1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አገር ፍቅር ቤቴ ነዉ» አብራር አብዶ

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 5 2007

ዋና መቀመጫዉን ጀርመን ያደረገዉ «የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኪነ-ጥበብ ማዕከል» ለኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጉዋል ሲል የሸለመዉን አንጋፋዉን አርቲስት አብራር አብዶን ጵጥሮስ ያችን ሰዓት የተሰኘዉን ድራማ በመድረክ ላይ አቅርቦ ተመልካችን አስደምሟል።

https://p.dw.com/p/1GUBk
Frankfurt Ehrung Künstler Äthiopien
የክብር ተሸላሚዉ አርቲስት አብራር አብዶ በፍራንክፈርት ጀርመን መድረክ ላይምስል DW/E. Zamora

«አገር ፍቅር ቤቴ ነዉ» አብራር አብዶ

አርቲስት አብራር አብዶ አገር ፍቅር ትያትርን ከእናቴ ቤት በላይ የኖርኩበት ቤቴ ነዉ ሲል ይገልፀዋል። ቅዳሜ ነሐሴ 30/ 2007 ዓ,ም ጀርመን ፍርናክፈርት ካልክ ሃይም በሚገኝ ሰፊ አደራሽ ዉስጥ በተከናወነዉ የክብር ሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት በኢትዮጵያና አዉሮጳ ነዋሪ የሆኑ በርካታ አርቲስቶችም ተገኝተዉ ነበር።

ከኢትዮጵያ ዝግጅቱ ላይ ለመገኘትና ሙዚቃ በማቅረብ የሚሰበሰበዉ ገንዘብ ለኪነ-ጥበብ ድጋፍ እንዲሆን በማድረግ አስተዋፅዎ ካደረጉት ሙዚቀኞች መካከል አንድዋ ድምፃዊ እመቤት ነጋሲ በማኅበሩ ዓመታዊ ዝግጅት ላይ ተገኝታ ሙዚቃዎችዋን አቅርባለች።

Frankfurt Ehrung Künstler Äthiopien
ምስል DW/E. Zamora

ዋና መቀመጫዉን ጀርመን ያደረገዉ «የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኪነ-ጥበብ ማዕከል» የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ለመርዳት በኪነ-ጥበብ ካደጉ ሃገሮች እኩል ኪነ-ጥበብና ከያኒን ለማሳደግ እንዲሁም በኪነ-ጥበብ ካደጉ ሃገሮች ጋር ኪነ-ጥበብን ከያኒን ለማስተካከል፤ የተቋቋመ ማዕከል ነዉ። ይህ ማዕከል ከተቋቋመ አምስተኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን ድርጅቱ አቅም ያነሳቸዉን አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ይደግፋል፤ አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ወደ ጀርመን በመጋበዝ የክብር ሽልማት ይሰጣል። ማሕበሩ ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ ባዘጋጀዉ ዓመታዊ የክብር ሥነ-ስርዓት ላይ አንጋፋዉን አርቲስት አብራር አብዶን የክብር ተሸላሚ አድርጓል። የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ ፈቃደ እኔ ራሴ በዚሁ በኪነ-ጥበቡ ዉስጥ ያደኩ ሰዉ ነኝ። በመሆኑም ነዉ ይህንን ማኅበር ለመመስረት የተነሳሳሁት ሲሉ ገልፀዉልናል።

Frankfurt Ehrung Nigest Negassi II
ድምፃዊት እመቤት ነጋሲ ከሴቶች የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ተሸላሚምስል DW/E. Zamora

