1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የኮንጎ ህገመንግስት

ዓርብ፣ ጥር 5 1998

የዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፑብሊክ ዜጎች ባለፈዉ ታህሳስ ወር በአገራቸዉ ሊያዩት የሚፈልጉትን የለዉጥ ሁኔታ በማሰብ በአዲሱ ህገመንግስት ላይ ህዝበ ዉሳኔ ሰጥተዋል። ይህ የተገኘዉ ተቀባይነትም በደም መፋሰስ ስትታተመስ ለቆየችዉ አገር አንድ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል። በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1960ዓ.ም ነፃ በወጣችዉ በዚች አገር ታሪክም ይህ የመድበለ ፓርቲ ምርጫ የመጀመሪያዉ ይሆናል።

https://p.dw.com/p/E0j9
አንዲት ኮንጓዊት ለህገመንግስቱ ድምፃቸዉን ሲሰጡ
አንዲት ኮንጓዊት ለህገመንግስቱ ድምፃቸዉን ሲሰጡምስል AP

የአገሪቱ መንግስት ትናንት በወሰነዉ መሰረትም በመጪዉ ሚያዝያ 20ቀን 1998ዓ.ም. የምክር
ቤትና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይካሄዳል። በዚህ ዙሪያ የዶቼ ቬለ ባልደረባ ዑታ ሼፈር የፃፈችዉ
ሀተታ የሚከተለዉን ፍሬ ኃሳብ ያንፀባርቃል።


