጀርመን የበርሊኑ የሕዝብና የልማት ኢንስቲቲዩት ያለውንና የጎደለውን አጣምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪቃን ዕድገት የመረመረ ጥናት ወጤት ሰሞኑን አቅርቧል።

የተመራማሪዎቹ ዓላማ የአፍሪቃ ክፍል-ዓለም በእርግጥ ያላትን የዕድገት ብቃት ወይም አቅም ማጤን ሲሆን ጥናቱ እንዲካሄድ ያደረገው የጀርመን የፍጆት ምርምር ተቋም ነበር። ጥናቱ በ 50 የአፍሪቃ ሃገራት የኤኮኖሚ ይዞታ፣ የአስተዳደር ሕጋዊነት፣ የሕዝብ ዕድገትና በአጠቃላዩ የኖሮ ሁኔታ ላይ አተኩሯል። ለመሆኑ ጥናቱ ለምን በዚህ መልክ እንዲካሄድ ተፈለገ? የፍጆት ምርምሩ ተቋም ባልደረባ የኤኮኖሚው ባለሙያ ፕሮፌሰር ዶክተር ራይሙንድ ቪልድነር እንዲህ ይላሉ።

«ስለነዚህ ሃገራት እስካሁን ያለው መረጃ በጣሙን ትንሽ ነው። አፍሪቃ ደግሞ በማደግ ላይ ያለችው የመጨረሻዋ ክፍለ-ዓለም ናት። የዕድገቷን መጠን ከተመለከቱ አፍሪቃ መጪዋ ነብር መሆኗን ለመለየት ብዙም አያዳግትም»

አፍሪቃ እንግዲህ አንዴ በእሢያ ሃገራት እንደታየው ዛሬ መጪዋ ነብር ወይም በተፋጠነ ዕድገት ወደፊት የምታመራ ክፍለ-ዓለም መሆኗ ነው። የበርሊኑ የሕዝብና የልማት ምርምር ኢንስቲቲዩት በአዲስ ጥናቱ የደረሰበት ተሥፋ ሰጭ ውጤት እንግዲህ ይህን ይመስላል። ሆኖም ግን የምርምሩ ውጤት በሌላ በኩል አፍሪቃን በሕዝብ ቁጥር መናርና በድህነት በሚያውቀው በዚህ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸገው ዓለም ሕብረተሰብ ዘንድ ጥርጣሬን የሚፈጥር ነው።

Angola Bairro Rocha Pinto - Armenviertel in Luanda
ምስል DW

የከተሞች ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ መጨናነቅ፣ በድህነት የሚማቅቅና ዕለት ከዕለት ለሕልውናው የሚታገል የትላልቅ ቤተሰብ መበራከት ነው ከዓይኑ ላይ የሚደቀነው። ይሁንና የበርሊኑ ኢንስቲቲዩት እንደሚለው በጥናቱ ገንቢውንና ጎጂውን ለያይቶ ለማጤን ተሞክሯል። ከጥናቱ አጠናቃሪዎች አንዱ ራይነር ክሊንግሆልትስ ለአንድ አገር ልማት ይበልጥ ወሣኙ ነገር በሕዝቡ ይዞታ ላይ፤ ለምሳሌ በወጣትና አንጋፋው ግንኙነት መጠን ወይም ድርሻ ላይ የሚኖረው ለውጥ እንደሆነ ነው የሚያስገነዝቡት።

«በአንድ ብዛቱ እየጨመረ በሚሄድ ሕዝብ ዘንድ ከያንዳንዷ ሴት በነፍስ-ወከፍ የሚወለደው ሕጻን ቁጥር በሚቀንስበት ጊዜ ለሥራ ብቁ የሆነው ሕዝብ ቁጥር ደግሞ ያድጋል። በሕጻናቱ ቁጥር ማቆልቆል በራሱ በቻ ብሄራዊው አጠቃላይ ምርት በነፍስ-ወከፍ ይጨምራል ማለት ነው። እናም አሁን እንግዲህ ቁጥሩ ከፍተኛ ለሆነው ለሥራ ብቁ የሆነ ሕዝብ የሙያ ዕድል መፍጠር ከተቻለ የአፍሪቃ ሃገራት ግሩም ዕድገት እንደሚያደርጉ ግልጽ ነው»

