1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃና የ 2007 የኤኮኖሚ ዕድገቱ ትንበያ፧

ማክሰኞ፣ መጋቢት 25 1999

የአፍሪቃ ኤኮኖሚ፧ በያዝነው 2007 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ድኅነትን ለመቀነስ እንዲያበቃው፧ የተጠበቀውን 7% ሳይሆን 5.8% ዕድገት የሚያሳይ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪቃ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን ያቀረበው የጥናት ውጤት አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/E0d1
በ አ.አ. የሚገኘው፧ የአፍሪቃ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጽ/ቤት፧
በ አ.አ. የሚገኘው፧ የአፍሪቃ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጽ/ቤት፧ምስል picture-alliance/ dpa
ኮሚሽኑ፧ በነዳጅ ዘይት ዋጋ መናርና በዕቃ ዋጋ ግሸበት ሳቢያ የሚደርሰውን የዕድገት ሳንክ ለመቋቋም፧ አፍሪቃውያን በሰፊው በተለያየ የኤኮኖሚ ዘርፍ እንዲያተኩሩም ማሳሰቢያ አቅርቧል። አፍሪቃ ስለሚገኝበት የኤኮኖሚ ደረጃ ስለሚጠበቀው እድገት፧ ስለ አኅጉራዊና ዓለም ዓቀፍ ትብብሮች ያወሱትን ከጥናቱ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑትን፧ Leonce Ndikumana ን፧ ተክሌ የኋላ፧ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የኮሚሽኑ ዋና ጽህፈት ስልክ በመደወል አነጋግሮአቸዋል።
«በአዲስ አበባ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪቃ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን፧ ካሉት የሥራ ኀላፊነቶች መካከል አንዱ፧ በያመቱ በክፍለ-ዓለሙ የሚደረገውን የኤኮኖሚ እንቅሥቃሴና የሥራ ውጤት በአካባቢያዊና በሀገራዊ ደረጃ መለስተኛ የኤኮኖሚ እንቅሥቃሴዎችን እንዲሁም ማኅበራዊ ኑሮ ዕድገትን አጥንቶ ማቅረብ ነው።«
ልማት እንዲስፋፋ ኤኮኖሚ እንዲያድግ-እንዲመነደግ በቅድሚያ በዛ ላሉ ደንቃራዎች መፍትኄ መሻት ያስፈልጋል። የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ኮሚሽን ዘንድሮ የ 5.8 ከመቶ ዕድገት ይገኛል ሲል ከምን ጥናት በመነሣት ነው? Leonce Ndikumana.....
«ለ 2007 የጥንቱ ውጤትም ሆነ ዘገባው፧ በግምት እንደሚገልጸው፧ የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ባጠቃላይ የ 5.8 ከመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት ያሳያል ተብሎ ይጠበቅበታል። ይህም፧ ባለፈው 2006 ዓ. ም፧ ከተገኘው አመርቂ ውጤት ትንሽ ላቅ ያለ መሆኑ ነው። ይህ ጥሩ ዜና ነው። ይህ የጥናት አኀዝ የተገኘው፧ የተለያዩ ተቋማትን ተከታታይ የምርምር ምንጭ፧ የራሳችንን የ ECA ን ጥናት፧ የአፍሪቃ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን አካባቢያዊ ተቋማት እንዲሁም፧ ከአፍሪቃ ውጭ የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት፧ የዓለምን ባንክ፧ የኤኮኖሚ ዕድገት ፈታሽ ቡድን፧ እንዲሁም የ OECD ምንጮችን መጥቀስ ይቻላል። በመሠረቱ፧ የሁሉንም ተቋማት ምንጮች በመመርመር ነው ተገቢ መስሎ ከሚታይ የውጤት መግለጫ ላይ የምንደርሰው።«
አፍሪቃ እ ጎ አ በ 2006- 5.6% -. በ 2005.- 5.3%-. በ 2004 -. 5.2% ዕድገት ማሳየቱ በዘገባው ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፧ ስምንት አገሮች ብቻ ድህነትን መቅረፍ በሚያስችለው የዕድገት መጠን ማለትም ሰባት ከመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት በማስዝገብ ላይ ናቸው በማለት የአፍሪቃ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን አስታውቋል። እነርሱም፧ አንጎላ፧ ሞሪታንያ፧ ሱዳን፧ ኢትዮጵያ፧ ላይቤሪያ፧ ሞዛምቢክና የኮንጎ ሪፓብሊክ ናቸው። አይቮሪኮስት፧ ኮሞሮ፧ እስዋዚላንድ፧ ሲሸልስና ዝምባብዌ፧ አንዳች እመርታ አላሳዩም። ምናልባትም የማሽቆልቆል ዕጣ ሳይገጥማቸው አይቀርም፧..እንደ አፍሪቃ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን ጥናት ውጤት.....። እ ጎ አ በ 1980ኛዎቹ ዓመታት ኤኮኖሚአቸውን የዕድገት ፈር ለማስያዝ፧ በጀትንና የገንዘብን ሸርፍ መጠንን ማስተካከል፧ ወለድና ቀረጥም በመቀነስ፧ ከዚያም ሙስናን ለመታገል መንግሥታዊ የሥራ ዘርፎችን፧ በተቀላጠፈ አሠራር አገልግሎት እንዲሰጡ፧ ጥረት ተደረገ ቢባልም ገና የሚያስመሠግን ውጤት አልተመዘገበም። አፍሪቃውያን ባጠቃላይ እንደ እስያና ላቲን አሜሪካ የዕድገት ጎዳናን ለመያያዝ በመጀመሪያ በክፍለ-ዓለሙ የእርስ በርስ ትብብርን የንግድ ልውውጥንና የመሳሰለውን ማጠናከር ይጠበቅባቸውል። ከዚያም አልፈው፧ በዓሰም አቀፍ ገበያ ጠንክረው ለመፎካከር ማለም ይበጃቸዋል። ግንይህ ሲሆን አይታይም።
«የአፍሪቃ አገሮች፧ ከውጭ የንግድ ተባባሪዎች ጋር በተፈረሙ ውሎች አልተጠቀሙም። ሌላው፧ አፍሪቃውያን መንግሥታት እርስ-በርሳቸው፧ ንግድን በክፍለ ዓለማቸው ማስፋፋቱ ተስኗቸዋል።
ዓለም አቀፍ ንግድን በተመለከተ፧ ከቀሪው ዓለም ጋር እንዲያካሂዱ ሥምምነት ቢኖርም፧ የኤኮኖሚውን ዘርፍ ያላስፋፉ በመሆናቸው አልተጠቀሙም። ለገበያ የሚያቀርቧቸው ተመሳሳይ ምርቶች ናቸው። በዓለም ገበያም ዝቅተኛ ዋጋ ነው የሚሰጣቸው። በድርድርም ቢሆን፧ የአፍሪቃውያኑ ኃይል ደካማ ነው። ሌላው ችግር ደግሞ ስምምነቶች ቢፈረሙም እንኳ፧ በእርግጥ በተግባር የማይተረጎምበት ሁኔታ ነው የተከሠተው።