1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃና አከራካሪው የኤኮኖሚ ዕድገት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 8 2004

የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ዕድገት በአሃዝ አቀራረቡ አሻሚ፤ በማሕበራዊ ልማት አስተዋጽኦ ረገድም አከራካሪ የሆነ ጉዳይ ነው።

https://p.dw.com/p/RrWQ
ምስል DW

የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ዕድገት ይዞታ እሳካለፈው አርብ ድረስ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ተካሂዶ በነበረ አሥር ቀናት የፈጀ የፓን አፍሪቃ ፓርላማ ስብሰባ ላይም አንዱ የውይይት ርዕስ ነበር። የአዲሱ የአፍሪቃ የልማት ሽርክና የኔፓድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢብራሂም ማያኪ በአፍሪቃው ሕብረት ኮሚሢዮን ሊቀ-መንበር በጂያን ፒንግ ስም ባሰሙት ንግግር ባለፉት አሥር ዓመታት በተግባር ላይ የዋሉት የኤኮኖሚ ፖሊሲዎች መዋቅራዊ መሻሻልን እንዳስከተሉና ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ-ነዋይን ለመሳብ አመቺ ሁኔታ እንደፈጠሩ አስረድተዋል። ማያኪ ከዚሁ በማያያዝ እንደገለጹት ዕድገቱ ቀጣይ ሊሆን የቻለውም ስኬታማ የአስተዳደር ዘይቤ በመስፈኑና ሕብረተሰብን ወደ ዴሞክራሲ የማሸጋገር ጥልቅ ዕርምጃ በመደረጉ ነው።

እርግጥ ይህን ሁሉም እንደራሴዎች አልተቀበሉትም። ለምሳሌ ከናሚቢያ ሎይዴ ካሢንጎ ኤኮኖሚው በየቦታው ሊሻሻል ቢችልም ቅሉ ለሕዝብ ግን እንዳልጠቀመ ብዙዎች ተቺዎች የሚያነሱትን ሃቅ ሰንዝረዋል። ካሢንጎ መዋዕለ-ነዋይ የስራ መስኮችን ለመክፈት የሚበጅ እንዲሆን፤ አፍሪቃን ከጥሬ ሃብት ሻጭነት ወደ ኢንዱስትሪ አምራችነት ለማሸጋገር ለውጥ ሊደረግ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። የአፍሪቃ ሕዝብ እንግዲህ በተወሰኑ አገሮች አለ ከሚባለው የኤኮኖሚ ዕድገት ተጠቃሚ ለመሆን እንዲበቃ ገና ብዙ ነገሮች መስተካከላቸው ግድ መሆኑ አልቀረም። በደቡብ አፍሪቃ-በሚድራንድ በተካሄደው የፓን አፍሪቃ ፓርላማ ስብሰባ ላይ የተባለውን መንስዔ በማድረግ በዚያው በኬፕታውን የጀርመን የንግድ ጋዜጣ የሃንደልስ-ብላት ወኪል የሆኑትን ቮልፍጋንግ ድሬክስለርን አነጋግሬ ነበር። የኤኮኖሚው ባለሙያ ባለፉት አሥር ዓመታት በአፍሪቃ እርግጥ አንዳንድ አገሮች ተሥፋ ሰጭ ዕርምጃ ማሳየታቸውን ሲጠቅሱ የሕብረቱን ባለሥልጣናት አባባል ግን በቁጥብነት ነው የሚመለከቱት።

“አንዳንዶቹ ነጥቦች እርግጥ ትክክለኞች ናቸው። አፍሪቃ ውስጥ እንዳለፈው ምዕተ-ዓመት መፈንቅለ-መንግሥት የሚቀጥልበት ጊዜ አይደለም ዛሬ። በአፍሪቃ ብዙ ምርጫዎች ይካሄዳሉ። ግን ይህ ተገቢውን ለውጥ አምጥቷል ወይ? ብሎ መጠየቁም ግድ ነው። እርግጥ በአንዳንድ የአፍሪቃ አገሮች የዴሞክራሲ ዕርምጃ አለ። እንደ ምሳሌ ጋናን መጥቀስ ይቻላል። በቅርቡ የተሳካ ምርጫ የተካሄደባት ናይጄሪያም አለች። አዎን፤ ተሥፋ ሰጭ ነጥቦች አይታጡም። ይሁን እንጂ ባለፉት አሥር ዓመታት ሂደት ታላቅ ስኬት ተገኝቷል የሚለውን አባባል በቁጥብነት ነው የምመለከተው”

በእርግጥም ቮልፍጋንግ ድሬክስለር አያይዘው እንደሚያስረዱት የብዙዎች አገሮች ተጨባጭ ሃቅ ሌላ ነው የሚናገረው።

“በአፍሪቃ ዋና ዋና በሆኑ አገሮች ውስጥ ምን እንደተፈጸመ መለስ ብለን ብናስተውል ለምሳሌ ኬንያ መንግሥት በምርጫ መሸነፉን ባለመቀበሉ የተነሣ ከለየለት የእርስበርስ ጦርነት ለጥቂት ነበር ያመለጠችው። በምዕራብ አፍሪቃይቱ አይቮሪ ኮስት በግባግቦና በኡዋታራ መካከልም የእርስበርስ ጦርነት ጥፋት ለጥቂት ነው የተወገደው። ወደ ዚምባብዌ ወረድ ብንል ደግሞ ሙጋቤ ከሰላሣ ዓመታት በላይ ሥልጣን እንደያዙና አልወርድም እንዳሉ ነው። በአንጎላም ዶሽ ሣንቶሽ በአፍሪቃ ሥልጣን ላይ ለርጅም ጊዜ የተቀመጡት ገዢ ናቸው። እናም አፍሪቃ በአንድ፣ ሁለት ወይም ሶሥት ምርጫዎች የተነሣ በዴሞክራሲ አቅጣጫ እየተራመደች ነው ማለቱ በጣም የተጋነነ ነው የሚሆነው”

