1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አይሁድ ጀርመናዉያን ወደ ደቡብ አፍሪቃ ስደት

ሐሙስ፣ ኅዳር 27 2005

« በፖለቲካ እና በቀለም፤ በዘር ጉዳይ ከሆነ አይሁዳዉያን ከሌሎች ነጮች ይልቅ ግልፅ ሆነዉ ነዉ ያገኘኋቸዉ። ምናልባት እነሱም ከዚህ ቀደም በዘረኝነት ጉዳይ ሌሎቹ ተጠቂዎች ስለነበሩ ይሆናል»

https://p.dw.com/p/16wtt

« በፖለቲካ እና በቀለም፤ በዘር ጉዳይ ከሆነ አይሁዳዉያን ከሌሎች ነጮች ይልቅ ግልፅ ሆነዉ ነዉ ያገኘኋቸዉ። ምናልባት እነሱም ከዚህ ቀደም በዘረኝነት ጉዳይ ሌሎቹ ተጠቂዎች ስለነበሩ ይሆናል» የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪቃ ፕሪዚደንት የጥቁር ህዝቦች ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በደቡብ አፍሪቃ ተሰደዉ የገቡትን አይሁዳዉያን በተመለከተ የተናገሩት ነበር። ሁለተኛዉን የዓለም ጦርነት፤ እና የዘር መድሎ ና ግፍ ጭፈቸፋን በመሸሽ አይሁዳዉያን በተለያዩ አለማት ተሰደዋል። በለቱ ዝግጅታችን ከጀርመን ወደ ደቡብ አፍሪቃ ስለተሰደዱት የጀርመን አይሁዳዉያን ታሪክ ይዘናል
«በጎርጎረሳዉያኑ ጥቅምት 09/ 1936 ዓ,ም ነዉ። ስደተኞችን የሚያመላልሰዉ« ሽቱትጋርት» በየተሰኘችዉ መርከብ ላይ ተሳፍሬ በስተመጨረሻ ፀጥታን እና ግዜን አግንቼ፤ በሃሳብ ዉሳኔዬ ትክክል ነዉ ትክክል አይደለም እያልኩ ራሴን ስጠይቅ፤ በቀጣይ እንዴት ይሆን? በሚል፤ የለጋ ቤተሰቤን እጣ ፈንታ ለመወሰን ሳወጣ ሳወርድ ነበር።»  ሚሪያም ክላይናብስት፤ ቀለሙ የወየበዉን ይህን ደብዳቤ ሲያነቡ ሲቃ የያዛቸዉ የመሰለዉ ማንበብ ተስኖአቸዉ ይሆን? ወይስ ያሳለፉት ያሁሉ ዉጣ ዉረድ ተዝ ብሎአቸዉ? የሰማንያ ዘጠኝ አመትዋ ወይዘሮ በአንድ «የጥሩ ተስፋ ፓርክ» በተሰኘ የአዛዉንቶች መኖርያ ህንጻ፤ ስድስተኛ ፎቅ ላይ በሚገኘዉ መኖርያ ቤታቸዉ፤ የእንግዳ መቀበያ ክፍል ዉስጥ ተቀምጠዋል። በጃቸዉ አባታቸዉ የዛሬ 79 ዓመት «ሽቱትጋርት» በተሰኘችዉ መርከብ ጀርመንን ለቀዉ ሊወጡ ሲሉ እዚሁ አገራቸዉ ለቀሩት ቤተሰቦታቸዉ የጻፉትን ደብዳቤ ይዘዋል።

