1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የአውሮፓ የድንበርና ጠረፍ ጠባቂ ድርጅት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 12 2008

የአውሮፓ ህብረት በውጭ ድንበሮቹ ላይ ከቀድሞው የተጠናከረ ጥበቃ ለማድረግ ማቀዱን ባለፈው ሳምንት አስታውቋል ። ህብረቱ እንዳለው አባል ሃገራት ድንበራቸውን የማይጠብቁ ከሆነ የህብረቱ የድንበርና ጠረፍ ጠባቂ ድርጅት ቁጥጥሩን እንዲያከናውን አቅዷል ። እቅዱን አንዳንድ ባህል ሃገራት ሲደግፉት አንዳንዶች ደግሞ ተቃውመውታል ።

https://p.dw.com/p/1HRsq
Griechenland Frontex Küstenwache bei Lesbos
ምስል Getty Images/AFP/D. Dilkoff

አወዛጋቢው የአውሮፓ የድንበርና ጠረፍ ጠባቂ ድርጅት

በጎርጎሮሳዊው 2015 አውሮጳ የገባው ስደተኛ ብዛት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በክፍለ ዓለሙ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል ። ዓለም አቀፍ የሥደተኞች ጉዳይ ድርጅት IOM እንዳስታወቀው በዓመቱ ወደ አውሮፓ የተሰደደውከ 1 ሚሊዮን በልጧል ።ጦርነት ካመሰቃቀላቸውና ጭቆና ከበረታባቸው ሃገራት ወደ አውሮፓ የሚደረገው ስደት አሁንም ቀጥሏል ። ከዚህ ቀደም ስደተኞች በብዛት ወደ አውሮፓ የሚገቡት በኢጣልያ ደሴቶች በኩል ነበር ። አሁን ደግሞ አብዛኛዎቹ በቱርክ አቆራርጠው በግሪክ ደሴቶች አድርገው በባልካን ሃገራት በኩል ነው ወደ ሰሜን አውሮጳ የሚመጡት ። የአውሮፓ ህብረት የህብረቱ ድንበር በሆኑት ግሪክ ኢጣልያና ማልታን በመሳሰሉ ሃገራት በኩል ወደ ተቀረው የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገር በሚገባው ስደተኛ ላይ ከእስካሁኑ የጠበቀ ቁጥጥር ለማካሄድ ባለፈው ሳምንት አንድ አዲስ እቅድ አውጥቷል ። ለዚሁ ዓላማም ፍሮንቴክስ የተባለውን የህብረቱን የድንበር ጠባቂ ድርጅት፣የተጠናከረ አቅም ይኖረዋል በተባለው የአውሮፓ የድንበርና ጠረፍ ጠባቂ ድርጅት ለመቀየር ታስቧል ።የፍሮንቴክስ ቃል አቀባይ ኤቫ ሞንክዩር እንዳሉት አዲሱ የድንበር ጠባቂ ድርጅት አሁን በድንበር ጥበቃ ከተሰማራው ከፍሮንቴክስ በተለየ ፣መጠኑ የታወቀ ና ከቀድሞውም ከፍ ያለ ድንበር ጠባቂ ተጠባባቂ ኃይል ይኖረዋል ።
« አንደኛ ወደ 1500 የሚሆኑ በድርጅቱ ትዕዛዝ የሚንቀሳቀሱ ድንበር ጠባቂዎች ይኖሩታል ። በአሁኑ ጊዜ ፍሮንቴክስ በአውሮፓ የውጭ ድንበር ላይ ጠባቂዎችን የሚያሰማራው ሁሌም አባል ሃገራት ድንበር ተቆጣጣሪ እንዲያዋጡ እየጠየቀ ነው ።እነዚህን የመሳሰሉ የሰው ኃይልና የመሣሪያዎች መዋጮ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ሁሉም አባል ሃገራት የሚፈለገውን ላያሟሉ ይችላሉ ።»
ለዚህ ሞንክዩር እንደ ምሳሌ ያነሱት በቅርቡ በግሪክ ድንበር ላይ ሊወሰድ ለታሰበው እርምጃ የተጠየቀውን የሰው ኃይልና የተገኘው ምላሽ ነበር ።
« በግሪክ ለታቀደው ዘመቻ የፍሮንቴክስ ሃላፊ በዚህ ዓመት በጥቅምት ወር ፣ አባል ሃገራት 775 ድንበር ጠባቂዎችን እንዲልኩ የሚጠይቅ ደብዳቤ ልከው ነበር ። ሃገራቱ ማዋጣት የቻሉት ከ450 በላይ ድንበር ተቆጣጣሪዎችን ነው ። ይህ ብዙ ቁጥር ነው ። ሆኖም በተለይ በግሪክ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ለማካሄድ ተጨማሪ ተቆጣጣሪዎች ያስፈልጋሉ ። »
በቂ ና ቋሚ ድንበር ጠባቂ ኃይል የሌለው ፍሮንቴክስ በሚሰማራባቸው ሃገራት ያለው ሥልጣንም የተገበደ ነው ።ይህም ከድርጅቱ ተግዳሮቶች አንዱ ነው ይላሉ ሞንክዩር ።