«ለኪነ-ጥበብ ፍቅር ያለኝ ፍቅር ነበር ይህን ማኅበር ለማቋቋም ያነሳሳኝ። ዋናዉ ነገር ግን ከብዙ ጊዜ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ በሄድኩት የአርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ሞትን አስመልክቶ ነበር። እዚህ ቦታ ላይ ስገኝ ቀደም ሲል በየትያትር ቤቱ የማዉቃቸዉ አንጋፋ የተባሉ ኢትዮጵያዉያን የሚወድዋቸዉ የሚያከብሩዋቸዉ አርቲስቶች በእዉነቱ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ሆነዉ ነዉ ያገኘኋቸዉ። እነዚህ በጣም ጥበብና ለኪነ-ጥበብ ፍቅር ያላቸዉ ሰዎች በኤኮኖሚም በጣም ወድቀዉ፤ ነዉ ያገኘኋቸዉ። ህክምናም በበቂ ሁኔታ የሚያገኙበት ነገር አልነበረም። ይህን ነገር ስመለከት ነዉ ወድያዉኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉን ክፍሎች ማለት እንደ ሙዚቀኛ ማኅበር፤ በትያትር ማኅበር የተለያዩ ክፍሎችን ይህ እንዴት ሆነ? እንዴትስ ነዉ ልንረዳቸዉ የሚገባዉ? ስል አነጋግርኩ። ብዙዎቹም ትኩረት ሰጡት ስብሰባ አድርገን ይህ ማኅበር ሊመሰረት ቻለ»

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የተቋቋመዉ ድርጅት ዛሬ አምስተኛ ዓመቱን ይዞ ለሶስተኛ ጊዜ ከአርባ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ መድረክ ታዋቂ የሆነዉን አንጋፋዉን ተዋናይ አብራር አብዶን ጋብዞ የክብር ሽልማት አበርክቶአል። አብራር አብዶ ስለተሰጠዉ ክብር እንዲህ ነበር የገለፀዉ።

«ብዙ ነገር ነዉ የተሰማኝ ። 42 ዓመት መድረክ ላይ ሰርቻለሁ፤ በዚህ ጊዜ ዉስጥ እንዲህ አይነቱን እዉቅና ሁለት ጊዜ ነዉ ያገኘሁት። ያገኘሁትም በመንግሥት ሳይሆን ከግለሰብ ነዉ። አንድ ጊዜ ፍቅር ሲፈርድ የሚል አንድ ትያትርን ሰርቼ በግለሰብ ተሸልሚያለሁ፤ ይህ ሶስተኛዩ ነዉ። እኔ ያገለገልኩት ረጅም ዓመት ለመንግሥት ነዉ፤ ከመንግሥት ግን አይደለም ይህን እዉቅናን ያገኘሁት። ሰርቼ አገልግዬ ጡረታ ከወጣሁ በኋላ ለእንዲህ አይነት እዉቅና መብቃት ትልቅ ነገር ነዉ ለኔ። ማንም ያላደረገዉን ጀርመን ሀገር መጥቼ ለዝያዉም ተጋብዤ፤ ወጪዬን አየር መንገድን ጠይቀዉም ቢሆን እዚህ ድረስ መጥቼ መሸለሜና ይህን እዉቅና ማግኘቴ፤ ለኔ ትልቅ ክፍያ ነዉ። ለኔ ለ42 ዓመት የሥራ አገልግሎቴ ትልቅ ክፍያ ነዉ። እንደገና ወጣት መሆን ቢቻል ይህ ሽልማት እንደገና ሥራዬን ሀ ብዬ እንድጀምር የሚያበረታታኝ የሚያስገድደኝ ነበር። አሁን ግን በተደረገልኝ ነገር እያመሰገንኩ ከመሄድ ዉጭ ልጅ መሆን አይቻልም እንጂ ይህ ሽልማት ልጅ ባደረገኝ ነበር። በጣም ነዉ ደስ ያለኝ።»

Frankfurt Ehrung Abrabrr Abdo
ምስል DW/E. Zamora

እንዲህ አይነቱ እዉቅና እኛ ተዋንያንን አልያም የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ መድረክ ማበብ ትልቅ አስተዋፅዖ አለዉ ያለዉ አንጋፋዉ ተዋናይ አብራር አብዶ ፤ በጀርመን ካለዉ ተሞክሮ መማር ይገባናል ሲል ገልጿል።