ሚሪያም ክላይንቢስት አስራ ሁለት አመት እስኪ ሆናቸዉ፤ ለዘብተኛ አቋም ካላቸዉ አያታቸዉ ጋር፤ ያለምንም ችግር ቦርቀዉ ነዉ ያደጉት። በጨቅላ ዕድሜያቸዉ ከአያታቸዉ ጋር የረፍት ግዜያቸዉን በሰሜናዊ ጀርመን አኳያ በሚገኘዉ «ሽፒከሮግ» በተባለችዉ ደሴት ላይ በዋና እንዲሁም በበረዶ መንሸራተቻ ስፖርት ተዝናንተዋል። ያም ሆኖ አያታቸዉ ለቀቅ ያለ አያያዝ ቢኖራቸዉም፤ በቤቱ ደንብ መሠረት የአይሁድ ባህል በከፍተኛ ሁኔታ ይጠበቃል፤ ይታወሳልም። የአይሁድ ባህላዊ ምግብ ይሰራል፤ አርብ እና ቅዳሜም ሙክራብ ማለትም የአይሁድ ቤተ-መቅደስ ይኬዳል።
ያ የቡረቃ የደስታ የልጅነት ግዜ ሂትለር በጎርጎረሳዉያኑ 1933 ዓ,ም ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ አበቃ። በሂትለር ርዕዮተ አለም የተኮተኮቱ ወጣቶች የዛን ግዜዋን ወጣት ልጃገረድ በመንገድ ላይ ሲያገኙዋት ይደበደቡዋት ያሰቃይዋት ነበር። አንድ ግዜ እንደዉም እንደዚሁ ወጣቶች መንገድ ላይ አግኝተዋት ተናካሽ ዉሻ ወደስዋ በመልቀቅ አስፈራርተዋታል። ከዚያ ግዜ ወዲህ ወጣትዋ ሚሪያም ለወትሮዉ በየግዜዉ ትዝናናበት ወደነበረበት ሲኒማ ቤት መሄድን አቆመች፤ አባትዋም የነበራቸዉን ጫማ መስርያ ቤት ለመዝጋት ተገደዱ።  ከዚያም ጀርመንን እየጣለ የሚወጣዉ አይሁዳዊ ቁጥር ተበራከተ። በዚህ ምክንያትም፤ በርካታ የጀርመን አጎራባች አገሮች ለጀርመን አይሁዳዉያን ድንበሮቻቸዉን እየዘጉ መጡ። በአሜሪካ፤ በአዉስትራልያ፤ በካናዳ፤ በጥገኝነት የገባዉ አይሁድ መጠን አገራቱ መቀበል ከሚችሉት መጠን በላይ ሆነ ቁጥሩ። በሌላ በኩል በደቡብ አፍሪቃ በጥገኝነት የገቡ ጀርመናዉያን አይሁዶች በነጭ የደቡብ አፍሪቃ ፖለቲከኞች የተወደዱ፤ ጥሩ ስደተኞች ሆነዉ ተገኙ። በጎርጎረሳዉያኑ 1936 ዓ,ም በአንድ አመት ግዜ ዉስጥ ብቻ 2500 ጀርመናዉያን አይሁዶች፤ በደቡብ አፍሪቃ ጥገኝነት ጠይቀዋል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሁኔታዎች በሙሉ ተቀያየሩ። በደቡብ አፍሪቃዉያኑ በአገራችን የዉጭ አገር ዜጋ በዛብን የሚል ተቃዉሞ ምክንያት ፤ አገሪቱ በጥገኝነት የምትቀበለዉን የዉጭ አገር ዜጋ መጠን የሚደነግግ ህግ ይፋ ሆነ።

Symbolbild - Kapstadt
ምስል Getty Images
Deutsch-jüdisches Kulturerbe: Gegenstand Südafrika
ምስል DW
Deutsch-jüdisches Kulturerbe Südafrika
ምስል DW/Schadomsky

በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ነጭ ዘረኞች በአገራችን የዉጭ አገር ዜጋ እያጣበበ ነዉ ሲሉ አመፅ ጀመሩ። በጀርመን ነዋሪ የሆኑት አይሁዳዉያኑ የሳምሶን ቤተሰቦች ጀርመንን ለቆ ለመዉጣት መፍጠን ይኖርባቸዋል። በጎርጎረሳዉያኑ ጥቅምት ወር 1936 ዓ,ም በጀርመን ብሬመን ወደብ ሽቱትጋርት የተሰኘዉ መርከብ በመጨረሻ ጉዞዉ 570 አይሁድ ጀርመናዉያንን አሳፍሮ ጉዞዉን ሲጀምር ሞሪትዝ ሳምሶንም ከመርከቡ ተሳፋሪዎቹ አንዱ ነበሩ።