«እስካሁን በሚሰራበት ህግ በፍሮንቴክስ ሥር ያሉ ድንበር ጠባቂዎች የስደተኞችን የግል ዳራ የመመርመር መብት የላቸውም ።ያ ማለት ማንኛውንም መረጃ ማጣራት አይችሉም ።እናም የደህንነት ጉዳዮችን በራሳቸው ማጣራት ካልቻሉ ሥራውን የዘመቱበት ሃገር መኮንኖች ሊያከናውኑ ይገባል ። ማናቸውንም የስደተኞች የግል ዳራዎች ለብሔራዊ ባለሥልጣናት ማስተላለፍ አለባቸው ። እያንዳንዱ ስደተኛ በተገቢው መንገድ መመዝገብ ፣ማንነቱ መታወቅ አለበት አሁን ባለው ሁኔታ ይህ ፈታኝ ሆኗል ።መኮንኖቹ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ሂደቱን ያጓትተዋል ።»
ፍሮንቴክስ በቅርቡ 376 ድንበር ጠባቂዎችን የሚያሰማራበትን ዘመቻ በግሪክ የባህር ጠረፍ ይጀምራል ።በዘመቻው ከአውሮፓ ህብረትና ከ26 ቱ የሸንገን ስምምነት ፈራሚ አባል ሃገራት የሚውጣጡ ድንበር ጠባቂዎች ይካፈላሉ ። ሞንክዩር እንደሚሉት ወደፊት ተጠባባቂው ኃይል እንደታሰበው የሚቋቋም ከሆነ፣ ለሚፈለገው ተልዕኮ ፣በሚፈለግበት ጊዜ ያለ አንዳች ችግር ሊሰማራ ይቻላል ።ለተልዕኮ ስኬት አስፈላጊ የሆነው በጀት እንደሚጨምርም ተነግሯል ። ከዚህ ሌላ የድንበር ተቆጣጣሪዎችን ዘመቻ የሚያስተባብሩ የአዲሱ የአውሮፓ የድንበርና የጠረፍ ተቆጣጣሪ ድርጅት ሠራተኞች ቁጥርም ቀስ በቀስ እንዲያድግ ይደረጋል ።
«የድርጅቱ የሚቀጥለው ዓመት በጀት 250 ሚሊዮን ዩሮ ነው ። በጀቱ ከ2014 ዓመተ ምህረት አንስቶ ነው የተጨመረው ። ባለፈው ዓመት 90 ሚሊዮን ዩሮ ተጨማሪ በጀት አግኝቷል ። በቀረበው ሃሳብ መሠረት ደግሞ ከዚህም በላይ አድጎ 300 ሚሊዮን ዩሮ ይደርሳል ተብሎ ይታሰባል ።የሠራተኛው ቁጥርም ከአሁኑ 320 ወደ 1 ሺህ ያድጋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው »
ፍሮንቴክስ ከዚህ ቀደም ለድንበር ጥበቃ ዘመቻ የሚሰማራው ከአባል ሃገራት የእርዳታ ጥያቄ ሲቀርብልለት ነበር ። ጥያቄ ካልመጣ ስለ አንዳንድ አካባቢዎች አደገኛነት የተካሄደ ጥናት ሁኔታዎች አስቸጋሪ መሆናቸውን የሚጠቁም ቢሆን እንኳን አባል ሃገራት ፍሮንቴክስ እንዲሰማራ ላይወስኑ ፣ ጥቂት እንጠብቅም ሊሉ ይችላሉ ።በሞንክዩር አገላለጽ በአዲሱ የድንበር ተቆጣጣሪ ድርጅት ይህ አሠራር ይቀየራል ። ድርጅቱም በዚህ ሥራ የመሪነቱን ቦታ ይይዛል ።
«ፍሮንቴክስ በአንድ የአባል ሃገር ድንበር ላይ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነ በቀጥታ ለአባል ሃገሩ አሳውቆ አባል ሃገሩም ዘመቻ እንዲካሄድ ሊፈቅድ ይችላል ። ይህ ካልሆነ ደግሞ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፣የሸንገን አባል ሃገራት ለአደጋ መጋለጣቸውን በመግለፅ ፣ በህብረቱ ውሎች መሠረት ዘመቻ እንዲካሄድ ለተፈለገበት አባል ሃገር አስፈላጊነቱን ያሳስባል። ከዚያም ፍሮንቴክስ ሥራውን ሊያካሂድ ይችላል ። በርግጥ ይህ የመጨረሻው አማራጭ ነው የሚሆነው። በሂደት የሚደረስበት አማራጭ ነው ። »
ግሪክ ድንበርዋን ባለመጠበቅ፣ ወደ ሃገርዋ በብዛት የሚገቡ ስደተኞችን ባለመመዝገብ ፣ማንነታቸውንም ሳታጣራ፣ ጀርመንና ስዊድንን ወደ መሳሳሉ ሃገራት እንዲሄዱ በማሳለፍ ከፍተኛ ትችት ቀርቦባታል ። ይህን መሰሉ ቁጥጥር የማይካሄድበት የስደተኞች እንቅስቃሴ ደግሞ በአውሮፓ የደህንነት ስጋት ፈጥሯል ። ክፍለ ዓለሙ የሚወደስበትን ፣ ህዝብ በነፃ የሚዘዋወርበትን የሸንገን ቀጣና እንዳይፈረካክስም አስግቷል ። በነዚህ ስጋቶች መንስኤ አባል ሃገር ድንበር መቆጣጠር ሲያቅተው ወይም ድንበር ለመቆጣጠር አስፈላጊዎቹን እርምጃዎች መውሰድ ካልፈለገ እና ይህም የሸንገን ስምምነት አባል ሃገራትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ተብሎ ከታሰበ አዲሱ የአውሮፓ የየብስና የጠረፍ ጠባቂ ድርጅት በአስቸኳይ ጣልቃ በመግባት የጋራውን ድንበር የመቆጣጠር እርምጃ እንዲወስድ ይጠበቃል ።