«መማር ከቻልን በጀርመን ከተቋቋመዉ የኪነ-ጥበብ በጎ አድራጎት ማኅበር ነዉ መማር ያለብን። ይህ በጎ አድራጎት ማኅበር አዲስ አበባ ዉስጥም ቅርንጫፍ አለዉ። የአዲስ አበባዉ ቅርንጫፍም የሚረዳዉ በጀርመን በሚገኘዉ በጎ አድራጎት ማኅበር ነዉ። እዚህ ባሉ ወጣቶች በተለይም ተፈሪ ፈቃደ እና ጓደኞቹ በሚያደርጉርጉት ጥረት ጀርመን ያሉ ኢትዮጵያዉያን በሚደርጉት ጥረት ነዉ። በዚህ ማኅበርም ብዙ ሰዎች እየተረዱ ነዉ። ዓመት በአል ጦማቸዉን የሚያድሩ ሰዎች ዓመት በአልን በጾም እንዳያሳልፉ ፤ ሲታመሙ በማሳከም ሲሞቱ ቀብራቸዉ እንዲያምር በማድረግ ይህ ማኅበር በጣም ትልቅ ሥራን እየሰራ ነዉ። ይህን ጉዳይም ለአለፉት አራትና አምስት ዓመታት ሁሉም የሚያዉቀዉ ይመስለኛል። እንግዲህ መማር ከቻልን ከዚህ ማኅበር ነዉ ብዙ ነገርን መማር የምንችለዉ። ያገለገሉ ሰዎች እንደ ሸንኮራ ተመጠዉ እንዳይጣሉ እንደዚህ ዓይነት እገዛ ያስፈልጋቸዋል። ይህ ማኅበር እኔን መሸለሙ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ ያደረጋቸዉ ነገሮች ብዙ ናቸዉ። ኢትዮጵያም ያለነዉ ከዚህ ማኅበር ርዳታ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ተጠናክረን ማኅበሩን መደገፍ አለብን።»

አንጋፋዉ ተዋናይ አብራር አብዶ በሽልማቱ ሥነ-ስርአት ላይ በሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን የተደረሰዉን ጴጥሮስ ያችን ሰዓት የተሰኘዉን ትርኢት ተጫዉቶ ነበር። እንደ አቡነ ጴጥሮስ ቆብ ደፍቶ መስቀል አጥልቆ በመድረክ ላይ ገፀ-ባህሪዉን ሲጫወት በአዳራሹ ያለዉን ህዝብ እጅግ ነበር ያስደመመዉ። እንደ ጣልያንም ሆነ ተጫዉተኃል ?
«አዎ በ 1978ዓ,ም ነዉ። ብርኃኑ ዘሪሁን የደረሰዉን ትያትር ነዉ። ድርሰቱ በጣም ጥርት ባለ አማርኛ ነበር የተፃፈዉ። ታድያ ትያትሩ ላይ ጣልያን ሆነህ ተዉን ሲሉኝ አማርኛዉን እንዳላበላሽ ጣልያን መሆኑን የሚያሳይ ነገር መኖር አለበት ተመልካቹ ፍፁም ፈረንጅ ነዉ ብሎ እንዲያምን ብዬ ተናገርኩ። ፊቴን ሜካፕ ቀባሁ፤ ቋንቋዉን ግማሹን ጣልያንኛ አድርጌ ግማሹን ጠመም አድርጌ ሰራሁት። በዝያ ምክንያት ትያትሩ እጅግ ተወዳጅ ሆነ። ረጅም ጊዜም በመድረክ ታየ። መድረክ ላይ እዉነት ጣልያን መስያቸዉ ለመግደል ሁሉ ሙከራ ያደረጉብኝ ሰዎች ነበሩ።»

Äthiopien Künstlerin Aselefech Ashene
ወ/ሮ አሰለፈች አሽኔ በጎርጎረሳዉያኑ 2013 ዓ,ምምስል DW/A. Tadesse Hahn

ብዙ ቋንቋቆችን እንደሚናገር የነገረን የስድሳ ሶስት ዓመቱ አንጋፋ ተዋናይ አብራር አብዶ ፤ « ጣልያንኛ አልችልም ለመማር ፈልጌ ጊዜ አጥቼ ተዉኩት ግን ከዉጭ ቋንቋዎች ፈረንሳይኛ እንጊሊዘኛ አረብኛ እችላለሁ፤ ከሀገራችን ደግሞ አማርኛ ኦሮምኛ ጉራጌኛ ቋንቋዎችን እችላለሁ። አራት ልጆች አሉኝ ባለትዳርም ነኝ። አብራር በአብዛኛዉ የምታወቀዉ በአገር ፍቅር ስትተዉን ነዉ?

