1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የኤርትራ ናቅፋና ዉዝግቡ

ማክሰኞ፣ ጥር 10 2008

የኤርትራ መንግሥት አዲስ የናቅፋ ኖት አትሞ እያሰራጨ ነዉ። ህብረተሰቡም አሮጌዉን ናቅፋ በመመለስ በአዲስ እንዲቀይር መንግሥት ጠይቆአል። በአዲስ የተቀየረዉን ገንዘብ ግን ከባንክ ለማዉጣት ያለዉ ችግር ከፍተኛ መሆኑን ኤርትራዉያን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/1Hg8I
21.01.2013 Karte Eritrea Asmara eng

[No title]

በሌላ በኩል መንግሥት በባንክ ቤት ያለ ገንዘብ እንዳያወጣ የሚከለክል ምንም አይነት ችግር ወይም ሕግ የለም ሲል ይገልፃል።
የኤርትራ መንግሥት አዲሱን የመገበያያ ገንዘብ ናቅፋን ማከፋፈል ጀምሮአል። መንግሥት ይህን አዲስ የመገበያያ ገንዘብ « ናቅፋ» በሕዝብ እጅ እንዲገባ ከማድረጉ በፊት ኅብረተሰቡ በእጁ የሚገኘዉን የናቅፋ ኖት በአስቸኳይ ባንክ ቤት እንዲያስገባ የሚሣስቡ አዋጆችን አዉጥቶ ነበር። የኤርትራ ሕዝብ ነግዶ፤ ቆጥቦ ፤ በዉጭ ከሚኖሩ ዘመድ ወዳጆቹና ልጆቹ የተላከለትን ገንዘብ በአዋጁ መሠረት ባንክ ቤት አስገብቶአል። የዚህን አዲስ የመገበያያ ገንዘብ «ናቅፋ» መምጣት ተከትሎ በኤርትራ ዉስጥ ጉምጉምታ አለ። ጉምጉምታዉ ሕዝቡ ባንክ ቤት ያስገባዉን ገንዘብ እንደፈለገ በፈለገዉ ሰዓትና ወቅት ማዉጣት አልቻለም የሚል ነዉ። ሰዎች ኤርትራ በሚገኙ ባንክ ቤቶች ካላቸዉ ገንዘብ የተወሰነዉን ለማዉጣት መንግሥት ያዘጋጀዉን የመጠይቅ መዘርዝር መሙላት የግድ ይላቸዋል። ከመጠይቆቹ መካከል «ናቅፋ» ገንዘብን ለምን ከባንክ ታወጣለህ? የምትገዛዉ የቤት ቁሳቁስ ወይም ለንግድ የሚሆን የፍጆታ እቃ ከየትኛዉ መደብር ነዉ የምትገዛዉ የሚሉ ጥያቄዎች ይገኙበታል። ይህ ጉምጉምታና ቅሪታ አዉሮጳ ድረስ ተሰራጭቶአል። አዉሮጳ ጀርመን ነዋሪ የሆኑት ኤርትራዊዉ አቶ ወልደ ገብርኤል ስብኃቱ እንደሚሉት መንግሥት ሕዝቡን የባሰ ችግር ዉስጥ እያስገባዉ ነዉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ የኤርትራ ማስታወቅያ ሚኒስቴር አቶ የማነ ገብረ መስቀል እደሚሉት አለ የሚባለዉ ችግር ከባድ አይደለም።
«ሕዝቡ ከኤርትራ ባንክ ቤቶች ከባንክ እንዳያወጣ የሚከለክል ሕግ የለም። ግን ገንዘብ አወጣጥ ላይ የራሱ የባንክ ቤት ሕግ አለ። ከ 20 ሺህ ናቅፋ በላይ ከሆነ ባንክ ቤቱ ጥሪ ገንዘብ አይሰጥም። ቼክ ነዉ የሚሰጠዉ የቼክ አሰጣጥ ሕጉ አሁን የወጣ ሳይሆን ቀደም ሲል ይሰራበት ነበር። እና አሁን በቅርቡም የኤርትራ ባንክ ኃላፊዎች ከባንክ የገንዘ አሠጣጥና ሌሎች ተዛማች የባንክ አሠራሮችን በተመለከተ መግለጫ ስለሚሰጡ ተጠቃሚዉ ህብረተሰብ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ያገኛል። ጉዳዩ እኮ ግልፅ ነዉ። ገንዘብ ከባንክ ሲወጣ በቼክና በትራንዛክሽን ጭምር ስለሆነ ጥሬ ገንዘብ አወጣጥ ላይ ትኩረት ይደረጋል»
የኤርትራ መገበያያ ገንዘብ የሆነዉ « ናቅፋ» ወደ ይሮ ሲመነዘር 100 ይሮ ወደ 1800 ናቅፋ ሲሆን በጥቁር ገበያ እስከ 5200 ናቅፋ እንደሚሆን ይነገራል።


ጎይቶም ቢሆን

አዜብታደሰ