1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የቡሩንዲ መንግሥት እና የገጠመው ተቃውሞ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 16 2007

የቡሩንዲ ፕሬዝደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ የፊታችን ረቡዕ እጎአ ነሐሴ 26 ቀን፣ 2015 ዓ.ም. ቃለ መሀላ ይፈፅማሉ ተብሎ እየተጠበቀ ሳለ ነበር ባለፈው ሀሙስ ሳይታሰብ ለሶስተኛዉ የስልጣን ዘመናቸዉ ቃለ መሀላ የፈፀሙት። የሀገሪቱ መንግሥት ባለስልጣናት እና የጦር ኃይሉ ቃለ መሀላው እንደሚካሄድ እንዳላወቁ ነው የተናገሩት።

https://p.dw.com/p/1GJcp
Burundi Vereidigung Präsident Nkurunziza
ምስል Reuters/E. Ngendakumana

[No title]

ይሁን እንጂ፣ ስነ ስርዓቱ ወደተካሄደበት ቤተመንግሥት የክብር ልብስ ወይም መለዮ አጥልቀው እንዲሄዱ ፣ በአንፃሩ በቡሩንዲ የሚገኙት የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሰራተኞች በየቤታቸው እንዲውሉ ቀደም ሲል ተነግሮዋቸው እንደነበር ነው ባለስልጣናቱ የገለጹት። የፊታችን ረቡዕ ሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው በይፋ የሚያበቃው ንኩሩንዚዛ ቃለ መሀላውን ቀደም ብለው እንደሚፈፅሙ ቢገምቱም፣ እንዲህ ተፋጥኖ ይደረጋል ብለው እንዳልጠበቁ በቡሩንዲ የፕሬስ ስራ ታዛቢ ቡድን ኃላፊ እና የአንድ መገናኛ ብዙኃን ተቋም ባለቤት የሆኑት ኢኖሶ ሙሆዚ በማስታወቅ አሳሳቢው የፀጥታው ጉዳይ ሚና ተጫውቶ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

« በመዲናይቱ ቡጁምቡራ፣ ባጠቃላይ በቡሩንዲ የፀጥታው ሁኔታ አያስተማምንም። እና ባለስልጣናቱ ቃለ መሀላው የሚፈጸምበትን ቀን ይፋ ካደረጉ ምናልባት ጥቃት ሊጣል ወይም ተቃውሞ ሊካሄድ ይችላል በሚል ስጋት ይሆናል አስቀድመው ያካሄዱት፣ ዋናው ምክንያት የፀጥታ ጉዳይ ይመስለኛል።

Belgien Veranstaltung mit Exil-Burundern im Brüsseler Stadtparlament
በስደት የሚኖሩ የቡሩንዲ ዜጎችምስል DW/K. Matthaei

የቡሩንዲ ተቃዋሚዎች ሕገ ወጥ ነው በሚሉት የንኩሩንዚዛ መንግሥት አንፃር በየጊዜው ግልጹን የተቃውሞ ጥሪ የሚያስተላልፉበት ድርጊት ሲታሰብ ቃለ መሀላው አስቀድሞ መፈፀሙ በፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው ነው ከምክር ቤት ውጭ የሚንቀሳቀሰው የሕገ መንግሥቱ፣ የሰብዓዊ መብት እና የአሩሻ የሰላም ስምምነት አስጠባቂ ምክር ቤት የተባለው እና በስደት የሚኖሩ የቡሩንዲ ዜጎችን የሚወክለው በምህፃሩ «ሴናሬድ» በመባል የሚታወቀው ተቃዋሚ ቡድን ፕሬዚደንት ሌዎናር ኖንጎማ ያስታወቁት።

« በሕገ መንግሥታችን መሠረት፣ የስልጣን ዘመናቸው እጎአ ነሀሴ 26፣ 2015 ነው በይፋ የሚያበቃው፣ እና ዛሬ የፈፀሙት ቃለ መሀላ ሕገ መንግስቱን የሚጥስ ነው። በመሆኑም፣ ለኛ እንዳልተፈፀመ ነው የምንቆጥረው። »

በዚህም የተነሳ የተለያዩት የሃገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህብረት የሃገሪቱን ሕጎች መርገጣቸውን የቀጠሉትን ንኩሩንዚዛ እና መንግሥታቸው ፣ ካስፈለገም በኃይሉን ተግባር ለማስወገድ ቆርጦ መነሳቱን ሌዎናር ኖንጎማ አመልክተዋል።

« ንኩሩንዚዛ በሕዝቡ ፍላጎት አንፃር በስልጣን ሊቆዩ አይችሉም። በ«ሴናሬድ» ስር የተደራጀው የቡሩንዲ ሕዝብ የንኩሩንዚዛን አምባገነናዊ አገዛዝ ለመጣል ተዘጋጅቷል። ሕጉን የጣሰ ርምጃ ማስወገዱ የህዝቡ ሕጋዊ መብቱ ነው። ግን ፣ አሁንም ለድርድር ጊዜው ገና አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል። እና ንኩሩንዚዛ እስከ ነሀሴ 26 ድረስ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ከሆኑ፣ እኛም ከሳቸው በኋላ ከሚመጣው የመንግሥቱ ተወካይ ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነን። »

Flagge von Burundi
ምስል picture-alliance/Philipp Ziser

በናይሮቢ የሚገኙት የዓለም አቀፉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ዮሎንድ ቡካ እንደገመቱት፣ ንኩሩንዚዛ ሳይታሰብ ቃለ መሀላ መፈፀማቸው ከተቃዋሚዎች የተደቀነባቸውን ስጋት ለማስወገድ ነው።

«ንኩሩንዚዛ በዚሁ ርምጃቸው ባንድ በኩል በሶስተኛው የስልጣን ዘመናቸው እንደሚቀጥሉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ፣ መንግሥት በሃገሪቱ የፖለቲካውን ምህዳር እና የፀጥታውን ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ አሁንም መቆጣጠሩን ለተቃዋሚዎች ግልጹን መልዕክት ለማስተላለፍ የፈለጉ ይመስለኛል። ሕዝቡ ቃለ መሀላው በተፈጸመበት እና በፊት ይፈፀማል ተብሎ በታቀደበት ነሀሴ 26 መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ አለመረጋጋት ለመፍጠር ሲል የሆነ ተቃውሞ አስቦ እንደነበር ጭምጭምታ ተሰምቶዋል። »

ይህ የንኩሩንዚዛ ርምጃ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭም ቢሆን ትችት እንዳላጣው እና ገፅታቸውንም እንደማያያሻሽለው መንግሥታዊ ባልሆነው የቤልጅየም ድርጅት ቲስ ቫን ላየር አስታውቀዋል።

« ፕሬዚደንቱ በዚሁ ርምጃቸው ጥንካራ አቋም ላይ እንደሚገኙ ለማሳየት ነው የሞከሩት፣ ምክንያቱም፣ በፕሬዚደንታዊው ምርጫ አሸናፊ ሆነዋል። ይሁንና፣ ጠቅላላው የሶስተኛ የስልጣን ዘመናቸው በሃገሪቱ ብቻ ሳይሆን፣ የምርጫውን ውጤትም ሆነ አሸነፍኩ ያሉትን ፕሬዚደንት እንደማይቀበል ባስታወቀው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ዘንድ ቢሆን ማከራከሩ አይቀርም። »

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