ይህ በተለይ ሞሪሺየስን፣ ደቡብ አፍሪቃንና አንዳንድ የሰሜን አፍሪቃ ሃገራትን ይመለከታል። ሰርቶ ለማደር የሚችለው ሕዝብ መጨመር ደግሞ ብዙ ፍጆትንም የሚያስከትል ነው። የበርሊኑ ኢንስቲቲዩት ሃላፊ ራይነር ክሊንግሆልትስ እንደሚያመለክቱት በወቅቱ በብዙ የአፍሪቃ ሃገራት መካከለኛ የሕብረተሰብ መደብ እየተተስፋፋ ሲሄድ ነው የሚታየው። እነዚህ ደግሞ ዛሬ የተለያዩ ምርቶች መግዛት ይችላሉ። እርግጥ ለጊዜው ውድ የሚሆኑባቸው ነገሮች አይታጡም። ነገር ግን ለሕልውና ከመፍጨርጨር በላይ ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚበቁ ናቸው።

«በጣም እያደገ ስለሚሄድ መደብ ነው የምናወራው። የማጽጃ ዕቃዎችን፣ ባትሪዎችን፣ ሞባይል ስልኮችንና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የምግብ ምርቶች መግዛት ስለሚችል!ለጊዜው ምናልባት ውድ የቤት ዕቃዎችንና አውቶሞቢሎችን መግዛቱ ሊከብድ ይችላል። ሆኖም ግን ወደ ፍጆት ሕብረተሰብነት የመለወጥ የመጀመሪያ ዕርምጃ እየታየ ነው። የፍጆቱን ዕቃዎች በተቻለ መጠን በአገር የማምረቱ ፍላጎትም ከፍ እያለ ይገኛል»

የጀርመን ኤኮኖሚ ዘርፍ የአፍሪቃ ማሕበር ባልደረባ ሚሻኤል ሞነርያህንም አፍሪቃ ታላቅ የምጣኔ-ሐብት ምንጭ እንዳላት ነው የሚናገሩት። ይህ ደግሞ ከጀርመን ኩባንያዎች ጥቅም አንጻርም ማራኪነት አለው። ምክንያቱም ወደፊት ቴክኒክ-ነክ ዕቃዎችና አገልግሎቶች እያደገ ለሚሄደው ሕዝብ ይበልጥ አስፈላጊ እየሆኑ እንደሚሄዱ ግልጽ ነው።

«በተለይ በባንኩ ዘርፍ ወይም በቴሌኮሙኒኬሽን ረግድ ከ15 ዓመታት በፊት ጨርሶ ሊታሰብ ይችል ያልነበረ ትልቅ ዕድገት ነው የተደረገው። የሞባይል ባንክ አገልግሎትን የመሳሰሉ አዳዲስ አገልግሎቶች እየተፈጠሩ ነው። ኬንያ ለምሳሌ በዚህ በኩል በዓለምአቀፍ ደረጃ ቀደምቷ ናት»

Armut in Mosambik
ምስል Romeu da Silva

የጀርመኑ የሕዝብና የልማት ምርምር ኢንስቲቲዩት ወደፊት በዚህ ዘርፍ የተሻለ የዕድገት ዕድል ከሚሰጣቸው መካከል አሥር የጠረፍ ሃገራትን ዘርዝሯል። እነዚህም ደቡብ አፍሪቃና ናሚቢያ በደቡባዊው አፍሪቃ፤ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያና ግብጽ በሰሜን አፍሪቃ፤ ከዚያም ሤኔጋል፣ ጋምቢያ፣ ጋና፣ ጋቡንና ሞሪሺየስ ናቸው። ዝርዝሩ በልምድ ታላቅ የዕድገት ዕድል የሚሰጣቸውን ናይጄሪያንና ኬንያን አለመጠቅለሉ ምናልባት ብዙዎችን ሳያስደንቅ አይቀርም።