እቅዱን ኢጣልያ ጀርመንና ፈረንሳይ ሲደግፉት ከምሥራቅ አውሮጳ ሃገራት በኩል ደግሞ ተቃውሞ ገጥሞታል ።ሥደተኞች እንዳይገቡ ድንበሯን ያጠረችው ሃንጋሪ እቅዱን « ያልተመጣጠነ »ስትለው ፖላንድ ደግሞ «ኢ-ዲሞክራሲያዊ» ስትል ተችታዋለች ።የህብረቱ ባለሥልጣናት ለነዚህ ና ለሌሎችም የእቅዱ ሎዓላዊነትን ይጋፋል ሲሉ ለተቃወሙ አባል ሃገራት በሰጡት መልስ ድርጅቱ በአንድ ሃገር ለዘመቻ ከመሰማራቱ በፊት ዘመቻው የሚካሄድበት ሃገር ይሁንታን ማግኘት እንደሚኖርበት ና ህብረቱም አባል ሃገራት የውጭ ድንበር ጠባቂ መሰማራትን እንዲቀበሉ ጫና የማያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል ። የፍሮንቴክስ ቃል አቀባይ ሞንክዩርም እቅዱ ኢዴሞክራሲያዊ መባሉን አልተቀበሉትም ፣ ይልቁንም በአውሮፓ ድንበር ተቆጣጣሪ ድርጅት አማካይነት የሚወሰድ ይህን መሰል እርምጃ ተግባራዊ እንዲሆን የታሰበበትን አባል ሃገር ስምምነት የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን በድርጅቱ አስተዳደር ቦርድ ተመክሮበትና ስምምነት ላይ ከተደረሰ ብቻ በተግባር የሚተረጎም ነው ብለዋል ።
«ፍሮንቴክስ በአስተዳዳሪ ቦርድ ነው የሚተዳደረው ። ይህ ቦርድ ደግሞ የሸንገን ስምምነት አባል ሃገራት የድንበር ጉዳይ ባለሥልጣናትን ያካትታል ። ከዚህ ሌላ ቦርዱ ውስጥ ሁለት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ተወካዮች ይገኛሉ ። ፍሮንቴክስ በተለያዩ ጊዜያት ከአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የተለያዩ ኮሚቴዎች ለሚቀርቡለት ጥያቄዎችና ዘገባዎች መልስ ይሰጣል ። ማናቸውም ውሳኔ የሚያስፈልገው ከባድ ጉዳይ በቦርድ ደረጃ ውይይት ይካሄድበታል ። ለማናቸውም ውሳኔዎች ደግሞ የቦርድ አባላት ስምምነት ያስፈልጋል »
የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎች ባለፈው ሳምንት ባካሄዱት የ2015 የመጨረሻው ጉባኤያቸው በአውሮፓ ያለ ቁጥጥር የሚካሄድ የስደተኞች እንቅስቃሴን ለመከላከል ይበጃል በተባለው በአዲሱ የአውሮፓ ህብረት የድንበርና የጠረፍ ጠባቂ ድርጅት ጉዳይ ላይ በስድስት ወራት ውስጥ ውሳኔ እንዲሰጥ ተስማማተዋል ። እቅዱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት እና በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ መፅደቅ ይኖርበታል ።

Italien Küstenwache Navy Rettungsoperation
ምስል Getty Images/Tullio M. Puglia
Mitglieder von Frontex auf einem Schiff vor der Insel Lesbos Griechenland
ምስል picture-alliance/AP Photo/A.Palacios
Griechenland Flüchtlingsboot und Flugzeug von Frontex
ምስል Reuters/Y. Behrakis
Kroatien Slowenien Deutschland Frontex Polizei
ምስል picture-alliance/Pixsell/G. Stanzl

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