የአይሁዳዊዉ ጀርመናዊ የሞሪትዝ ሳምሶን ቤተሰቦች ግን ሚሪያምን ጨምሮ በሚቀጥለዉ መርከብ ተሳፍረዉ ሊመጡ በማቀድ  እዚሁ ጀርመን ቀርተዉ በአፍሪቃ ሲኖሩ ቶሎ ገንዘብ ለማግኘት እንዲረዳቸዉ እናታቸዉ ልብስ ቅድ እና ስፌትን ተማሩ። ከዚያም ሚሪያም እናትዋ እና ወንድሟ ክላዉስ በጎርጎረሳዉያኑ 1937 ዓ,ም ጥር ወር ነዉ በጣልያን ሰሜናዊ ምዕራብ የወደብ ከተማ ከሆነችዉ ጌኑአ በመርከብ ተሳፍረዉ ወደ አፍሪቃ ጉዟቸዉን ያቀኑት። በጉዞ ወቅት እናት ልጆችዋ  በፍርሃት እንዳይሸበሩ ነገሮችን ለመሸፋፈን የተቻላትን ሁሉ አድርጋለች። እዚሁ ጀርመን የቀሩት አያት ግን፤ ቤተሰቦቻቸዉ ወደ አፍሪቃ ጉዞ ሲጀምሩ ስንብት ላይ «መቼም ደግመን አንተያይም» በማለት እዉነቱን ሳይናገሩ አላለፉም።  ትዳር ከመያዛቸዉ በፊት በአባታቸዉ ስም ሚሪያም ሳምሶን በመባል ይጠሩ የነበሩት የዛሬዋ አዛዉንት ሚሪያም ክላይንብስት በ13 አመታቸዉ አባታቸዉ ወደተሰደዱባ ደቡብ አፍሪቃ ኬፕታዉን በመጓዝ ነዉ ከአባታቸዉ የተገኛኑት። ሚሪያም ከአባታቸዉ ጋር ደቡብ አፍሪቃ ላይ ዳግም ሲገናኙ የነበረዉን ሁኔታ ከ 75 ዓመት በኃላ ዛሬ ካይን የተሰኘዉን የኬፕታዉን ወደብ እየጎበኙ እንዲህ ያስታዉሳሉ፤

Deutsch-jüdisches Kulturerbe Südafrika Museumsexponat
ምስል DW/Schadomsky

« ቀኑ በጣም በጣም ሞቃት ነበር። መርከቡ ላይ ሆኜ ማግኘት የምፈልገዉ አባቴን ብቻ ነበር። መርከቡ ላይ ቆሜ ቁልቁል ስመለከት አባቴን አየሁት። በዚህም ምክንያትም አካባቢዉ ምን ይመስል እንደነበር እንኳ አላስተዋልኩም። የደረስነዉ ማለዳ ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰአት ላይ ነዉ። በርግጥ በጣም ተርበን ነበር። ያን ግዜ አባቴ መርከቡ ላይ የሚሰራ ሰዉ ያዉቅ ስለነበር፤ ቸኮላት እና አይስክሪም ሰጠን እና ርሃባችንን አስታገስን፤ አንድም ከአባታችን በኩል የመጣ በመሆኑም እጅግ ጣፈጠን፤ በሌላ በኩል በጣም እርቦኝ በመጀመርያ ያገኘሁት ይህንኑ አይስክሪም ነዉ።»