ለማንኛውም አንዳንድ የአፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያቸውን ብዙዎች ባለሙያዎች ከሚሉት ከፍ አድርገው ያቀርባሉ። የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ለምሳሌ በአፍሪቃ በሚቀጥለው ዓመት የሚጠብቁት አማካይ ዕድገት ከስድሥት እስከ ሰባት ከመቶ የሚሆን ነው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያን የመሳሰሉ አገሮች ከአሥር በመቶ በላይ ዕድገት ይገኛል ባይ ናቸው። ልዩነቱ እንግዲህ በጣም ሰፊ ነው። የሆነው ሆኖ ቮልፍጋንግ ድሬክስለር በበኩላቸው እንደሚሉት እነዚህ አገሮች ድህነትን ለማስወገድ ለረጅም ጊዜያት ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማሳየታቸው ግድ ነው።

“የግምቱ መቃረን የሚፈጠረው ኤኮኖሚው በአብዛኛው በጥሬ ሃብት አቅርቦት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው። እንዳለፈው ዓመት የነዳጅ ዘይት ወይም የመዳብ ንግድ ጥሪ በሚራመድበት ጊዜ የሚመለከታቸው አገሮች ትልቅ ዕድገት ሊታይባቸው ይችላል። ግን የነዳጅ ወይም የኮኮ ዋጋ ሲያገግም ብቻ የሚገኝ ዕድገት አስተማማኝ ዕድገት አይሆንም። በዚህ ላይ ተመስርቶ ብሄራዊ ኤኮኖሚን ማነጽ አይቻልም። ኤኮኖሚን በአግባብ ለመገንባት ሰዎችን በሙያ ማሰልጠን፣ ሕብረተሰብን በዕውቀት ማዳረስ፤ የትምሕትና የጤና ጥበቃ ተቋማትን ማነጽ ወዘተ. ግድ ነው። የአፍሪቃ አገሮች ደህነትን ለማስወገድ ከ 15 እስከ 20 ዓመታት ያለማቋረጥ ቢያንስ አሥር በመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህ እስካሁን አልነበረም። ቢሆን ግን የኤኮኖሚ ዕድገት በዕውነት መደረጉን ማረጋገጥ በተቻለ”

ቢሳካ ምንኛ ግሩም በሆነ ነበር። ግን አፍሪቃ ውስጥ ዕድገት ሁሌም ዕውነተኛ ዕድገት አይደለም። ልምድ የሚያሳየው እርግጥ በርከት ባሉ አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት በመሠረቱ መታየቱን፤ ሆኖም ግን በበጎ አስተዳደር ጉድለት፣ በዴሞክራሲ እጦትና በሙስና የተነሣ ወደ ማሕበራዊ ዕድገት አለመመንዘሩን ነው። በአብዛኛው ድህነት ሲብስ እንጂ ሲለዝብ አይታይም።

“ትክክል ነው። ቁስሉን በትክክል ነው የነካኸው። ያሳዝናል ዕርምጃው እስካሁን በጣም ትንሽ ነው። አፍሪቃ ዛሬ ደግሞ የተማሩ ሰዎቿን ይበልጥ ማጣት ቀጥላለች። ብዙዎች አሁንም አገር ለቀው ይሄዳሉ። በዚህ የተነሣም ለዕድገት የሚያበቃ መዋቅር በሚገባ ማነጹ ይከብዳል። በወቅቱ እርግጥ ኬንያ ውስጥ መንግሥት ለውጥ ማስፈለጉን ተረድቶ ሁኔታውን ለማሻሻል ጥረት እያደረገ ነው። በሌላ በኩል በደቡብ አፍሪቃ እንደሚታየው ለምሳሌ መንግሥታት በየጊዜው በነጻው የኤኮኖሚ ዘርፍ ላይ የሚፈጥሯቸው ተብታቢ ደምቦችና መሰናክሎች ኩባንያዎችን ማቋቋሙን የሚቻል ነገር አያደርጉትም”

የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ከቤት ሰራሹ መሰናክሎች ባሻገር በመጪዎቹ ዓመታት ሌሎች የአካባቢና የውጭ ግፊቶች ሊገጥሙት እንደሚችሉ ከወዲሁ አንዳንድ ምልክቶች አልታጡም። አውሮፓን በወቅቱ የወጠረው የኤውሮ ቀውስ በአብዛኛው በጥሬ ሃብት ንግድ ጥገኛ በሆነው የአፍሪቃ አገሮች ኤኮኖሚ ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ሊኖረው የሚችል ነው። ይሄው የኤውሮው ችግር መፍትሄ ካጣና ዓለም ጠለቅ ወዳለ የኤኮኖሚ ቀውስ ከተሻገረ መጪው ዓመት ለአፍሪቃ ከባድ የሚሆን ይመስላል። ከዚሁ ሌላ በወቅቱ በአፍሪቃ ቀንድ ላይ የተከሰተው ረሃብ ለዓመታት በአካባቢው የተለመደ ቢሆንም አሁን ከሕዝቡ ቁጥር በሰፊው መናር ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያና በአካባቢው ይበልጥ ፈታኝ መሆኑ አልቀረም። የአካባቢው ሕዝብ በሃያ ዓመታት ውስጥ እጥፍ ሊደርስ ሲቃረብ የቤተሰብ ይዞታ ዕቅድ ገቢር ካልሆነ ዕድገትን ይብስ የሚያከብድ ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