1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በፅንፈኛዉ መሪ ላይ የክስ ሂደት በ«ICC»

ሰኞ፣ ነሐሴ 16 2008

አኽመድ ኧል ፋቂ ኧል ማሃዲ የተባለ የፅንፈኞች መሪ በሰሜን ማሊ ቲምቡክቱ በዓለም ቅርስ የተመዘገቡ ቅርሶችን በማዉደሙ ዛሬ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ የጥፋተኝነት ብይን ተላለፈበት። ይህ አይነት ክስ በፍርድ ቤቱ ሲቀርብና ብይን ሲሰጥ ዛሬ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1Jn9z
Mali Ahmad Al Faqi Al Mahdi vor dem Internationalen Strafgerichtshof in Den Haag
ምስል Reuters/R. van Lonkhuisen



በሰሜናዊ ማሊ የሚንቀሳቀሰዉና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለዉ የሚነገረዉ አንሳር ዲን የተባለዉ ፅንፈኛ ቡድን መሪ አኽመድ ኧል ፋቂ ኧል ማሃዲ ዛሬ ዴንሃግ ኔዘርላን በሚገኘዉ ዓለም አፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ፤ ክሱን በጥልቅ ኃዘኔታ ማመኑ ተዘግቦአል። አኽመድ ኧል ፋቂ ኧል ማሃዲ ወንጀሉን ካመነ በኋላ የማሊን ማኅበረሰብ ይቅርታ መጠየቁም ተመልክቶአል። በጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ,ም ኧል ማሃዲ በቲምቡክቱ የሚገኝ ዘጠኝ ጥንታዊ መቃብር ቤቶችንና አንድ መስጊድን ለማዉደም ጽንፈኞችን አደራጅቶአል በሚል ነበር ክስ የተመሰረተበት። በጥንታዊዋና ንግድ ማዕከል በነበረችዉ ቲምቡክቱ ዉስጥ በመካከለኛዉ ክፍለ ዘመን የታነፀ ታሪካዊ ቅርስ ሲወድም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጣና ሃዘንን ማስነሳቱ ይታወሳል። በሰሜን ማሊ ሰሐራ ምድረ በዳ ጫፍ ላይ የምትገኘው በቲምቡክቱ፤ ከመቶ ዓመታት በላይ የእስላም ዋንኛ ባህላዊ ማዕከል ሆና መቆይትዋ ይታወቃል። ዛሬ ለፍርድ ችሎት የቀረበዉ የፅንፈኛዉ አንሳር ዲን ቡድን መሪን ለፍርድ ያቆሙት የከሳሾች ዋና ተጠሪ ፋቱ ቤንሱዳ ወንጀሉ በማኅበረሰቡ ክብርና ማንነት ላይ የተቃጣ የፈሪ ጥቃት ሲሉ ተናግረዋል።


አዜብ ታደሰ


አርያም ተክሌ