የአስራ ሶስት አመትዋ ሚሪያም በደቡብ አፍሪቃ የኬፕታዉኑን አዲስ ቤት ቶሎ ተላመደች። ኬፕታዉን በገባች በነጋታዉ በጎረቤት የሚኖሩ ልጆች ከወላጆችዋ የተገናኘችዉን አዲስ እህታቸዉን ለመተዋወቅ መጡ። አዲስ ህይወት በአዲስ አገር የጀመሩት ወላጆችዋ ግን ሁኔታዉ ከብዷቸዋል። አባት ሳምሶን ምንም አይነት ስራን ማግኘት አልቻሉም። ቤተሰቡን የማስተዳደሩ ሃላፊነት እናት ላይ ወደቀ። የአገሩን አኗኗር እና ባህል በቶሎ ለመተዋወቅ እና ስራ ፍለጋዉንም ለማቃለል ቤት ዉስጥ የመነጋገርያ ቋንቋዉ ጀርመንኛ ሳይሆን እንግሊዘኛ ብቻ ሆነ። ጀርመንኛ ቋንቋን ቤት ዉስጥ ለመግባቢያ መጠቀሙ ሲቆም የአይሁድ ባህላዊ አኗኗራቸዉም እየደበዘዘ መጣ ። የቤቱ ጥበትም የአይሁድ ባህላዊ ምግቦችን ማብሰልን ከባድ አደረገዉ።  ለሁለት አመት ብቻ ትምህርቷን መከታተል የቻለቸዉ ሚሪያም ትምህርትዋን አቋርጣ በባርኔጣ ስፊት ስራ ተቀጠረች። በሁለተኛዉ አለም ጦርነት የሂትለርን ጦር በመዉጋት ላይ ያለዉን ጥምሩን ጦር ደቡብ አፍሪቃ መርዳት መፈለግዋን ስታስታዉቅ ከሚሪያም እና ከናቱ ጋር ኬፕታዉን ደቡብ አፍሪቃ የገባዉ የሚሪያም ወንድም ክላዉስ ሂትለርን ለመዉጋት በፈቃደኝነት ለዘመቻ ተነሳ።

ከዚያም  እ,ጎ,አ 1948 ዓ,ም የመጣዉ እድል የወደፊት ህይወታቸዉን እጣ ፈንታ ቀየረዉ።  በደቡብ አፍሪቃ በተደረገዉ ምርጫ የብሄራዊ ፓርቲ አሸንፎ በርካታ ህጎች በተለይም የቀለም የዘር ልዩነትን መሠረት ያደረጉ  ህግጋቶች ፀደቁ። የወጣዉ ህግ ለሳምሶን እንደማይበጅ የታወቀ ነዉ።  ከአስርተ ዓመታት በላይ የናዚን ጦር ሽብር ሲሸሹና ሲሳደዱ የነበሩ የጀርመን አይሁዳዉያን፤ ለዚህ በአዲስ ስልት ሰብአዊ መብትን ለሚገፈዉ ስርዓት ምላሻቸዉ እንዴት ይሆን?

