1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብዝኃ ከተሞች አወቃቀር

ሰኞ፣ ነሐሴ 2 2014

አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጲያ ህዝቦች ክልል ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደው የብዝኃ ከተሞች አወቃቀር የክልሉን ፖለቲከኞችና ሊህቃን እያወዘገበ ይገኛል ፡፡ አንዳንዶቹ አወቃቀሩ አስፈጻሚ ተቋማትን በተለያዩ ከተሞች ሥለሚበትን አገልግሎት ፈላጊ ነዋሪውን ለእንግልት ይዳርጋል በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4FGhH
Äthiopien | Stadt Bonga in Süd Äthiopien
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የብዝኃ ከተሞች አወቃቀር እና ደቡብ ሞዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል

አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጲያ ህዝቦች ክልል ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደው የብዝኃ ከተሞች አወቃቀር የክልሉን ፖለቲከኞችና ሊህቃን እያወዘገበ ይገኛል ፡፡
አንዳንዶቹ አወቃቀሩ አስፈጻሚ ተቋማትን በተለያዩ ከተሞች ሥለሚበትን አገልግሎት ፈላጊ ነዋሪውን ለእንግልት ይዳርጋል በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአንፃሩ  ሌሎች ደግሞ አሠራሩ በከተሞች መካከል የተመጣጠነ ዕድገትን ለመፍጠር የሚያስችል ነው በማለት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡
የብዝኃ ከተሞች አወቃቀር በኢትዮጲያ የሚታየውን የአውራ ከተማነትን ባህሪ የሚያስቀር መሆኑን የገለጹት የከተማ ዘርፍ ሙሁራንና ተመራማሪዎች በበኩላቸው አደረጃጀቱን የፌዴራሉ መንግሥት ጭምር በተሞክሮነት ወስዶ ሊተገብረው ይገባል ይላሉ ፡፡
አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው የተባለለትን የብዙሃ ከተሞች አወቃቀር ገቢራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ በክልሉ የተዘጋጀው የዋና ከተማ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በክልሉ እኩል ደረጃ ያላቸው አራት ዋና ከተሞች እንደሚኖሩት ይደነግጋል ፡፡ የከፋ ዞን ቦንጋ የፖለቲካና የርዕሰ መስተዳድር ፣ የዳውሮ ዞን ተርጫ የክልሉ ም/ቤት ፣ የቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን የዳኝነት አካላት እንዲሁም የሸካ ዞን ቴፒ የብሄረሰቦች ም/ቤት መቀመጫ እንደሚሆኑ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተዘርዝሯል፡፡
የክልሉ መንግሥት የብዝሃ ከተሞች አወቃቀሩ በከተሞች መካከል የተመጣጠነ ዕድገት ለማስገኘት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ቢገልጽም ፤ አደረጃጀቱ ግን  ድጋፍም ተቃውሞም እያስተናገደ ይገኛል፡፡