ምክንያቱ የጥናቱ ተቋም መሪ ራይነር ክሊንግሆልትስ እንደሚሉት የፖለቲካ መረጋጋት እጦትና መጥፎ የኑሮ ሁኔታ ነው። ኬንያ እየጨመረ ለሚሄድ ሕዝቧ አስፈላጊውን ምግብና መድሃኒቶች ማቅረብ ሲሳናት በናይጄሪያ ደግሞ ከነዳጅ ዘይት የሚገኘው ገቢ አሁንም ከጥቂት ሰዎች ዕጅ አልወጣም። በመሠረቱ በናይጄሪያ በፍጥነት እያደገ የሚሄደው የሕዝብ ቁጥርና ተስፋፊው ኤኮኖሚ የውጭ ኩባንያዎችን ይበልጥ እየሳበ መሄዱ አልቀረም። ጥያቄው ሕዝብ ምን ጥቅም አገኘ ነው።

ለምሳሌ ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ከምታደርገው ንግድ አሥር በመቶውን ድርሻ የምትይዘው ናይጄሪያ ናት። የሕዝብ ቁጥሯ ከአሁኑ ከ 150 ሚሊዮን በላይ የሆነው አገር ደቡብ አፍሪቃን በክፍለ-ዓለሚቱ በኤኮኖሚ ጥንካሬ የመተካት ትልቅ ዕድል ነው ያላት። እርግጥ የፖለቲካው አለመረጋጋት ባይኖር!

በበርሊኑ የሕዝብና የልማት ጥናት ኢንስቲቲዩት ምርመራ እንደተጠቀሰውዴሞክራሲና በጎ አስተዳደርም ለዕድገት ያላቸው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው። የበለጸገው ዓለምም ዴሞክራሲ ከሰፈነባቸው አገሮች ጋር መሥራቱ ይቀለዋል። የሕግ የበላይነት የሰፈነበት የአስተዳደር ስርዓትና ዴሞክራሲ እንግዲህ ጥሩ ለሆነ የንግድ ግንኙነት ወሣኝ ቅድመ-ግዴታዎች ይሆናሉ ማለት ነው።

በሞነርያህን አባባል በፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የተያዙ መንግሥታት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ለጀርመን የኤኮኖሚ ዘርፍ የተረጋጉና አስተማማኝ ሆነው ቆይተዋል። ይህ ለምሳሌ ሞአማር ጋዳፊ በሚገዟት በሊቢያ የታየ ሃቅ ነበር። ከሁለት ወይም ሶሥት ዓመታት በፊት ቢጠየቅ የጋዳፊ ቤተሰብ ከሥልጣን ይወገዳል በሎ ያሰበ አንድም ታዛቢ ባልተገኘ ነበር። ግን ጋዳፊም ለረጅም ጊዜ የእርጋታ ዋስትና መስለው መቀጠሉን አልቻሉም። እናም ለዘለቄታው የሚያዋጣው በጠንካራ ክንድ ጸጥ አሰኝቶ አገዛዝን ማራመድ ሣይሆን ግልጽነትን፣ የሕግ የበላይነትንና ዴሞክራሲን ማስፈን ነው።

ከዚህ አንጻር አፍሪቃ ውስጥ በእጣት ከሚቆጠሩ ሃገራት አልፎ በአብዛኞቹ የረባ ዕርምጃ ተደርጓል ለማለት አይቻልም። አፍሪቃ ከቅኝ አገዛዙ ዘመን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት አደረገች በተባለበት ባለፈው አሠርተ-ዓመት በርካታ ምርጫዎች ሲካሄዱ አብዛኞቹ ከማስመሰል ያለፉ አልነበሩም። የገዢዎችን የሥልጣን ዘመን በአዲስ መልክ ለማራዘምና ሕጋዊ ልባስ ለመስጠት ካልሆነ በስተቀር ለዴሞክራሲ ማበብ ያበረከቱት አንዳች አስተዋጽኦ የለም።

ባለፉት ዓመታት እጅግ የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ማድረጓ በሚነገርላት በኢትዮጵያም ቢሆን የዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ጥያቄ አከራካሪ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው። አፍሪቃ በልማት ረገድ ዕውነትም መጪዋ ነብር እንድትሆን ከተፈለገ ሙስና፣ የዜጎች መብት ረገጣና አምባገነን የአገዛዝ ዘይቤ ሊወገድ ይገባል። ይህ ካልተሣካ የክፍለ-ዓለሚቱን የምጣኔ-ሃብት ምንጭ ተጠቅሞ ማሕበራዊ ልማትን ወደፊት ማራመዱ፤ እንዲያም ሲል ሕዝቡን ከድህነትና ከረሃብ ማላቀቁ የማይቻል ነገር ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