Deutsch-jüdisches Kulturerbe in Südafrika Bildergalerie Bild 8
ምስል DW/Schadomsky

ሪቻርድ ፍሪድማን በደቡብ አፍሪቃ ኬፕታዉን ከተማ በግፍ የተገደሉ አይሁዳዉያን መታሰቢያ ማዕከል ዋና ዳይሪክተር  ናቸዉ። በኬፕታዉን የሚገኘዉ የፍሪድማን መኖርያ ቤት ከጥቂት አመታት በፊት የጀርመን ስደተኞች ቤት ተብሎ የአዉደርዕይ ማዕከል ሆኗል። በዚህም የሚሪያም ሳምሶን የአሁንዋ ሚሪያም ክላይቢስት ታሪክ ተጽፎ ይገኛል። «በደቡብ አፍሪቃ ጀርመን አይሁዳዉያን እንደሌሎች ስደተኞች ሁሉ በድጋፍ እና ከለላ ስር ለመቆየት ሞክረዋል። በወቅቱ የዚህ ስቃይ ሰለባ ከነበርክ ይህ የግፍ እልቂት በሌሎች ላይ ሲደርስ  እንዴት ዝም አልክ? ብሎ አንድ ከዚህ ጭፍጨፋ የተረፈ አይሁድን መጠየቅ ተገቢ አይመስለኝም። እርግጥ ነዉ አፓርታይድ ህይወታቸዉን በጥብጧል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኑሯቸዉን እንደገና ለማቋቋምና ቤተሰብ ለመስረት ትዳር ለመያዝ ስራ ለማግኘት እና ስቃያቸዉን ለማስታገስ እየታገሉ ነበር። ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ እንደዉም የመብት ተሟጋቾች ሆኑ። ይሄ በእዉነቱ የሚያስገርም ነዉ። ከነሱ ይህን ማንም አልጠበቀም ነበር።» የእስራኤል ቤተ-መቅደስ በተሰኘዉ የአይሁዳዉያኑ ፀሎት ቤት ደግሞ  ራቢ ሪቻርድ ኒዉ ማንን እናገኛለን። ይህ የአይሁዳዉያኑየ ፀሎት ቤት የሚገኘዉ ግሪን ፖይንት በሚባለዉ እና ቀድሞ የአይሁዳዉያ መኖርያ ስፍራ ነዉ። በዚህ ቦታ አሁንም የአይሁዳዉያን ማህበር የሚገበያይበት እና የአይሁዳዉያን ባህል የምግብ አይነቶች የስጋ መሸጫ ቤትም አለ። ከዛሬ አምስት አመት ጀምሮ በኬፕታዉን ግሪን ፖይንት የተሰኘዉን የአይሁዳዉያን ማህበር የሚያስተዳድሩት ራቢ ኖይ ማን፤ የልጅነት ግዜያቸዉን በርሊን ዉስጥ አሳልፈዉ ከዚያ ከቤተሰቦቸዉ ጋር ወደ ብሪታንያ ተሰደዉ ኖረዋል። በደቡብ አፍሪቃ ስራ ከመጀመራቸዉ በፊት በእስራኤል፤ ዩናይትድ ስቴትስ  እንዲሁም ጀርመንም ሰርተዋል።   «የአይሁዳዉያን ጭፍጨፋ እና የሁለተኛዉ የአለም ጦርነቱ በጀርመን በአይሁዳዉያን ላይ ያሳደረዉ ተፅዕኖ  ጠንካራ በመሆኑ  ወደ ደቡብ አፍሪቃ  የተሰደዱት አይሁዳዉያን ስሜታቸዉ ተጎድቷል፤ በዚህ ምክንያትም አፓርታይድን ለመቃወም ፖለቲካዉ ዉስጥ አልተሳተፉም። ከጀርመን የተሰደደዉ የኔ የራሴ አባት ለምሳሌ፤ ስሜቱ እጅግ ተጎድቶ ነበር። ጨቋኝ አስተዳደርን ቀርቶ የማይደግፈዉን የፖለቲካ አቋም እንኳ  ለመታገል ፍፁም አቅም አልነበረዉም።» የሚሪያም ቤተሰብ አሁን «መንደር  ስድስት» ተብሎ ታዋቂ ከሆነዉ አካባቢ መንግስት ኗሪዎችን በግዳጅ ከአካባቢዉ ሲያነሳ ጭንቅ ዉስጥ ወደቁ። በአካባቢዉ ከአስርተ አመታት በላይ ነጭ ፤ጥቁር ሙስሊም ክርስትያን እና ይሁድ በጋራ በወንድማማችነት ኖረዋል። ከዕለታት ባንዱ ቀን ምሽት ከነጩ በቀር፤ ጥቁር እንዲሁም የህንድ ዝርያ ያላቸዉ ዜጎች በሙሉ ከስፍራዉ ተባረዉ ቤታቸዉ በቡልዶዘር ታረሰ። እንድያም ሆኖ ይላሉ የ89 አመትዋ ሚሪያም ክላይንቢስት እነሱ ቤት በማዕድ ጠረጴዛ ዙሪያ የፖለቲካ ጉዳይ ለዉይይት አይቀርብም ነበር።  «ቤተሰባችን ዉስጥ በፖለቲካ ጉዳይ የተወያየነዉን ነገር አላስታዉስም።በዚያን ግዜ የእኛ ፍላጎት ያተኩር የነበረዉ ትምህርት ላይ፤ እንዲሁም ምን ቢማር አንድሰዉ ኑሮዉ ይሻሻላል የሚለዉ ነበር። አዋቂዎቹም ቢሆኑ የፖለቲካ ጉዳይ በቅቷቸዉ ነበርና በሰላም ስለሚኖሩበት ሁኔታ ብቻ ነበር የሚያስቡት። በርግጥ ጀርመን ዉስጥ ምን ተካሄደ በሚለዉ ጉዳይ ይወያዩ ይሆናል እንጂ ሌላ የሚነሳ ነገር አልነበረም፤,,,» ቆየት ብሎ በርካታ ታዋቂ አይሁዳዉያን የሚደርስባቸዉን በደል ለመታገል ፤ ፀረ- አፓርታይድ እንቅስቃሴአቸዉን ጀመሩ። ሚሪያም እና በደቡብ አፍሪቃ ኬፕታዉን ግሪን ፖይንት በመባል የሚታወቀዉ የአይሁዳዉያን ማህበር አባላትም እንዲሁ የበኩላቸዉን ማድረግ ጀመሩ። በአፓርታይድ ስርአት ትምህርት ላልተፈቀደላቸዉ ጥቁሮች ትምህርት እንዲማሩ እያመቻቹ ለ1000 ተማሪዎች የምግብ ማደያ ካርድ እየሰጡ እና ከትምህርት ቤት የሚሰጡ የቤት ስራዎችን እያገዙ ይረዱ ነበር በዚህም ነዉ አሁን በሚሪያም የመኖርያ ቤት ኮሪደር ዉስጥ የተለያዩ የምስጋና ወረቀቶች ተሰቅለዉ የሚገኙት።  የሚሪያም የበኩር ልጅ ሮኒ ሄልዝ ፊልድ እንዲህ ያስታዉሳሉ  «ቤተሰቦቼ በየቀን የህይወት ገጠመኛቸዉ ሂደት የተሻለ ነገር ለማድረግ ሞክረዋል። አፓርታይድን የሚያራምደዉ መንግስት የየሰዉን በራስ የመተማመን ስሜት ሲሰርቅ እኛ በየቀኑ የምንገናኛቸዉ ሰዎችን በትክክል እና በእኩልነት ለማስተናገድ ሞክረናል»  ዛሬ ደቡብ አፍሪቃ አነሰም በዛ ጥሩ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የሰፈነባት ነፃ የሆነ ህገ-መንግስት ካላቸዉ የአለም አገራት አንዷ ሆናለች። ለዚህም የህዝብ አሰፋፈሯንና የልዩ ልዩ ቋንቋዎች ህብሯን ለመግለጽ በቀስተ ደመና የምትመሰለዉ ሀገር፤ ምንም እንኳ ሙስና፤ በዘምድና መጠቃቀም እንዲሁም ድህነት ቢያስቸግራትም ቅሉ የህዝቦችዋን ፍላጎት እኩል ለማዳረስ ጥረት ላይ ትገኛለች።  በአሁኑ ወቅት ደቡብ አፍሪቃ በሚገኙት አይሁዳዉያን ማህበረሰቦች፤ መካከል  ልዩነቶች እየታዩ ነዉ። የአይሁዳዉያን  ሃይማኖት መሪዎች በአክራሪ ሃይማኖተኞች እና በለዘብተኛዉ ማህበረሰብ፤ እንዲሁም ከምስራቅ አዉሮጳ እና ከሩስያ የሚመጡትን ለማላመድ እና የሚታየዉን ልዩነት ለማጥበብ መስራት ይኖርባቸዋል። የ94 ዓመቱ ጉንተር ክላይንቢስት እና ባለቤታቸዉን የ 89 ዓመትዋ ሚሪያም ጋር ለመጎብኘት በወይን ተክል ወደምትታወቀዉና