በክልሉ የሚንቀሳቀሱት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ / ኢዜማ / እና ነጻነትና እኩልነት ፖርቲ በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ የከተማ አደረጃጀቱ የሕዝቦችን የመልማት ጥያቄ በፍትሃዊነት የሚመልስ ነው በሚል ለአዋጁ ተግባራዊነት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአንጻሩ የካፋ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ሕብረት በበኩሉ ረቂቅ አዋጁ ተቋማትን ወደ ተለያዩ ከተሞች ስለሚበትን አገልግሎት ፈላጊ ነዋሪውን ለእንግልት ይዳርጋል ሲል ሥጋቱን ገልጿል፡፡ ፓርቲያቸው ረቂቅ አዋጁን የተቃወመበትን ምክንያት ለዶቼ ቬለ DW የገለጹት የሕብረቱ ሊቀመንበር አቶ ቦጋለ ሃይሌ ‹‹ አስፈጻሚ አካላት በተለያዩ ቦታዎች ይደራጁ የሚለው አጨቃጫቂ አጀንዳ እየሆነ ይገኛል ፡፡ ምክንያቱም  አስፈጻሚ አካላት ከተበተኑ ህዝቡ አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም ሦስት እና አራት ቦታ እንዲንከራተት ያደርገዋል፡፡ ተቋማቱ በአንድ ቦታ ላይ ከሆኑ ግን ጉዳዩን በቀላሉ በእንድ ማዕከል ለማስፈጸም ይችላል ፡፡ ሥለሆነም አደረጃጀቱ ከወጪ አንፃር ጉዳት አለው ›› ብለዋል፡፡
ዶክተር ኢንጂነር እሸትአየሁ ክንፉ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የከተማና ቀጠናዊ ልማት መምህርና ተመራማሪ ናቸው፡፡ ዶክተር እሸትአየሁ ‹‹ የብዝሃ ከተሞች አወቃቀር በአፍሪካም ሆነ በሌሎች የዓለም አገራት የተለመደ ስለሆነ ሊያስደነግጠን አይገባም ›› ይላሉ ፡፡
‹‹ የብዝኃ መቀመጫ ከተማን መጠቀም በብዙ አገራት በጣም የተለመደ ነው ፡፡ ለምሳሌ በአፍሪካ ብቻ ደቡብ አፍሪካ  ፣ ታንዛኒያ ፣ ቤኒን፣ ኮትዲቮር የመሳሰሉ አገራት የኢኮኖሚ ፣ የፖለቲካ በሚል አንድንዶቹ ሁለት ሌሎቹ ደግሞ ሦስት የመቀመጫ ከተሞች አላቸው፡፡ በኢትዮጲያ ሁኔታ በተፈጥሮዊ አቀማመጥና በተለያዩ ምክንያቶች ከተሞችን ለተለያዩ ሥራዎች የመጠቀም ሁኔታ  አለ ፡፡ ነገር ግን በህግ በተደነገገ መልኩ አኩል የአስተዳደር ከተማ የማድረግ ልምዱ አዲስ ነው ›› ብለዋል ፡፡ 
የብዝኃ መቀመጫ ከተማ አወቃቀር ምን ጥቅም ያስገኛል ? አገልግሎት ፈላጊ ነዋሪውን ለእንግልት አይዳርግም ወይ ? በሚል በዶቼ ቬለ DW  የተጠየቁት ዶክተር እሸትአየሁ ‹‹ ነገሩ የእይታ ጉዳይ ነው ፡፡ ለምሳሌ ሚዛንን ወይም ቦንጋ ከተማን የሁሉ ነገር መቀመጫ ብታደርገው አውራ ከተማ / urban privacy / በመሆን በአካባቢው ያሉትን ሌሎች ከተሞች ማቀጨጫቸው  አይቀርም ፡፡ የብዝኃ መቀመጫ አወቃቀር ይህን ችግር ያስቀራል ፡፡ ይህ በጥናት የተረጋገጠ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሲሆን የትኞቹ ተቋማት የት ከተሞች ላይ መሆን አለባቸው ፤እንግልቶች እንዳይፈጠሩ  በተቋማቱ እና በአገልግሎት ሰጪው መካከል ምን ያህል ትሥሥር አለ የሚለውን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ማከናወን ይጠይቃል ፡፡ በእኔ ግምት ወይም እንደ አንድ ባለሙያ የከተሞች አደረጃጀቱ እንደ አገር ከተተገበረ በኋላ የተገኘው ልምድ ተቀምሮና አሥፈላጊው ማሻሻያ ተደርጎበት የፌዴራሉ መንግሥቱ ጭምር ቢተገብረው ጠቃሚ ነው ብዬ እመክራለው ›› ብለዋል ፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ያዘጋጀውና አስተያየቶች እየቀረቡበት የሚገኘው ረቂቅ አዋጅ ነገ ማክሰኞ በቦንጋ ከተማ በሚካሄደው የክልል ም/ቤት ጉባኤ ላይ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፌዴራሉ ሪፖብሊኩ 11ኛ ክልል በመሆን የተቋቋመው መስከረም 20 2013 ዓም በተካሄደው የሕዝበ ውሳኔ ድምጽ ውጤት መሠረት ነበር፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ

Äthiopien Bonga | Wahl
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW
 Äthiopien Stadt Bonga
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW Korri