አዲስ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ለመከተል የጀመረዉ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ደካማ መንግስት በዚህ ረገድ በዙ ተጠብቆበታል። ህገመንግስቱም 84 በመቶ የሚሆነዉን የኮንጎ ዜጎች ድምፅ ድጋፍ አግኝቷል።
በአገሪቱ ያለዉ ያልተረጋጋ ሁኔታና ሊከሰት የሚችል ማንኛዉም አጋጣሚ እንዳለ ሆኖ በአገሪቱ ያለዉ ግጭት በስምምነት እልባት ያገኛል የሚል ከፍተኛ ተስፋ ተጥሏል።
በአገሪቱ ያለዉን ስር የሰደደዉ የግጭት ሁኔታ ሲታይ የእነዚህ ተስፋዎች እዉን መሆን በእርግጥም ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነዉ። ምክንያቱም በምስራቃዊዉ የአገሪቱ ግዛት አሁንም ግጭቶችና አለመረጋጋት አለ።
በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙት ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ በታጠቀ ኃይል ቁጥጥር ስር ሲሆኑ የደንብ ልብስ የለበሰ የመንግስት ወታደር በአካባቢዉ አይታይም።
የአሜሪካ የህክምና ባለሙያዎች በዚህ ሳምንት ባወጡት ዘገባ መሰረት ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ የሰዉ ህይወት መጥፋቱ የተመዘገበዉ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ነዉ።
ላለፉት ሰባት ዓመታት በአካባቢዉ የታየዉ የአራት ሚሊዮኖ ሰዎችን ህይወት ለህልፈት የዳረገዉ መዘዝ ተደጋጋሚዉ የርሃብ አደጋ ወይም የጅምላ ጭፍጨፋ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ለግማሾቹ ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሚሆነዉነዉም የጤና እክል እንዲያም ሲል የወባ በሽታ ወረርሽኝ ነዉ።
እንዲህ ያለዉ የተፈጥሮና የጤና ችግር ሳያንስ በአካባቢያቸዉ ባለዉ የሰላም መደፍረስ የተቸገሩ ወገኖች የተረጋጋ ህይወት ለመኖር በመጓጓት አዲሱን ህገመንግስት በአዎንታ ተቀብለዋል።
ለኮንጎ ዲምክራቲክ ሪፑብሊክ ደካማነት ለሚታይባቸዉ መንግስታት በቂ ምሳሌ ነች ከአስተዳደሩ ደካማነት የተነሳ ማዕከላዊዉ አስተዳደር ለየአካባቢዉ መስተዳድሮች የሚሰጠዉ መመሪያ የተሰነካከለ ነዉ።
ህዝቡ ቀላል የሚባሉ መሰረታዊ ነገሮችን እንኳን ለማግኘት አይችልም። መሰረተ ልማቱም በእጅጉ የተዳከመ ነዉ።
ህዝቡ ንፁህ የመጠጥ ዉሃ ሆነ ህክምና የማግነት እድል የለዉም፣ይኸም ከ60 ሚሊዮኑ ህዝብ መካከል የአብዛኛዉ ህዝብ ዕጣ ፈንታ ነዉ።
ከዚህ ተነስቶም ህዝቡ ለአዲሱ ህገመንግስት ድጋፉን ቢያሳይ አይገርምም ለምን ቢባል ህግመንግስቱ የዕለት ተዕለት ህይወታቸዉን ሊያሻሽሉ የሚችሉ መሰረታዊ ጉዳዮችን አካቷልና ነዉ።
የፖለቲካዉ መሰረታዊ ችግር ተፈትቶ በሰዎች ህይወትና የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚደርሰዉ ሰቆቃ እንዲያ ከትም 84በመቶ የሚሆነዉ የበርካታ ኮንጓዉያን የዉሳኔ ህዝብ ድምፅ ያሳየዉም ይኼንኑ ነዉ።
ዲምክራቲክ ኮንጎ ከምትገኝበት የድህነት ኑሮና የምጣኔ ሃብት ቀዉስ እንድትወጣም የሚያስፈልጋት በህገመንግስት በአግባቡ የሚተዳደር ዲምክራሲ የሰፈነበት አካሄድ መከተል ይሆናል።
ይህ ህገመንግስት በፓለቲካዉና በጦር ኃይሉ እንዲሁም የአገሪቱን የምጣኔ ሃብት ተቆጣጥረዉ የነበሩ ወገኖች ተሳስረዉ የነበሩበትን ሁኔታ ይቃረናል።
በአካባቢዉ የሚታየዉን ስርዓተ አልበኝነት፤ በተጨማሪም በምስራቃዊዉ የአገሪቱ ክፍል በአማፅያንና ተዋጊዎቻቸዉ የሚፈፀመዉ ዝርፊያና አስገድዶ የመድፈር ተግባርን ለማስወገድ የጋራ እንቅስቃሴ እንደሚኖር ይገልፃል።
እዚህ ጋ የትኞቹ ጉዳዮች መቅደም አለባቸዉ የሚለዉን ቁልፍ ጥያቄ መመለስ ይከብዳል። በቅድሚያ ኮንጎዎች ፕሬዝደንታቸዉን መርጠዉ የፓርላማ አባላትን ይምረጡ? ወይም ፓርላማ አባላትን ቅድሚያ ከዚያ ፕሬዝደንታቸዉን?
በረጨማሪም ፀኃፊዋ የአገሪቱን ጦር መልሶ ከመመስረቱ ሂደት ጋርስ ነፍጥ ያነገቡትን ልዩልዩ አካላትን ትጥቅ የማስፈታቱ ነገር እንዴት መሆን ይገባዋል? በማለት ትጠይቃለች።
በፀኃፊዋ እምነት አዲሱ ህገ መንግስት በተዳከመችዉ አገር ያለዉን የታጠቀ ኃይል ለማስወገድ የሚችል የተዘጋጀ መፍትሄ ይዞ የቀረበ አይደለም።
ሆኖም በአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ምስረታ መጀመሪያ ሊታይ ይችላል በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በጋራ መድረክ ተጠቅመዉ በመካከለኛዊቷ ሰፊ የአፍሪካ ግዛት በዚሁ መንግድ ሊወዳደሩና ሊመረጡበት ይችላሉ።
በዚህም ለተወሰነ ዓመት ሊያገልግል የሚችል ፕሬዝደንት በመምረጥ እንዲሁም ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተወከሉበት የጋራ መንግስት በበዲሞክራሲያዊ መንገድ በመመስረት ያለፈዉ መንግስት የሚያከትምበት ይሆናል።
ሆኖም በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረ የዲሞክራሲ ፅንሰ ኃሳብ ብቻ ግን ምንም የሚፈይደዉ አይኖርም።