በሰሜናዊ ኬፕታዉን ወደምትገኘዉ ሪቤክ ካስትል እናምራ። የሚሪያም ሁለተኛ ልጅ ማይክል በደቡብ አፍሪቃ አፍሪቃንስ የተሰኘዉን ቋንቋ የምትናገር እና የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ ባለቤቱ እና ልጆቹ ጋር ይኖራል። እነዚህ የተለያየ እምነት ያላቸዉ ጥንዶች ልጆቻቸዉ የሚከተሉት የአያቶቻቸዉን የአይሁድ እምነትን ይሆን? «የአይሁድ እምነት አንዱ ጎናቸዉ ቢሆንም ፤ ግን ጠንካራዉ እምነት በዉስጣቸዉ የለም። የሚያጋድሉት ግን ወደተለያየዉ የክርስትናዉ ህይወት ነዉ። ለምሳሌ የልጅ ልጄ ክርስትና ህይወትን አምኖ የተቀበለ ነዉ ነገር ግን በአመት ሁለት ግዜ ከኛ ጋር የአይሁዳዉያንን የእምነት በአል ያከብራል። ምርጫዉን ለነሱ ትተነዋል፤ ለኛ ጥሩዉ እንደዚያ ቢሆን  ነዉ።» ሰሜናዊ ኬፕታዉን አቅራብያ የሚገኘዉን አካባቢን ለቀን ወደ ኬፕታዉን ከተማ ተመለስን፤  የመልካም ተስፋ መናፈሻ ወደሚባለዉ ወደአዛዉንቶች መኖርያ። የሰማንያ ዘጠኝ አመትዋ የሳምሶን ቤተሰብ አባል ሚሪያም ክላይንቢስት ክፍላቸዉ ዉስጥ ሆነዉ በመስኮት አሻግረዉ በርቀት ይመለከታሉ፤ የጥቁሮች ነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ሁለት አስርተ አመታት ወደ አሳለፉበት ሮቢን በተሰኘዉ ደሴት ላይ ወደሚገኘዉ ወህኒ ቤት። በተጓዳኝ ሚሪያም በአፍሪቃ ከ75  አመት በላይ የኖሩበትን ግዜ ያስታዉሳሉ። ወ/ሮዋ በመጭዉ የጎርጎረሳዉያኑ ዓመት የ90 አመት የእድሜ ባለ ጸጋ ይሆናሉ።
«እናቴ እጣ ፈንታ ድንቅ ነገር ነዉ አንድ ሰዉ በአግባቡ ሊጠቀምበት እንዲችል ወደ ትክክለኛዉ አቅጣጫ ስቦ ማስተካከል እስከ ቻለ ድረስ በማለት ትናገር የነበረዉ በእርግጥ እዉነት ነዉ። ምናልባት ማለት የፈለኩትን በትክክል መግለፅ አልቻልኩ ይሆናል። ማለት የፈለኩት ግን፤ በእርግጥ ሁኔታዉ ሁሉ ቀላል አልነበረም። ሆኖም በጥሩ ሁኔታ አልፎአል።» አድማጮች በዶቼ ቬለዉ ሉድገር ሻዶምስኪ በሁለተኛዉ አለም ጦርነት ወቅት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ስለፈለሱት አይሁድ ጀርመናዉያን ታሪክ የተፃፈዉን ታሪክ ቅንብር ነበር ያደመጣችሁት፤ በሚቀጥለዉ ሳምንት በሌላ ርዕስ ቅንብር እስክንገኛኝ እሰናበታለሁ።  

Spurensuche: Deutsch-jüdisches Kulturerbe
ምስል DW/L.Schadomsky
Deutsch-jüdisches Kulturerbe in Südafrika Bildergalerie Bild 7
ምስል DW/Schadomsky
Deutsch-jüdisches Kulturerbe in Südafrika Bildergalerie Bild 4
ምስል DW/Schadomsky

አዜብ ታደሰ

ሸዋዪ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