«ከመጀመርያ ጀምሮ ሀገር ፍቅር ነዉ የጀመርኩት የጨረስኩትም ሀገር ፍቅር ነዉ። በርግጥ ጡረታ ሳልደርስ ነዉ በ 57 ዓመቴ በገዛ ፈቃዴ ሥራዬን የለቀኩት። ሥራዬን ለመልቀቅ ምክንያት ነበረኝ። አሁን በጡረታ ከተገለልኩ ስራዬን ትቼ ከወጣሁ አራት ዓመቴን ጨርሻለሁ። » ስራህን ከተዉክ በኋላ ወደ አገር ፍቅር ሂድ ሂድ አይልህም፤ አይናፍቅህም?
« ይለኛል ከዝያም ተለይቼ አላዉቅም። አገር ፍቅር የምደርሰዉ መደበኛ ሰራተኞች ጠዋት ስራቸዉ ላይ ከመገኘታቸዉ በፊት ነዉ። ሁሉኑም እቀድማቸዋለሁ። ማንም የሚፈልገኝ ሰዉ የሚያገኘኝ አገር ፍቅር ነዉ። እኔም ሰዉ የምቀጥረዉ አገር ፍቅር ኑ ብዩ ነዉ። እዛ እንኳ ባልቀጥር ሌላ ቦታ መሄድ ብፈልግ በግሪም ሆነ ቀጥታ ታክሲ ይዤ ብሄድ መጀመርያ የምሄደዉ አገር ፍቅር ነዉ። እዛ ሳልደርስ የትም ቦታ መሄድ አልችልም ሁሉ ነገር ነዉ የሚጠፋኝ። መኪናዬም ራስዋ መጀመርያ ይዛኝ የምትሄደዉ አገር ፍቅር ነዉ። ከዛ በኋላ ነዉ ወደ ጉዳዬ መሄድ የምችለዉ። እዛያ ሳልደርስ መሄድ አልችልም። ይህ የኔ ልምድ ነዉ። ምክንያቱ ደግሞ አገር ፍቅር ከእናቴ ቤት በላይ የኖርኩበት ቤቴ በመሆኑ ነዉ ፤ 42 ዓመት፤ ረጅም ጊዜ ነዉ።»

እኔ በነበርኩበት ባለሁበት ሞያ ላለዉ ወጣት መንገር የምፈልገዉ ይላል አንጋፋዉ ተዋናይ አብራር አብዶ በመጨረሻ « ወጣቱ ሞያዉን ወዶ እንዲሰራ ነዉ»

Äthiopien Künstlerin Aselefech Ashene
ወ/ሮ አሰለፈች አሽኔ በጎርጎረሳዉያኑ 2013 ዓ,ምምስል DW/A. Tadesse Hahn

ጀርመን ፊስ ባድን ነዋሪ የሆነችዉ ወጣት ሚስጥረ ነጋሽ «የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኪነ-ጥበብ ማዕከል» መድረክ ተሳታፊ ነበረች በመድረኩ ጥያቄ የሚል ግጥሟን አቅርባ ነበር።

ለዚሁ በጎ ተግባር ከአዲስ አበባ መጥታ በመድረክ ላይ ሙዚቃዎችዋን ያቀረበችዉ ድምፃዊት እመቤት ነጋሲ በበኩልዋ ፤« ማኅበሩን ለመርዳት ነዉ ሙዚቃዩን በመድረክ ያቀረብኩት ። ባህር ማዶ አቋርጦ እንደዚህ አይነት ትብብር ሲኖር እጅግ ጥሩ ነገር ነዉ። በዚህ ረገድ አቶ ተፈሪ ፈቃደ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ያለ ብቸኛ ሰዉ ነዉ፤ ሊበረታታ ድጋፍ ሊሰጠዉ የሚገባ ማኅበር ነዉ » ድምጻዊ እመቤት ነጋሲ ለዶይቼ አድማጮች ምን ይሻላል የሚለዉን አዲሱን ሙዚቃዋንም ጋብዛለች።

«የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኪነ-ጥበብ ማዕከል» የአገር ሀብት የሆኑትን የኪነ-ጥበብ ሰዎች በመደገፍ እየሰራ ያለዉ ሥራ ይበል የሚያሰኝ ይመስለናል። በኢትዮጵያም ሆነ በጀርመን የሚገኘዉን ይህን ማዕከል በመደገፍ የኢትዮጵያን ኪነ ጥበብ ማጎልበት ይኖርብናል ያሉንን የማኅበሩን አባላትና አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ሰዎች በማመስገን ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